የእስራኤል መንግስት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራኤላዉያንን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን እና ወደ እስራኤል መመለሱን አስታወቀ። የሀገሪቱ የኢሚግሬሽን ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በዚህ ዓመት በትግራይ ክልል የሚገኙ በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራኤላውያን ቢኖሩም ወደ እስራኤል መመለስ የተቻለው ጥቂቶቹን ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ5 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላውያን ወደ ሀገሪቱ መግባታቸውም ተገልጿል።
የኢሚግሬሽን ሚኒስትሯ ትውልደ ኢትዮጵያዊዋ ታማኖ ሻታ እንደሚገልፁት አሁንም ቤተ እስራኤላዊ መሆናቸው ስለሚወሰንበት መንገድ አለመግባባቶች በመኖራቸው የቀሩት ቤተ እስራኤላውያን ቁጥርን በአግባቡ ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል። እስካሁን በተለየው መሰረትም ወደ እስራኤል ያልተመለሱ እስከ 2 ሺህ የሚደርሱ ቤተ እስራኤላውያን በኢትዮጵያ እንደሚገኙ የኢሚግሬሽን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
እስራኤል በጠቅላላው በዚህ አመት 60 ሺህ ስደተኞችን እና ቤተ እስራኤላዉያንን ወደ ሀገሪቱ መመለሷን ያስታወቀች ሲሆን ቴል አቪቭ፣ ሀይፋ፣ ኔታንያ እና እየሩሳሌም ከተማዎች ከፍተኛ ከፍተኛ ተጓዦችን በማስተናገድ ተጠምደው የነበሩ ዋነኛ የእስራኤል ከተሞች ናቸው። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የእስራኤል መንግስት ወደ ሀገር ፈቅዶ ያስገባቸው ተጓዦች ቁጥር ከቀደመው አንድ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ128 እጥፍ የሚበልጥ መሆኑን የሀገሪቱን ባለስልጣናት ዋቢ አድርገው 'ዘ ጄሩሳሌም ፖስት' እና ሌሎችም የዜና ምንጮች ዘግበዋል።
የእስራኤል መንግስት ወደ ሀገራቸው ከመለሳቸው ዜጎች በርካቶቹ የሰላም እጦት ካለባቸው ሀገራት ሲሆን ከነዚህም ኢትዮጵያ፣ ሩስያ፣ ዩክሬን እና ፈረንሳይ በርካታ ስደተኞች እና ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል ከተመለሱባቸው ሃገራት ቀዳሚዎቹ ናቸው። በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ እስራኤል ከተመለሱት ስደተኞች ውስጥ 47 በመቶ ከሩስያ፣ 25 በመቶ ከዩክሬን፣ 6 በመቶ ከአሜሪካ፣ 4 በመቶ ከፈረንሳይ እና 2 በመቶ የሚሆኑት ከኢትዮጵያ ናቸው።
የእስራኤል የኢሚግሬሽን ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በተለይም ከሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት በኋላ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ይጎዳሉ ተብሎ ከታሰቡ ሀገራት ቤተ እስራኤላዉያንን ለመመለስ ጥረት መደረጉ ቁጥሩ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። ሚኒስትሩ እንዳስታወቀው 60 ሺህ ቤተ እስራኤላዉያንን ለመመለስ በመላው ዓለም የሚገኙ የእስራኤል ተወላጆች እስከ 100 ሚልየን ዶላር አሰባስበዋል።
የእስራኤል መንግስት በኢትዮጵያ ሁለት ዓመቱ እየተቃረበ ካለው ጦርነት እንዲሁም ቤተ እስራኤላዉያን ያልሆኑ ግለሰቦች ተቀላቅለው በመግባታቸው ሰበብ በርካቶቹ አሁን ላይ ቢነሱም በተለያዩ ጊዜያት ኃይማኖታዊ ተጓዦችን ጨምሮ ከኢትዮጵያ የሚነሱ ጉዞዎችን አግዳ ነበር።
በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. የእስራኤል ካቢኔ አባል እና የኢሚግሬሽን ሚኒስትሯ ታማኖ ሻታ በወቅቱ በተካሄደ የካቢኔ ውይይት ላይ ስድተኞችን በተመለከተ የዘር መድልዎን ጉዳይ ያነሳች ሲሆን ከዩክሬንና ከኢትዮጵያ ለመጡት ስደተኞች በእስራኤል በተደረገው አቀባበል ላይ የታየውን የዘር መድልዎ በተመለከተ ባልደረባ የካቢኔ አባላቱን “አስመሳዮች” በማለት በግልፅ መተቸቷም ይታወሳል።