ፌስቡክ የጥላቻ ንግግርንና ሌሎች እኩይ ይዘቶችን በቋንቋ ምክንያት መቆጣጠር ተስኖታል

Addis Zeybeጥቅምት 1 ፣ 2014
City: Addis Ababaዜና
ፌስቡክ የጥላቻ ንግግርንና ሌሎች እኩይ ይዘቶችን በቋንቋ ምክንያት መቆጣጠር ተስኖታል

የፌስቡክ አገልግሎት በመላው አለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ በመጣ ቁጥር አብረው በሚመጡት አዳዲስ የተጠቃሚ ቋንቋዎች ምክንያት የጥላቻ ንግግሮችንና ሌሎች እኩይ ይዘቶችን መቆጣጠር እንደተሳነው ሬውተርስ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ማወቅ እንደተቻለ ተገልጿል።

ፌስቡክ 2.3 ቢሊየን ለሚሆኑ ተጠቃሚዎቹ 111 በሚሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎቱን ማቅረብ የሚችል ቢሆንም ወደ 31 ለሚሆኑ በሰፊው በሚነገሩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ግን የፌስቡክ አገልግሎቶችን በራሳቸው ቋንቋ ማግኘት አንደማይችሉ ታውቋል። ተጠቃሚዎች የጥላቻ ንግግርን ጨምሮ አኩይ ይዘቶችን አንዳይለጥፉና እንዳያጋሩ የሚከለክለው የደንብ ዝርዝር (Community Standards) ከ 111 ዱ የፌስቡክ አገልግሎት ከሚቀርብባቸው ቋንቋዎች ተተርጉሞ የቀረበው  በ 41 ዱ ብቻ ነው።

ድርጅቱ እኩይ ይዘቶች በተጠቃሚዎች ዘንድ እንዲሁም በራሱ በድርጅቱ ህልውና ላይ ሊፈጥሩት የሚችሉትን ጥፋት በቀላሉ መከላከል እንዳይችል ይህ የቋንቋ እክል ሁኔታዎቹን አወሳስበውበታል።

የደንብ ዝርዝሮችን በተመለከተ የፌስቡክ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆነችው ሞኒካ ቤኬት እንደተናገረችው አገልግሎቱን በሁሉም ቋንቋዎች መተርጎም ለድርጅቱ ማንሳት የማይችሉት ከባድ ጭነት ሆኖበታል።

በሬውተርስ ዘገባ መሰረት ባለፈው አመት በማይናማር የተፈጠረውን የዘር ማፅዳት ዘመቻ ያጋጋለው በፌስቡክ የተሰራጨውን የጥላቻ ንግግር መቆጣጠር ያልተቻለው ይዘቱን መከላከያና መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን ለመተግበርና በሀገሪቱ ቋንቋ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ለማሰማራት በተፈጠረ መዘግየት ምክንያት ነበር።

ይህን በተመለከተ ፌስቡክ አገልግሎቱ የሚቀርብባቸው ቋንቋዎችን በማሻሻልና የበለጠ በማስፋት ከፍተኛ ጥረት እያደረኩ ነው ቢልም እንደ ሰብአዊ መብት ጥበቃ ባለሙያዎች አስተያየት አገልግሎቱን በአካባቢው ቋንቋዎች የማቅረብና የመቆጣጠር ጥረቱ ማህበራዊ ሚድያው ካለው ከፍተኛ ተፅዕኖ ጋር በሚስተካከል መልኩ ካልተተገበረ በማይናማር የደረሰው ጥፋት በሌሎች በግጭት በሚናጡ አካባቢዎች የማይደገምበት ምንም ምክንያት የለም።

በነዚህ አካባቢዎች ያሉ ተጠቃሚዎች በራሳቸው ቋንቋ ይዘቶችን እንዲለጥፉ ከተፈቀደ የአጠቃቀም ደንብና መመሪያዎቹም በራሳቸው ቋንቋ መቅረብ እንደሚኖርባቸው ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

የተለያዩ ግጭቶች በፌስቡክ እኩይ ይዘቶች እየተቀጣጠሉ ባሉባቸው ሀገራት አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያም የፌስቡክ አገልግሎት በአማርኛ ቢቀርብም የአጠቃቀም ደንብና ግዴታዎቹን ግን ተጠቃሚዎች ሊያነቡ የሚችሉት በእንግሊዝኛ ብቻ ነው።

ፌስቡክ አገልግሎቱን የሚያቀርብባቸውን ቋንቋቆች የሚናገሩ ቢያንስ 652 ሚሊየን ተጠቃሚዎች በአለም ዙሪያ ቢገኙም የአጠቃቀም ደንብና ግዴታዎች ግን በነዚህ ቋንቋዎች አልተተረጎሙም። ሌሎች ከ 230 ተጠቃሚዎች በላይ የሚሆኑት ደግሞ የፌስቡክ አገልግሎት በቋንቋቸው ከማይቀርብባቸው ቋንቋዎች የአንዱ ተናጋሪ ናቸው።

እኩይ ይዘቶች እንዳይሰራጩ እየተከላከልኩበት ነው በማለት ፌስቡክ የሚናገርለት  Machine Learning በሚባለው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ድጋፍ የተሰራው አውቶማቲክ ሶፍትዌር የጥላቻ ንግግርንና እኩይ ይዘቶችን ሊከላከል የሚችለው በ 30 ቋንቋዎች ብቻ እንደሆነ ድርጅቱ ይገልፃል። ይህን የቁጥጥር ዘዴን በተመለከተ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚሰሩት ጋይ ሮሰን ለሬውተርስ እንደተናገሩት በ Machine Learning ኮምፒዩተሮችን ለማሰልጠን እጅግ አያሌ ዳታ የሚያስፈልግ ሲሆን በአንድ ቋንቋ ውስጥ በአገልግሎቱ የተካተቱት ቃላት እጥረትና አነስተኝነት የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎቹንና ዘዴውን በፍጥነት ማሳደግ እንዳይቻል ዋነኛው ማነቆ ሆኗል።

እኩይ ይዘቶችን ለመቆጣጠር ባለው በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አሁንም ሁነኛ መፍትሄ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ተጠቃሚዎች በሚለጥፉትና በሚያጋሩት ይዘት ላይ ኃላፊነት እንዲሰማቸው ግንዛቤያቸውን መጨመር እንደሆነ ተጠቁሟል።