ከእንስሳት ተነስተው ወደ ሰው ከሚተላለፋ የቫይረስ ዘሮች 'ዙኖሲስ' ከሚባሉት ጎራ የሚመደበውና ጎጂነቱ እምብዛም ነው የተባለው 'የዘንጀሮ ፈንጣጣ' የአለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው ከዚህ ቀደም የበሽታው መገኛ ናቸው ከተባሉት የአፍሪካ ሀገራት ውጪ ባሉ ሀገራት መከሰቱን ይፋ አድርጓል።
ከግንቦት 5 2014 ዓ.ም ጀምሮ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ስዊድን እና ስፔንን ጨምሮ በ23 ሀገራት የተከሰተው በሽታው አሁን ላይ የአለም የጤና ድርጅት መካከለኛ ደረጃ የአለም የጤና ስጋት ነው ሲል የበሽታውን ደረጃ በግንቦት 29 2022 በአውሮፓዊያኑ ሪፖርቱ አስታውቋል። እንደ ሪፖርቱ ገለጻ እስከአሁን በበሽታው ተይዞ ለሞት የተዳረገ ባይኖርም 257 በበሽታው መያዛቸውን እና ከ120 ሰዎች ደግሞ በሽታው ሳይኖርባቸው አይቀርም ብሎ መጠርጠሩን ገልጿል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ስያሜውን ያገኘው በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር እ.ኤ.አ በ1958 ለመጀመሪያ ጊዜ በዝንጀሮ ላይ ከተገኘ በኋላ ሲሆን ወደ ሰው ተላልፎ በቅድሚያ የተገኘው ደግሞ በማዕከላዊ አፍሪካ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እ.ኤ.አ 1970 ነበር። ከአፍሪካ ውጪም በ2003 እ.ኤ.አ በሀገረ አሜሪካ ከጋና ወደ አሜሪካ በገቡ እንስሳት አማካኝነት በአሜሪካ መታየቱን የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ መረጃ ያሳያል።
በዘንድሮ 2022 እ.ኤ.አ አህጉር ተሻግሮ አውሮፓ እና አሜሪካ ላይ የተከሰተው በሽታው ምንም እንኳን በእነኚህ ሀገራት መታየቱ በተለያየ መገናኛ ብዙሃን ቢነሳም በሽታው መነሻው ናቸው በሚባሉ የአፍሪካ ሀገራት እስከሞት የደረሱ የበሽታ ሪፖርቶች በቅርብ ወራት ተስተውለዋል። ለአብነትም ከዴሴምበር 2021 እ.ኤ.አ ጀምሮ በካሜሮን ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኮንጎ፣ ናይጄሪያ ከ1ሺህ 3 መቶ 15 በላይ ሰዎች ተይዘው 67 ሰዎች መሞታቸው የአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያሳያል።
በማዕከላዊ አፍሪካ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊኮ ኮንጎ ለመጀመሪያ ጊዜ የተስተዋለው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ሁለት ዝርያዎች አሉት የማዕከላዊ እና የምዕራብ አፍሪካ ዝርያዎች ተብለው ይታወቃሉ።
በቀጥተኛ ንክኪ የሚተላለፈው በዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ከተጠቃ እንስሳ ወደ ሰው አልያም ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።
በዝንጀሮ ፈንጣጣ ከተጠቃ እንስሳ ጋር የሚደረግ ቀጥተኛ ንክኪ ፣ ወይም ከእንስሳቱ የሚወጡ ፈሳሽ ፣ ደም እና ስጋቸውን መመገብ ለበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎች ናቸው።
ትክክለኛ የበሽታው ተሸካሚ የሆኑ እንስሳት በሙሉ ባይታወቁም እንደአይጥ፣ ጥንቸል ፣ ሽኮኮ ያሉ እንስሳት ላይ እንዲሁም የሰውን ልጅ ጨምሮ እንደዝንጀሮ እና ጦጣ ያሉ አጥቢ እና ተራማጅ እንስሳት ላይ በጉልህ ይታያል።
በፈረንጆቹ 2019 ዓመት የተከሰተውና እስካሁንም ዓለማቀፍ የጤና ስጋት ሆኖ የቀጠለው ኮቪድ 19 ሙሉ ለሙሉ ሳይጠፋ አዲስ ሌላ ተላላፊ በሽታ መከሰቱ ሀገራትን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡
ከባድ የራስ ምታት፣ የጡንቻ ህመም፣ የድካም ስሜት ፣ የጀርባ ህመም፣ የሊንፍ እብጠት፣ የቆዳ ሽፍታ፣ የሰውነት ቁስለት የዝንጀሮ ፈንጣጣ ዋነኛ ምልክቶቹ የሆነው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በ1970 እ.ኤ.አ በአለም ጤና ድርጅት ከዓለም መጥፋቱ ከታወጀው ፈንጣጣ (Smallpox) ጋር እጅግ ተቀራራቢ ባህሪያት እና ምልክቶችን ያሳያል ።
የማይክሮባዮሎጂ መምህር የሆኑት መሳይ ምትኩን በዝንጀሮ ፈንጣጣ ባህሪያት እና ህክምና ጉዳይ አነጋግረናቸው ነበር።
"አሁን የበሽታውን መከሰት አዲስ ያደረገው መነሻው ነው ከሚባልበት አፍሪካ ውጪ በአውሮፓ እና አሜሪካ መገኘቱ ነው። ሌላ ጉዳይ ደግሞ በበሽታው የተያዙት ሰዎች ምንም የጉዞ ታሪክ የሌላቸው መሆኑ ነው" የሚሉት ማይክሮባዮሎጂስቱ መሳይ ምትኩ በቅርብ ወራት ሁለቱም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ዝርያዎች መነሻ ስፍራዎች አካባቢ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ሞትም መመዝገቡን ያስታውሳሉ።
ባሳለፍነው ግንቦት 13 2014 ዓ.ም ተቀማጭነቱን ናይሮቢ ያደረገውና የውጭ ሚዲያዎች ማህበር በአፍሪካ የተሰኘ የሚዲያ ባለሞያዎች ማህበር በአውሮፖ እና ሰሜን አሜሪካ ከበሽታው መቀስቀስ ጋር በተገናኘ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ጉዳዩን ለመዘገብ እየተጠቀሙባቸው የሚገኙትን በበሽታው የተጠቁ ጥቁር ሰዎች ምስል አጥብቆ ኮንኗል። በሽታውን ከጥቁሮች ጋር ለማያያዝ የሚደረገው ስራ ተገቢ እንዳልሆነና እንዲታረም በይፋዊ መግለጫው ላይ መግለጹ ይታወሳል።
የበሽታው መነሻ ዝንጀሮዎች ቢሆኑም የተለያዩ እንስሳት በበሽታው መጠቃታቸው የበሽታውን ስርጨት ለመቆጣጠር አንደኛው እንስሳ ላይ ብቻ በትኩረት እንዳይሰራ ማድረጉን የሚናገሩት ባለሞያው በገዳይነቱ ከዚህ ቀደም ከአለም ከጠፋው የፈንጣጣ በሽታ (smallpox) አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው ይላሉ። ህጻናት፣ ነብሰጡር ሴቶች፣ በተለያየ በሽታዎች ምክንያት የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተጎዳ ሰዎች ላይ እንደሚበረታ ይናገራሉ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ እና ከዓለም የጠፋው ፈንጣጣ እጅግ ተቀራራቢ ምልክትች አሏቸው። በአሁን ወቅት ለዝንጀሮ ፈንጣጣ ልንጠቀም የምንችለው ክትባት ከዚህ ቀደም ለፈንጣጣ (smallpox) ይሰጥ የነበረውን ነው ያሉት ማይክሮ ባዮሎጂስቱ መሳይ ምትኩ ከሰላሳ እና አርባ ዓመታት በፊት የፈንጣጣ ክትባትን የተከተቡ ሰዎች በአሁን ወቅት ክሮስ-ፕሮቴክት ሊያገኙና በዝንጀሮ ፈንጣጣው ያለመጠቃት እድል እንዳላቸው ይናገራሉ።
የፈንጣጣ በሽታን ከዓለም መጥፋት ተከትሎ የፈንጣጣ ክትባት መስጠት ከቆመ ከ3 አስርት ዓመታት በላይ ሆኖታል የሚሉት ባለሞያው ምናልባትም በሽታው ወጣቶች ላይ እድሜያቸው ከገፋ ሰዎች ይልቅ የተጠቂነት መጠናቸው ከፍ ሊል እንደሚችል ይናገራሉ።
ባለሞያው ክሮስ ፕሮቴክት ያሉትን ሀሳብ ሲያብራሩ በበሽታዎቹ ተቀራራቢ ተፈጥሮ እና ባህሪ ምክንያት ለአንደኛው የተሰጠ መድሃኒት እና ክትባት ለሌላኛው ሊያገለግል ይችላል ሲሉ ያስረዳሉ።
ከበሽታው ባህሪ ተነስተን የወረርሽኝ ስጋት ሊሆን ይችላል ያልናቸው ማይክሮባዮሎጂስቱ መሳይ ምትኩ " ለፈንጣጣ እንጠቀም የነበረውን ክትባት እና መድሃኒቶች መጠቀም ስለምንችል የወረርሽኝ ስጋት ይሆናል ተብሎ አያሰጋም።" ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተውናል።
በሽታው በሰውነት ውስጥ ገብቶ ምልክቶችን ለማሳየት ከ6 እስከ 13 ቀናት ይወስድበታል። እነኚህን ምልክቶች በራሱ ላይ አልያም በሌሎች ላይ የተመለከተ ሰው ራስን በማግለል እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።