መስከረም 5 ፣ 2015

ጠጅ እና ጎንደር- ከአበቄለሽ እስከ አትጠገብ እልፍኝ

City: Gonderባህል የአኗኗር ዘይቤ

በአትጠገብ እልፍኝ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች መግባት አይችሉም፣ የጦር መሳሪያ ይዞ መግባት አይቻልም፣ ዘመናዊ መጠጫ ወይም መመገቢያ ወደ ቤቱ አይገባም

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ጠጅ እና ጎንደር- ከአበቄለሽ እስከ አትጠገብ እልፍኝ
Camera Icon

ፎቶ፡ ትራቭል ማኒያ

በጎንደር ከተማ ከጃንተከል ዋርካ 120 ሜትር ገደማ ዝቅ ብሎ ይገኛል፣ አበቄለሽ ጠጅ ቤት። ከተከፈተ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ያስቆጠረው ይህ ዝነኛ ጠጅ ቤት አሁን አሁን በሌሎች መጠጥ ቤቶች እየተዋጠ ቢሆንም ሰርክ ክፍት በመሆን ታማኝ ደንበኞቹን ያስተናግዳል። 

አበቅየለሽ ጠጅ ቤት ስያሜውን ያገኘው ከመስራቿ ወ/ሮ አበቅየለሽ ይመር ነው፤ ወ/ሮ አበቅየለሽ በአብዛኛው የጎንደር ነዋሪ ዘንድ እማዋይ አበቅየለሽ ተብለው ይጠሩ ነበር።  

ወ/ሮ አበቄለሽ ማን ናቸው?

በ1912 ዓ.ም በጭልጋ የተወለዱት አበቅየለሽ ከወጣትነታቸው ጀምሮ የተዋጣላቸው የማር ጠጅ ጣይ እንደነበሩ ይነገራል። በሞያቸው ላይ መልካም መስተንግዷቸው ተጨምሮ በ1934 ዓ.ም በጃንተከል አቅራቢያ የከፈቱት ጠጅ ቤት ዘመናትን የተሻገረ ታዋቂነትን አትርፎላቸዋል። 

በጀመሩት የጥሩ ማር ጠጅ ጣይነት በማህበረሰቡ ዘንድ ተወዳጅነት አትርፈው በጎንደር ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ነዋሪ ህብረተሰብ ዘንድ ከመታወቅ አልፈው በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም ስማቸውና ዝናቸው ታውቆ በኪነት ሰዎችም ዘንድ ጎንደር አበቄለሽ እየተባለ የተገጠመላቸው እና የተነገርላቸው እናት ናቸው።

በእማዋይ አበቄለሽ ጠጅ ቤት በከተማዋ ረጅም ርቀት የሚያሽከረክሩ ሹፌሮች፣ ጠጅ ያማራቸው ሰዎች፣ እንግዶች እንዲሁም አዝማሪዎች ይውሉና ያመሹ እንደነበር ይነገራል። ይህ ከ60 አመታት በላይ ያስቆጠረ ጠጅ ቤት በዚያን ጊዜ ታዋቂና ብቸኛው ጠጅ ቤት ነበር። 

አበቄለሽ ጠጅ ቤት አሁን ላይ ከዛ ሁሉ ሰው ጋጋታ ታቅቦ፣ ቤቱ ብቻውን ቆሞ “አጫዋቾቼ የታሉ? ወዴት ሄዱ?” የሚል ይመስላል። ወ/ሮ አበቄለሽ መጋቢት 16 ቀን 1994 ዓ.ም ካረፉ በኋላ ጠጅ ቤቱ እየተቀዛቀዘ መጣ።  የአዲስ ዘይቤ ባልደረባ ነሃሴ 2014 ዓ.ም ጠጅ ቤቱን ለመጎብኘት በሄደበት ጊዜ ባለቤት አልባ ይመስላል። 

አቶ ዘለቀ ተገኘ የእማዋይ አበቄለሽ የእህት የልጅ ልጅ ነው። ጠጅ ቤቱ በጎንደር ከተማ ብቸኛው እና በቱሪስቶችም ዘንድ ታዋቂ የነበረ መሆኑን ገልፆልናል። 

“ከ1990ዎቹ በፊት እንዳሁኑ የኑሮ ውድነት ሳይገዝፍ አንድ ጠርሙስ የአበቄለሽ ጠጅ 3 ብር የነበረ ሲሆን በብርሌ ደግሞ 1 ብር ከ 50 ሳንቲም እንዲሁም አፈድስት ተብላ በምትጠራው መጠነኛ የጠጅ መጠጫ 1 ብር ይሸጥ ነበር” በማለት ትውስታውን አካፍሎናል። 

በ2014 ዓ.ም አንድ ጠርሙስ የአበቄለሽ ጠጅ 200 ብር ሲሆን ብርሌ ተብሎ በሚጠራው የጠጅ መጠጫ 100 ብር እንዲሁም ትንሽ መጠን ባላት አፈድስት እየተባለች በምትጠራው የጠጅ መጠጫ 50 ብር ይሸጥ እንደነበር ዘለቀ ነግሮናል።  

“ለጠጅ የሚሆን ማር ጎንደር አካባቢ የት ይገኛል?” ለሚለው ጥያቄ አቶ ዘለቀ በሰጠው ምላሽ የማር ምርት በብዛት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች ሰሜን ጎንደር ዞን ተጠቃሽ ሲሆን ከአዳርቃይ፣ ማይፀብሪ፣ ሮቢት፣ ጭልጋ ከሚባሉ አካባቢዎች በነጋዴዎች አማካኝነት ማር እያስመጡ እንደሚጠቀሙ ነግሮናል። 

ነሃሴ 2014 ዓ.ም ገበያ ላይ ያለው የማር ዋጋ እንደየጥራቱ የሚለያይ ቢሆንም  አንድ ኪሎ ማር ከ 180 እስከ 300 ብር የገባ ሲሆን አንዳንድ ነጋዴዎች ከማሩ ላይ ስኳር እየቀላቀሉ እንደሚሸጡ የነገረን ደግሞ ከ1987 እስከ 2007 ዓ.ም ለተከታታይ 20 አመታት የአበቄለሽ ጠጅ ቤት ደንበኛ የነበረው የጎንደር ከተማ ነዋሪ አቶ ቴዎድሮስ አስፋው ነው። 

አንድ ጠጅ ቤት የማር ምርት ብቻ የሚያመጡ ነጋዴዎችን በቋሚነት ደንበኛ አድርጎ ካልያዘ ከማሩ ላይ ያልተገባ ነገር እየጨመሩ በሚሸጡ ህገወጥ ነጋዴዎች እንደሚታለሉ አቶ ቴዎድሮስ ይናገራል። 

ሁሉንም የማር ምርት አቅራቢዎች በጀምላ መኮነን ባይቻልም አንዳንዶቹ ንፁህ ማር ይዘው አይንቀሳቀሱም። ስኳር፣ ሙዝ እና የተለያዩ ነገሮች ከማሩ ጋር ሲቀላቀሉ በቀላሉ ሊለዩ የማይችሉ ነገሮችን ጨምረው የሚሸጡ በመኖራቸው በየመንገዱ የማር ምርት ይዘው የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን ለመግዛት እንደሚቸገሩ እና ተዓማኒነት እንደሚያጡ ጠቁመውናል። 

አቶ ቴዎድሮስ የጠጅ ደንበኛ በነበረባቸው ጊዜያት ጎንደር ከተማ ውስጥ የሚታወቀው አበቄለሽ ጠጅ ቤት ብቻ ስለነበር ቤቱ በሰዎች ተሞልቶ ይውላል። “እማዋይ አበቄለሽም ጠጇን በዛ አድርጋ ስለምትጠምቀው ቶሎ የሚያልቅ አልነበረም።  እየተጠጣ ያለው እስኪያልቅ ሌላ በጎን ያዘጋጁ ነበር ፣ ሳምንቱን ሙሉ ጠጅ ከቤታቸው አይጠፋም ነበር” ይላሉ አቶ ቴዎድሮስ። 

“ጎንደር ከተማ ካለው አበቄለሽ ጠጅ ቤት ወጣ ብለን ከከተማዋ ውጭ ጠጅ ለመጠጣት በሄድንበት ወቅት ስኳር የተቀላቀለበት ጠጅ ጠጥተን የጠጅ ፍላጎታችን ቀንሶ ቀርቷል” ያሉን ደግሞ አቶ ፍርድይወቅ አምባው ናቸው። 

ጠጅስ ባሳየንሽ ከነአበቄለሽ፣

ምነው አንቺስ ደግሞ በስኳር ጠመቅሽ።

በማለት ባለቤቷን በነገር ሸንቆጥ አድርገዋቸው እንደነበር በፈገግታ አጫውተውናል። 

ወ/ሮ ሮማን ሙሃመድ በአበቄለሽ ጠጅ ቤት አጠገብ ይኖራሉ። እንደ እሳቸው ገለፃ ወደ አበቄለሽ ጠጅ ቤት የማይመጣ እንግዳ እና የከተማዋ ነዋሪ አልነበረም። ቤቱ 24 ሰዓት ድምቅ እንዳለ በሰው ተሞልቶ ይውል እንደነበር ይናገራሉ። በ2014 ዓ.ም ጠጅ ቤቱ ለሌላ ሰው ተሽጦ ሊታደስ እና በአዲስ መልክ ሊስፋፋ እንደሆነ መስማታቸውን ጠቁመውናል።  

የአበቄለሽ ምትክ፡ አትጠገብ እልፍኝ

በጎንደር ከተማ የአበቄለሽን ጠጅ ቤት በከተማዋ ነዋሪ እንዲሁም በቱሪስቶች ታዋቂ እና አዋጭ እንዲሁም በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ መሆኑን ተከትሎ በከተማው ከ50 በላይ ጠጅ ቤቶች የተከፈቱ ሲሆን ከእነዚህ ጠጅ ቤቶች ታዋቂነትንና በቱሪስቶች እንዲሁም በአካባቢው ማህበረሰብ ተወዳጅነትን ያገኘው እንዲሁም በባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች የሚታወቀው አትጠገብ እልፍኝ ጠጅ ቤት አንዱ ነው። ይህ መሃል ጎንደር የሚገኝ ቤት በባህላዊ ቁሳቁሶች ብቻ የተጌጠ ለየት ያለ የመዝናኛ ስፍራ ነው። 

በዚህ ቤት ውስጥ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የመጠጫ እና የመመገቢያ ቁሳቁሶችን እንደጌጣጌጥ ያካተተ ነው። ወስከንቢያ፣ ቀለምሻሽ፣ ጥራር እንዲሁም ሰበጥራ በግድግዳው ተንጠልጥሎ ይታያሉ። ቅል፣ አጎዛ፣ ከከብት የተሰሩ ቀንዶች፣ በብራና የተፃፉ ግዕዝና አማርኛ ፅሁፎች፣ በጣራ እና ምሰሶው ላይ የተንጠለጠሉ ደረቅ የገብስ እሸቶች እንዲሁም የባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች ምስሎች ይገኛሉ። 

በአትጠገብ እልፍኝ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች መግባት አይችሉም፣ የጦር መሳሪያ ይዞ መግባት አይቻልም፣ ዘመናዊ መጠጫ ወይም መመገቢያ ወደ ቤቱ አይገባም። በአትጠገብ እልፍኝ ቤት የመመገቢያ እና መጠጫ እቃዎቹ በሙሉ ባህላዊ ናቸው።

አቶ ታደሰ እያያ እና ወ/ሮ እሌኒ እንየው የአትጠገብ እልፍኝ ባለቤቶች ናቸው። ሁለቱም የተወለዱት ጎንደር ከተማ ቀበሌ 13 አካባቢ ነው። አትጠገብ እልፍኝን መክፈት ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚያስቡት ህልማቸው እንደነበር ይናገራሉ። በኋላ አድገው በትዳር ከተሳሰሩ በኋላ ህልማቸውን እውን አድርገውታል። 

ወ/ሮ እሌኒ እንደነገረችን ልጅ እያለች በተማሪነቷ ባህላዊ እቃዎችን ትሰበስብ ነበር። እየዞረች ሞያ ትማር ነበር። ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ሆቴል ምግብ ዝግጅት ተማረች። ተቀጥራ የተለያየ ቦታ እየሰራች የተለያዩ የውጭ ሃገር ቱሪሥቶች “ዘመናዊ ምግብ ባለንበት ቦታ አለ፣ ባህላዊ ምግብ የት ነው ያለው?” እያሉ ይጠይቋቸው እንደነበር ታስታውሳለች። የቱሪስቶቹ ጥያቄና ፍላጎት ወደ እዚህ ስራ ለመቀላቀል መንገድ እንደከፈተላቸው ትናገራለች።  

እንግዶች በአትጠገብ እልፍኝ በባህላዊ ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም በአዝማሪዎች ግጥም እየተዝናኑ ቀናቸውን አሳምረው ይውላሉ። በአትጠገብ እልፍኝ መቀመጫው ጠፍር ወንበር፣ የሚነጠፈውም አጎዛ፣ መመገቢያዎችም ቀለምሻሽ (ከሰበዝ የተሰራ የምግብ መመገቢያ) ነው። እንግዶች በቆሎ እና በበቆልት በአዋዜ እያዋዙ፣ ገበጣ እየተጫወቱ ጠጅ እና ጠላቸውን ይጎነጫሉ። 

በዚህ ጠጅ ቤት ኮረፌ እና ቀይ ጠላ የሚጠጣው ከቅል በተዘጋጀ አንኮለል ተብሎ የሚጠራ መጠጫ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከከብት ወይም ከጎሽ ቀንድ የተሰራ ዋንጫ ለመጠጫነት ይገለገሉበታል። 

አልኮል ለማይጠጡ እንግዶች ሱፍ ጭልቃ ፣ብርዝ እና ተልባ ጭልቃ ይቀርብላቸዋል። የሱፍ ጭልቃ የተባለው መጠጥ የሚዘጋጀው ከሱፍ እና ማር ሲሆን ሱፉን በመውቀጥ ታሽቶ በማር ተደርጎ በተለይ በፆም ወቅት የሚጠጣ ነው። ተልባ ጭልቃ እንዲሁ ተልባን ከማር ቀላቅሎ የሚዘጋጅ ሲሆን በተለይ ለአራስ ሴቶች የሚዘጋጅ ነው። ለሆዳቸው መድሃኒት ነው በሚል አራስ ሴቶች ይጠቀሙታል።    

ብርዝ ጠጅ አልኮል ለማይጠጡ እንግዶች ከንፁህ ማር የተዘጋጀ ሲሆን፣ አውዛ የሚባለው ደግሞ ጌሾ ለማይጠጡ ሰዎች የሚዘጋጅ ጌሾ አልባ ጠጅ ነው። የእነዚህ የጠጅ አይነት ስሞች ከድሮ ጀምሮ በማህበረሰቡ ዘንድ ተለምደው የተወረሱ ናቸው የምትለዋ ወ/ሮ እሌኒ እንየው ባህሉን እንደጠበቀ እንዲቆይና ስያሜያቸውም እንዳይጠፋ በሚል እንጠቀማቸዋለን ትላለች።   

አቶ ታደሰ እያያ በበኩላቸው አትጠገብ እልፍኝ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሰባት አመታትን ማስቆጠሩንና ከ20 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን ነግሮናል። ራዕያቸው ኢትዮጵያን ጎንደር ላይ ማስቀመጥ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ታደሰ እያያ የኢትዮጵያን የተለያዩ ቦታዎች ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም መገልገያ እቃዎች በአንድ ቦታ ለማግኘት ለሚፈልግ ሰው አትጠገብ እልፍኝ ትክክለኛ ቦታ ነው ይላሉ። 

ጎንደሮች ባለሞያ ናቸው ይባላል በተለምዶ። ከሚወደሱባቸው የሞያ ትሩፋቶቻቸው አንዱ ደግሞ ጠጅ ነው። ጠጅ እንደየደረጃው ለስለስ ያለ፣ መካከለኛና ደረቅ ተብሎ የሚለይ ሲሆን በውሃ የተበረዘውን ማር ከጌሾ ጋር ቀላቅሎ እንደየዝግጅታቸው የጊዜ ሰሌዳ ወይም እንደሚፈለገው ልስላሴ ወይም ደረቅነት በመጀመሪያ በርሜል ለተወሰኑ ቀናት ከቆየ በኋላ በወይራ በጌሾ ወደታጠነ በርሜል ይገለበጣል። 

የጠጁ ቀለም ቢጫ እንዲሆንላቸው አንዳንዶቹ እርድ ሲጠቀሙ አንዳንዶቹ ደግሞ ስኳርን አመስ አመስ በማድረግ ይጠቀማሉ። የጌሾ እንጨቱን በብረት ምጣድ በማመስ የጠጁን ጣዕምና ጥንካሬ እንዲሁም ተፈላጊውን ቀለም እንዲያመጣ የሚያደርጉም አሉ። ጠጅ ከሌሎች ባሕላዊ መጠጦች በተለየ መልኩ በሂደቱ ልዩ ጥንቃቄን ይፈልጋል። ጠጅ በተጣለበት ቤት አጠገቡ እጣን ወይም ሰንደል ማጨስ ወይም ወደቤቱ ሽቶ ተቀብቶ መግባት ልፋታቸውን ከንቱ ሊያደርገው እንደሚችል ባለሞያዎቹ ይናገራሉ።  

ይህ ባህላዊ መጠጥ በዓላትን ከማድመቅ በዘለለ ወደ ፋብሪካ ገብቶ ዳጎስ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ወደሚያመጣበት ደረጃ አለመድረሱ እንደሚቆጫቸው በሙያው የተሰማሩ ሰዎች ይናገራሉ።  

በጎንደር ከተማ አግኝተን ያነጋገርናቸው የውጭ ሃገር እንዲሁም የሃገር ውስጥ ቱሪስቶች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ጎንደር ላይ ባህላዊ ነገሮችን ፈልገው እንደሚመጡ ገልፀው አትጠገብ እልፍኝ ሁሉንም የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦችንና መጠጦችን አጠቃሎ ይዞ እንደሚያገኙት እና ተዝናንተው እንደሚሄዱ ነግረውናል። 

አስተያየት