በጎንደር ከተማ እና አካባቢዋ በዘንድሮው 2014 ዓ.ም በ9 ወራቶች ውስጥ 3397 ውርጃ ተፈጽሟል። ከእነዚህ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ያለ ጤና ባለሙያ ከትትል ደህንነቱ ባልተጠበቀ በባህላዊ መድሃኒት መንገድ የተከናወኑ ናቸው።
ውርጃ የሚባለውን ነገር ስንሰማ ብዙ አከራካሪ ሀሳቦች ይነሳሉ። ሆኖም ግን ጽንስ ማስወረድ ህጋዊ መሆን አለመሆን ያለው ውዝግብ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአለም ዙሪያ ሁሉ እንዳለ ይነገራል። ጽንስ ማስወረድን በተመለከተ የሲቪል ማህበራትም ሆነ የጤና ባለሙያዎች ያላቸው አስተያየት በሁለት ጎራ ከፍለው ይመለከቱታል።
በአንድ በኩል ጽንስ ማቋረጥ የሴቷ መብት ነው የሚል ሲሆን ሌላኛው ጎራ ደግሞ ጽንሱ ህይወት ያለው ፍጡር በመሆኑ ጽንስ ማስወረድ አውቆና ሆን ተብሎ ህይወት እንደማጥፋት ይቆጠራል የሚሉ ናቸው።
"በኢትዮጵያ የአፍላ ወጣቶች የጽንስ መቋረጥ ሁኔታ ጥናት" በሚል ርዕስ በጉትማቸር ኢንስቲትዩት እና በአይፓስ ትብብር ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በ2006 ዓ.ም ከነበሩት ጽንስ የማቋረጥ ተግባራት ውስጥ 64 በመቶ የሚሆኑት ደህንነታቸው የተጠበቀ በጤና ተቋማት የተደረጉ እንደነበሩ ያሳያል።
እድሚያቸው ከ25 እስከ 29 የሆኑት ሴቶች 46 በመቶ ጽንስ ያቋረጡ ናቸው። እንዲሁም እድሚያቸው ከ 35 አመት በላይ በሆኑ ሴቶች ከተደረገው ጽንስ ማቋረጥ ውስጥ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ በጤና ሞያተኞች የተከናወኑት 22 በመቶ ብቻ ናቸው። 78 በመቶ የሚሆነው በባህላዊ መድሃኒት፣ ፋርማሲ ያለማንም ትዕዛዝ ገዝቶ በመጠቀም (ደህንነቱ ባልተጠበቀ መልኩ) የተከናወኑ መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል።
አዲስ ዘይቤ ወደ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ባመራችበት ወቅት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ሃላፊ የሆኑትን ወ/ሮ ምሳ ታረቀኝን አናግራለች።
ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሀገራችን በ1997 ዓ.ም የተደረገው የጽንስ ማቋረጥ ህግ መሻሻል የፌደራል ወንጀል ህግ አንቀጽ 521 እንደሚለው ውርጃ የሚፈቀደው በጽንሱ ላይ የአፈጣጠር ችግር እንዳለበት ከታወቀ፣ እርግዝናው ለእናትየዋም ይሁን ለህጻኑ ለህይወታቸው አደገኛ ከሆነ፣ እርግዝናው የመጣው በአስገድዶ መደፈር ከሆነ፣ ከዘመድ አዝማድ ከተረገዘ፣ እድሚያቸው ከ18 አመት በታች ከሆነ እና አቅማቸው ልጅ ለማሳደግ ያልደረሱ ከሆኑ እንዲያስወርዱ ይፈቅዳል ብለውናል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደረጃ በዘንድሮው 2014 ዓ.ም በዘጠኝ ወር ውስጥ 1933 ውርጃ መፈጸሙን ነግረውናል። በአምናው 2013 ዓ.ም በዘጠኝ ወር ሪፖርት 1793 ውርጃ መፈጸሙን ተናግረው ከ ዘንድሮው 2014 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር 2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
የ 2013 ዓ.ም የ9 ወር ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአመቱ ውስጥ ከ 5760 ነፍሰ ጡሮች መካከል 1793 ሴቶች ውርጃ መፈጸማቸውን ገልጸው ከእቅዳቸው አንጻር ሲታይ 28 ፐርሰንት ያክል ውርጃ መፈጸሙን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ከዘንድሮው 2014 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር የ 9 ወር ሪፖርት ከ6481 ነፍሰጡር እናቶች ውስጥ 1933 የሚሆኑት አስወርደዋል። ከእቅዱ አንጻር ሲታይ 30 ፐርሰንት ያክሉ ውርጃ መፈጸማቸውን ነግረውናል።
በአብዛኛው በጤና ባለሙያ ሳይታገዙ ውርጃ የሚፈጽሙ ሴቶች እድሚያቸው 24 አመት በታች የሚሆኑት ናቸው የሚሉት ወ/ሮ ምሳ አብዛኞቹ ውርጃ የፈጸሙ ሴቶች በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደንቢያ በሚባል አካባቢ የሚኖሩ ናቸው ብለውናል። በዘንድሮው 2014 ዓ.ም ከ15 እስከ 19 የሚሆኑት 95 ሴቶች፣ ከ20 እስከ 24 የሚሆኑት 111 ሴቶች በዚህ አመት ውርጃ ያካሄዱ መሆናቸውን ያስታውሳሉ።
የጤና ባለሙያን ሳያማክሩ በባህላዊ መድሃኒት ጽንስ ማቋረጥ ጽንሱ ሙሉ ለሙሉ ሳይወጣ ሊቀር ይችላል። ጽንሱ ሙሉ ለሙሉ ሳይወጣ ሲቀር የጡት ህመም ይከሰታል። ወርጃው ከተፈጸመ በኋላ በስድስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የወር አበባ አለማየት ሊከሰት ይችላል። ለሳምንታቶች ያክል የማህጸን ውስጥ መድማት፣ ማቅለሽለሽ፣ ትኩሳት፣ ማስታወክ፣ ተቅማጥ አለፍ ሲልም ለሞት ይዳርጋል።
አዲስ ዘይቤ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያን ካነጋገረች በኋላ ወደ ከተማዋ ጤና መምሪያ አመራች። የጎንደር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት ኦፊሰር የሆኑት ወ/ሮ ሻሼ ዘውዱን ስለጉዳዩ አነጋገረች። በዘንድሮው 2014 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ውስጥ ብቻ 1464 ውርጃ መፈጸሙን ነገሩን ። ከ እነዚህ ውስጥ 648 ያክሉ ያለ ጤና ባለሙያ ትዕዛዝ በባህላዊ መድሃኒት ያስወርዱ ናቸው።
ያለ ጤና ባለሙያ ትዕዛዝ በባህላዊ መድሃኒት የሚያስወርዱ አብዛኞቹ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ የኮሌጅ ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸውን ነግረውናል።
ያልታሰበ እርግዝና የሚያጋጥማቸው ሴቶች ጽንሱን ለማቋረጥ ያልተገቡ ሙከራዎችን አድርገው ለአደጋ ይጋለጣሉ። ከጤና ባለሙያ ጋር ሳይነጋገሩ የባህል መድሃኒቶችን እና ከፋርማሲ የሚገኙ መድሃኒቶችን በመጠቀም፣ ሆዳቸውን በመደብደብ የውስጥ አካላታቸውን ለመጉዳት እና እራሳቸውን አውቀው ከፍ ካለ ቦታ ወደታች በመውደቅ ጽንሱን ለማወረድ የሚያደርጉት ሙከራ ለአደጋ እያጋለጣቸው እንደሆነ ነግረውናል።
አቶ አፈራ ጌታሁን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ እቅድ ዝግጅት ክትትል እና ግምገማ ኦፊሰር ናቸው። ባለፈው 2013 ዓ.ም በእነሱ ተቋም የ9 ወር ሪፖርታቸው 1457 ወርጃ መፈጸሙን ያሳያል። በአጠቃላይ በ 2013 ዓ.ም በ12 ወር 2410 ውርጃ ተፈጽሟል ።ከ እነዚህም ውስጥ 48 በመቶ የሚሆኑት ያለ ጤና ባለሙያ ክትትል ያስወረዱ ናቸው።
በጤና ባለሙያ የተደገፈ የጽንስ ማስወረድ የእናትየውን የወደፊት የመውለድ እድል ብቻ ሳይሆን ህይወትዋንም ጭምር ይጥብቅላታል። ጽንስ ካስወረዱ በኋላ በአስር ቀን ውስጥ ድጋሚ ሊያረግዙ ስለሚችሉ የወሊድ መቆጣጠሪያ ተብለው የሚጠሩ እንክብሎችን፣ በማህጸን ውስጥ የሚደረግ አይዩዲ፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ መርፌ እና በቆዳ ስር የሚቀበሩ ኢምፕላንቶች መጀመር እንዳለባቸው መክረዋል። በተደጋጋሚ ጽንስ ማስወረድ ለመካንነት ሊዳርግ ይችላል ብለውናል።