ግንቦት 22 ፣ 2014

የድሬን ከሰሞኑን ሙቀት የከዚራ ዛፎች ያስጥሏት ይሆን

City: Dire Dawaወቅታዊ ጉዳዮች

የድሬደዋ ነዋሪ ቶሎ ቶሎ እራሱን እንዲያቀዘቅዝ፣ ፈሳሽ አብዝቶ እንዲወስድ፣ በመኝታ ሰአት ከመከናነብ መቆጠብና ህፃናት እና አእምሮ ህሙማን ለብቻቸው እንዳይተዉ ሲል የከተማው ጤና ቢሮው አሳስቧል፡፡

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የድሬን ከሰሞኑን ሙቀት የከዚራ ዛፎች ያስጥሏት ይሆን
Camera Icon

Photo Credit: Dire Dawa Mayor’s Office

ሞቃታማ አየር ንብረት መገላጫዋ የሆነው ድሬደዋ ዘንድሮ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሙቀት መጠኗ ከፍ ብሏል፡፡  ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም የሙቀት መጠኑ እንደሚያሰጋ ማሳሰቢያ የከተማዋ ጤና ቢሮ አውጥቷል።

በአለማችን የሙቀት መጠን መጨመር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርስዋል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት (WHO) ባወጣው መረጃ መሰረት በአለም ዙሪያ ለከፍተኛ ሙቀት ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ቁጥር እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ በ125 ሚልየን አሻቅቧል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1998 እስከ 2017 በአለም ዙሪያ በከፍተኛ ሙቀት መጠን መጨመር የተነሳ 166000 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡  እ.ኤ.አ በ2003 ደግሞ በአውሮፓ ለሶስት ወራት (ከሰኔ እስከ ነሐሴ) በተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት 70000 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡

የአካባቢ ሙቀት ለሰውነታችን ጠቃሚ መሆኑን ያህል ከመጠን ያለፈ ሙቀት ደግሞ ጤናችን ላይ እክልን ያመጣል፡፡ ባስ ሲል ደግሞ እንደ ልብ ድካም እና ስኳር ዓይነት ተጓዳኝ በሽታዎች ላለበት ሰው ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡

በድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ  የኮምኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት የስራ ሂደት ሀላፊ ወ/ሮ ስንታየሁ ደበሳ እንደገለጹት የድሬደዋ ነዋሪ ሰሞኑን በተስተዋለው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ምክንያት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት የሚያሳስብ የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ መግለጫ እንዳወጣ ይናገራሉ፡፡ 

ከዚህ ቀደም ድሬደዋ ከተማ ነፋሻማ እንደነበረች እና የሙቀት መጠንዋ ከ34 እስከ 35 ዲግሪ ሴሊሺየስ የሚበልጥ እንዳልነበር ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን የአየሩ ሁኔታ ወበቃማ እና እስከ 40 ዲግሪ የሚደርስ ሙቀት እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ 

ስለዚህም በተለይ አረጋዊያን፣ ህፃናት፣ የልብ ህመም እንዲሁም ከመተንፈሻ አካላት ጋር ችግር ያለባቸው ሰዎች ጥንቃቄ ያደርጉ ዘንድ የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የማስጠንቀቂያ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ 

የድሬደዋ ነዋሪ ቶሎ ቶሎ እራሱን እንዲያቀዘቅዝ፣ ፈሳሽ አብዝቶ እንዲወስድ፣ በመኝታ ሰአት ከመከናነብ መቆጠብና ህፃናት እና አእምሮ ህሙማን ለብቻቸው እንዳይተዉ ሲል የጤና ቢሮው አሳስቧል፡፡ እንደ አስተዳደርም የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር አጠናክሮ መቀጠልና ህብረተሰቡም በየግዜው ዛፎችን የመትከልና የመንከባከብ ባህልን ማዳበር ይገባል ሲሉ የጤናው ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ተናግረዋል፡፡

በድሬደዋ አስተዳደር ዴልት ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት እና በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሮቤል ግዛቸው ሰሞኑን በድሬደዋ ያለው የሙቀት መጠን ከፍተኛ እደሆነ ይናገራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሮቤል ገለፃ ከመጠን ያለፈ ሙቀት ሲከሰት ሰውነታችን በተፈጥሮ የውስጡን ሙቀት ለመጠበቅ ይሞክራል፡፡ ነገር ግን የልብ ህመም፣ ስኳር እና ግፊትያለባቸው ሰዎች ህመማቸው እንዲባባስ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እድሜያቸው የገፋና ለጨቅላ ህፃናትም ያሰጋል፡፡

ዶ/ር ሮቤል ከፍተኛ የሙቀት መጠን በሚከሰትበት ወቅት በግለሰብ፣ እንደ መሀበረሰብም እንዲሁም እንደ አስተዳደር ማድረግ የሚገቡን ጥንቃቄዎች አሉ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ በግለሰብ ደረጃ አልኮል ያለማብዛት፣ ቡና ያለመጠጣት፣ ፈሳሽ በብዛት መውሰድ ሰውነትን ቶሎ ቶሎ ማቀዝቀዝ፣ ፕሮቲን የበዛበትን ምግብ የሙቀት መጠንን ስለሚጨምር ፕሮቲን አለመጠቀም ሙቀትን ለመከላከል ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 

በድሬደዋ ውስጥ የኮንስትራክሽን ባለሞያ ኢንጂነር ሔኖክ ካሱ ለሙቀት አካባቢ የሚሆኑ የቤት አሰራር አይነቶች እንዳሉ እና ድሬደዋ ውስጥም ያ ተግባራዊ ቢደረግ ጥሩ እንደሚሆን ተናግረዋል። በሞቃታማ አካበቢ ጣሪያቸው ከፍ ያለ እና የፀሀይ መውጫና መግቢያና መውጫን ታሳቢ ቢደረግ ጠቃሚ ነው። የቤቱ መግቢያ በፀሀይ ትይዩ ከሆነ ቀኑን ሙሉ ፀሀይ ይመታውና ለሊትም ሙቀትን ይፈጥራል ሲል ገልፀዋል።

የአገር አቀፉ አረንጓዴ አሻራ አስተባባሪ ኮሚቴ አባልና የፎረስተሪ ባለሙያ ዶ/ር አደፍርስ ወርቁ በአየር ጠባይ እና በዛፎች መካከል ያለው ትስስር ከፍተኛ እንደሆነ ተናግሯል። እንደ ዶክተር አደፍርስ ገለፃ ምንም ዛፍ የሌለበት አካባቢና የዛፎች ጥላ ያለበት አካባቢ በቴርሞ ሜትር ቢለካ ከ11⁰-20⁰ ዛፎች ያለበት ቦታ ይቀዘቅዛል። ዛፎች ጥላ ከመስጠት ባለፈ ከአፈር ውስጥ ውሀ ይመጡና በቅጠሎቻቸው ይተነፍሳሉ። ሲተነፍሱ የሚወጣው የውሀ ትናኞች ናቸው። ያ ትነት ውሀ ስለሆነ በራሱ አካባቢውን እንዲቀዘቅዝ ያደርገዋል። 

እንደ ዶክተር አደፍርስ ገለፃ በአለም አቀፍ ደረጃ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሙቀት መጠን እየጨመረ እንደሆነ ነው። ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት እንደ ካርቦንዳይኦክሳይድ ያሉ ሙቀት አማቂ ጋዞችን በህዋ ውስጥ እንዲጠራቀሙና ምድር እንድትሞቅ እያደረገ ነው። 

በዚህ ላይ የደን መመናመን የአለም ሙቀት እንዲከሰት ያደርጋል። ስለዚህ ሙቀትን ለመከላከል ዛፎች መተከል አለባቸው ሲሉ ገልፀዋል።

ዶክተር አደፍርስ እንደሚሉት " ከዛሬ 20 አመት በፊት ድሬዳዋ ውስጥ በሌሎች መንገዶች ላይ  መንቀሳቀስ የማይታሰብ ሲሆን በከዚራ ዛፎች ግን ምንም ፀሀይ ሳይነካን እንንሸራሸር ነበር።" በረሀ ውስጥ ዛፎች በመተከላቸው ምን ያህል አካባቢውን እንደሚያቀዘቅዙ ማሳያ የሆነች ከተማ ነበረች ሲሉም ትዝብታቸውን ተናግረዋል።

የከዚራ ዛፎች እንደ መፍትሄ

የኢቲዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡርን የገነቡት ፈረንሳዊያን መኖሪያ የነበረው ከዚራ በፕላኑና በመንገድ ዳር ዛፎቹ በየዘመኑ ብዙዎች አዚመውለታል፡፡ 

ያ ብዙ የተባለለት ከዚራ አሁንም ግርማ ሞገሱን ሙሉ በሙሉ አጥትዋል ባይባልም በእርጅና የተነቀሉና የደረቁ ዛፎች እንዲሁም ለኤሌትሪክ ደህንነትና ለሌሎች ጉዳዮች ምክንያት በሚቆረጡ ዛፎች የተነሳ በከዚራ ውስጥ መሄድ ሙሉ በሙሉ በጥላ ተከልሎ መሄድ መሆኑ እየቀረ ነው፡፡

በግለሰቦችና በፓርኮች እንደሚተከሉ ችግኞች ቋሚ ተንከባካቢ የሌላቸው የመንገድ ዳር ችግኞች እጣ ፈንታቸው ብዙ ጊዜ መነቀል፣ መቆረጥና መድረቅ ሲሆን መመልከት የተለመደ ነው፡፡

ከዚራ ተወልዶ ያደገው ዋለልኝ መኮንን ሁሉንም የከዚራ አካባቢ ባይሆንም ተወልዶ ያደገባትን መንገድ ዳር ወደ ቀድሞው ውበትዋ ለመመለስ ላለፉት 9 ዓመታት በግሉ ብዙ ጥረት ሲያደርግ ቆይትዋል፡፡ ‹‹በአያያዝ ችግርና በሚቆረጡ ዛፎች ምትክ ባለመትከል ምክንያት የከዚራ ዛፎች እየቀነሱ ስለመጡ በቁጭት ምንም አይነት የዛፍ መትከል እውቀት ሳይኖረኝ ነው የጀመርኩት፡፡ መጀመሪያ ዝም ብዬ አፀዳሁት ከዛ ያገኘሁትን ዛፎች እየተከልኩ በዛው አትክልተኛ ሆኜ ቀረሁ፡፡›› ሲል የከዚራን ዛፎች በምን መልኩ መንከባከብ እንደጀመረ ዋለልኝ ይናገራል፡፡

በተደጋጋሚ በጎርፍ ለምትጠቃውና ለሞቃታማዋ ድሬደዋ ዛፍ የህልውናዋ መሰርት ነው፡፡  እንደ ድሬደዋ ሞቃታማ የአየር ንብረት ያላቸው ሀገሮች ሞቃታማውን አየር ንብረት ከመቆጣጠር አንፃር ዛፎችን ይሻሉ፡፡ ድሬደዋ በመንገዶች ዛፍ ጥሩ ስም ነበራት፡፡  እውቅ የሀገራችን ሙዚቀኞች አዚመውላታል፡፡ አርቲስት ነዋይ ደበበ ከሐመልማል አባተ ጋር በዘፈነው ምርጥ ዜማ እንዲህ ማለቱ አይዘነጋም፡፡

                     “ከተፍ አለ ልቤ ደረሰልሽ

                   ከዚራ ጥላው ስር ተነጥፎልሽ”

 ድሬደዋ ካፈራቻቸው አንጋፋ ድምፃዊያን መካከል አንዱ አበራ ሙላቱ ባለጋሪው በተሰኘው ዘፈኑ፦   

                   “ጋሼ ባለጋሪ በጣም ብዙ ብረር

                 ፍቅርዬን ይዘሀት በከዚራው ጥላ ስር

                         በከዚራው ጥላ ስር”

አንጋፋው ገጣሚ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን “እሳት ወይ አበባ” በተሰኘው መድብላቸው ላይ እንዲህ ተቀኝተዋል፦

                      ድሬ ዳዋ ውስጠ ደማቅ

                   ሽፍንፍን እንደ አባድር ጨርቅ

                   ብልጭልጭ እንደ ሩቅ ምስራቅ

                       ያውራ ጎዳናሽ ዛፍ ጥላ

                      ጋርዶሽ ከንዳድሽ ብራቅ

 በድሬደዋ አስተዳደር  ለዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሀ ግብር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በፌደራል መንግስት ድጋፍ በመላው ሀገሪቱ ከተገነቡ ዘመናዊ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የድሬደዋው ይገኝበታል፡፡ ከ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን ዘመናዊ የችግኝ ማፍያ ጣቢያ  የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ እንደሚያግዘው ይታመናል፡፡

የድሬደዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር  ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የደንና የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ ተናግረዋል፡፡

የድሬደዋ አስተዳደር ግብርና ውሀ  ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢሊያስ አሊይ በበኩላቸው ችግኝ መትከልና ተንከባክቦ ማሳደግ ለድሬደዋ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ባለቤት የሌለው ችግኝ እንዳይተከል ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት በድሬደዋ ከተተከሉት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ በአማካይ 62 በመቶ መፅደቃቸውን ጠቁመዋል፡፡ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እስካሁን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

ሀገር በቀል የጥላና የፍራፍሬ ችግኞቹ በገጠርና በከተማ በሚገኙ 26 ችግኝ ጣቢያዎች በድሬደዋ ግብርና ቢሮና በባለስልጣኑ ቅንጅት እየተዘጋጀ መሆኑን የገለፁት በባለስልጣኑ የደን ልማት ቡድን መሪ አቶ ማሙሽ ዘውዴ ናቸው፡፡

አስተያየት