ጥቅምት 2 ፣ 2014

የችኩንጉኒያና ደንጊ ወረርሽኞች ስጋት ያንዣበባት ድሬዳዋ

City: Dire Dawaጤናማህበራዊ ጉዳዮች

በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት በስፋት ከተመዘገበባቸው ከተሞች አንዷ የሆነችው ድሬዳዋ ከሰሞኑ የደንጊ፣ የችኩንጉኒያና የወባ በሽታ ወረርሽኞች እንደተከሰቱባት ነዋሪዎቿም ተገቢውን ጥንቃቄ እየወሰዱ አለመሆኑ ይነገራል።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የችኩንጉኒያና ደንጊ ወረርሽኞች ስጋት ያንዣበባት ድሬዳዋ

ድሬደዋ ከተማ ውስጥ ልዩ ስሙ ጎሮ በተባለ ሰፈር ነዋሪ የሆነችው ወ/ሮ ሮማን ንጉሴ የደንጊና ችኩንጉኒያ በሽታ ወረርሽኝ እንደተከሰተ በዜና መስማቷን ትናገራለች። 

በአካባቢያቸው ዝናብ በሚመጣ ወቅት ውሀ የሚያቁር ጉድጓድ በመኖሩና ቦታው ለደንጊ እና ለችኩንጉኒያ በሽታ አምጭ ለሆኑ ተህዋሲያን መራቢያ ምቹ በመሆኑ በሰፈራቸው የበሽታው መዛመት እንደሚያሰጋት ስጋቷን ትገልፃለች።

"የሰፈራችን ነዋሪዎች ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ ያላቸው አይመስለኝም፤ ወረርሽኙን ለመካከል ማንም ጥረት ሲያደርግ አላየሁም" ትላለች ሮማን።  

በተመሳሳይ ወ/ሮ መብራት ጉልላት የተባለች የድሬደዋ ነዋሪ የዛሬ ሳምንት በኮቪድ 19 በሽታ እናቷን በሞት እንደተነጠቀች ትናገራለች። እናቱዋ ከመሞታቸው በፊት በድል ጮራ ሆስፒታል ውስጥ ህከምናቸውን እየተከታተሉ የነበረ ቢሆንም ምንም አይነት ጥንቃቄ ሲደረግ እንዳላየች ትናገራለች። እናቷን ስታስታምም መቆየትዋን ገልፃ ብዙ ሰው ሊጠይቃት ይመጣ እንደነበርም ትገልፃለች። 

"ስናስታምማት የነበረውም ከወንድሞቼ ጋር እየተቀያየርን ነበር" የምትለው ወ/ሮ መብራት "ስለበሽታ በቂ ግንዛቤ ያላቸው የህክምና ባለሞያዎቹ ሳይጠነቀቁ እንዴት ማህበረሰቡ ይጠነቀቃል" ስትልም አስተያየቱዋን ገልፃለች።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮቪድ 19 በሽታ ወረርሽኝ ስርጭት በስፋት ከተመዘገበባቸው ከተሞች አንዷ የሆነችው ድሬዳዋ ከሰሞኑ የደንጊ፣ የችኩንጉኒያና የወባ በሽታ ወረርሽኞች ስጋት እንዳንዣበቡባት የከተማዋ የጤና ቢሮ ነዋሪዎች የወረርሽኙን መዛመት ለመግታት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማሳሰብ ላይ ይገኛል።

የደንጊ ትኩሳት ወረርሽኝ በየዓመቱ ዝናብን ተከትሎ የሚከሰት ተላላፊ በሽታ ነው። በያዝነው አመትም 87 ናሙና ወደህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ተልኮ 4 ሰዎች በደንጊ ትኩሳት በሽታ መያዛቸውን የሚያረጋግጥ የምርመራ ውጤት መገኘቱን የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረዋል።

እንደ ወ/ሮ ለምለም ገለፃ ደንጊ በፍጥነት ከሰው ወደሰው የሚተላለፍና እስከሞት የሚያደርስ በሽታ እንደሆነ ተናግረዋል። ኃላፊዋ በአንድ ከተማ ውስጥ በደንጊ በሽታ አንድ ሰው ቢያዝ እራሱ ወረርሽኝ የሚባል እንደሆነ ገልፀዋል። 

የቺኩንጉኒያም ሆነ የደንጊና የወባ በሽታዎች በቀላሉ ከታማሚው ወደ ጤነኛው ሰው በትንኝ ንክሻ አማካኝነት የሚተላለፉ በሽታዎች ናቸው። የችኩንጉኒያና የደንጊ በሽታ ተቀራራቢ ምልክቶችን የሚያሳዩ ሲሆን የቺኩንጉኒያ በሽታ ምልክቶች ልክ እንደ ደንጊ በሽታ ከፍተኛ ትኩሳትና ራስ ምታት ብርድ ብርድ ማለት የመገጣጠሚያ ቁርጥማትና ህመም እንዲሁም የምግብ ፍላጎት ማጣት ሲሆኑ ከደንጊ ትኩሳት በሽታ በበለጠ የመገጣጠሚያ ቦታዎች ህመም ስሜትን ያስከትላል። 

እነዚህና የመሳሰሉ ምልክቶችን ሲያሳዩ ህመሞት ቺኩንጉኒያ የደንጊ ትኩሳት ወይም የወባ በሽታ ሊሆን ስለሚችል በፍጥነት በአካባቢዎ ወዳለው ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራና ህክምና ማድረግ  እንደሚገባ የጤና ባለሞያዎች ይናገራሉ። 

ወ/ሮ አረጋሽ ሙላቱ የተባለች የድሬደዋ ነዋሪ የደንጊ እና የኮቪድ ወረርሽኝ እንደተከሰተ መስማቷን ገልፃ ነገር ግን በጤና ተቋማት ላይ ክፍተት እንዳለ ገልፃለች። ወ/ሮ አረጋሽ ‹‹ የተለያዩ የህመም ስሜቶች ስለነበረብኝ ሳቢያን ጤና ጣቢያ ለመመርመር ሄጄ ነበር ነገር ግን ተደግፎ ወይም በአንቡላንስ የመጣ ሰው ካልሆነ ምርመራ አናደርግም ብለው እንዳንገላቷት ነግራናለች። ወረርሽኙን ልናልፈው የምንችለው የጤና ባለሞያው ሀላፊነቱን ሲወጣ ነው ስትልም ተናግራለች።

በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱዩት መረጃና የመረጃ አስተዳደር ባለሞያ አቶ አለምነህ በድሬደዋ ከተማ ውስጥ ስለሚገኘው ወቅታዊ ሁኔታ ሲገልፁ በድሬደዋ ከተማ ውስጥ መስከረም ከገባ ጀምሮ ደንጊና ችኩንጉኒያ እንዲሁም ሶስተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ዴልታ ቫርያንት ብዙ ሰዎችን እያጠቃ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። መስከረም ከገባ 1092 ሰዎች በኮረና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች እንደተያዙ የተናገሩት አቶ አለምነህ 14 የሚሆኑትም በዚሁ በሽታ ህይወታቸው እንዳለፈ ይገልፃሉ።

ከኮቪድ በሽታ ጋር በተያያዘ የድሬደዋ የጤና ሚኒስተር ባወጣው መረጃ መሰረት በተለይ የዴልታ ቫርያንት ብዙ ሰዎች እያሳጣ እንዳለና የህክምና ባለሞያዎችንም ዋጋ እያስከፈለ ከመሆኑ ባሻገር ህብረተሰቡንም እየጎዳ በመሆኑ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ቢወስዱ ይመከራል። በተለይ ከቀን ወደቀን የኮቪድ ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ተከትሎ ቤታቸው እንዲቀመጡ ያደረግናቸው ታማሚዎች በቸልተኝነት ከህብረተሰቡ ጋር እየተቀላቀሉና ትክክለኛ አድራሻቸውንም ያለመናገር ሁኔታዎች በመኖራቸው የኮቪድን ስርጭት እያስፋፋው ሲሆን ህብረተሰቡና ተቋማት የወረርሽኝን መስፋፋትና የበሽታውን ከባድነት ግምት ውስጥ አስገብተው የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባቸው ገልፀዋል።

በድሬደዋ ከተማ ውስጥ የደንጊ ትኩሳት በሽታ ወረርሽኝ መከሰቱ ተገልጿል። በአሁኑ ሰአት የችኩንጉኒያ ምልክቶችም እየታዩ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል።

አስተያየት