ግብርና እና ግብረ-ገብን ያካተተው አዲሱ ስርአተ ትምህርት የሙከራ ትግበራውን ጀመረ

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታጥቅምት 1 ፣ 2014
City: Addis Ababaዜናትምህርት
ግብርና እና ግብረ-ገብን ያካተተው አዲሱ ስርአተ ትምህርት የሙከራ ትግበራውን ጀመረ

ዛሬ በተጀመረው የ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን አዲሱ ስርአተ ትምህርት የሙከራ ትግበራውን እንደሚያከናውን ትምህርት ሚኒስቴር አሳውቋል። በአዲሱ ስርአተ ትምህርት ላይ የግብረ-ገብ፣ የግብርና፣ የጤና፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቶች ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ 12ኛ ባሉት ክፍሎች በየደረጃው ይሰጣሉ ተብሏል።

አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተማሪዎች ከቅድመ መደበኛ እስከ 6ኛ የግብረገብ ትምህርት ዓይነት እንዲወስዱ እና ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ የስነ-ዜጋ ትምህርት እንዲሰጥ ያስገድዳል።

ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ከ7ኛ ክፍል የሚጀምር ሲሆን በተጨማሪም የጤና እና የግብርና ትምህርት ዐይነቶችም ይካተታሉ ተብሏል።

12ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ ተማሪዎች በመለስተኛ ባለሙያነት በዲፕሎማ ተመርቀው ወደስራ እንዲገቡ እንዲያስችላቸው በማሰብ ከ11ኛ ክፍል ጀምሮ ከመደበኛ ትምህርቶች በተጨማሪ በመረጡት የትምህርት መስክ በተግባር የተደገፈ ስልጠና የሚያገኙበት ዕድል መመቻቸቱም ተገልጿል።

11ኛ እና 12ኛ ክፍል እንደከዚህ ቀደሙ የማኅበራዊ (ሶሻል) እና የተፈጠሮ (ናቹራል) ሳይንስ በሚል በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን፣ በስራቸው ከሚገኙት የቀድሞው መደበኛ ትምህርቶች በተጨማሪ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከሚቀርብላቸው ልዩ የትምህርት መስኮች መካከል የሚፈልጉትን መርጠው እንዲማሩ ይደረጋሉ። ተጨማሪ ትምህርቶቹም ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ጤና ሳይንስ እና ግብርና ሳይንስ ናቸው። 

የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የሚቀርብላቸው ተጨማሪ ልዩ የትምህርት መስክ ምርጫዎች ደግሞ ቋንቋ እና ማኅበራዊ ሳይንስ፣ ቢዝነስ እንዲሁም ስነ-ጥበባት ናቸው።

ትምህርት ሚኒስቴር የሁሉም አዳዲስ ትምህርቶች ሞጁል ተዘጋጅቶ ማጠናቀቁን የተገለጸ ሲሆን፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠነ 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቀ ተማሪ ለማፍራት ከተለያዩ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነትን ተፈራርሟል።

ይህ የኢትዮጵያ ትምህርት ስርዓት በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ8ኛ እና አስራ 12ኛ ክፍል ውጪ ለሚገኙት ክፍሎች በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በሙከራ የሚሰጥ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ለ11ኛ ክፍሎች ግን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ባሉ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።

የ8ኛ ክፍል እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ ተፈጻሚ የማይሆንበት ምክንያትም ለክልላዊ እና ብሄራዊ ፈተና የሚዘጋጁበት ዓመት ስለሆነ የተገለጸ ሲሆን በ2015 ሙሉ በሙሉ በመላው ሀገሪቱ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ከ200 በላይ ምሁራን እንደተሳተፉበት ተገልጿል።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist works at Addis Zeybe as a reporter while exploring her passion for storytelling and content creation.