መስከረም 5 ፣ 2015

ከትውስታ የማይጠፋው የወሎ ጭስ

City: Dessieባህል የአኗኗር ዘይቤ

የወይባ ጭስ በወሊድ ውቅት ማህፀን አካባቢ የሚፈጠር ቁስለት ቶሎ እንዲደርቅና እንዲድን ከማድረጉ ባሻገር ለመልካም ጠረንና ለሰውነት ጥራት እንደሚጠቅም በማህበረሰቡ ይታመናል

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከትውስታ የማይጠፋው የወሎ ጭስ
Camera Icon

የወይባ ጭስ በወሊድ ውቅት ማህፀን አካባቢ የሚፈጠር ቁስለት ቶሎ እንዲደርቅና እንዲድን ከማድረጉ ባሻገር ለመልካም ጠረንና ለሰውነት ጥራት እንደሚጠቅም በማህበረሰቡ ይታመናል

“ራያ ነሽ የጁ ባቲ ነሽ ከሚሴ፣  ጠረንሽ የሚለው አሽኩቲና ከሴ” በማለት ገጣሚው ቆንጆዋን ሲያወድስ በራያ፣ በየጁ፣ በባቲ እና ከሚሴ ከሚገኙት የወሎ ጭስ ጠረን እና ውብ መዓዛ ጋር ያመሳስላታል።

“ዘመድ ጎረቤት ተሰባስቦ ቡና ተፈልቶ ሲጠጣ በወሎ ጭስ ልዩ መዓዛ ካልታጀበ ቡና መጠጣትህ ስለማያስደስትህ ጭሱ ቤትህ ውስጥ መኖሩ እንደ ውዴታ ግዴታ ይሆንብሃል" ይላሉ የደሴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ የሺወርቅ ማስረሻ የዕጣን ጭስ ለማህበራዊ ስርዓቱ የሚሰጠውን ድምቀት ሲያስረዱ።

የወሎ ጭስ ለመልካም መዓዛ ከማገልገሉም በላይ ለጤና ተስማሚና የተለያዩ በሽታዎችን ሊፈውስ እንደሚችል በአካባቢው ነዋሪዎች ይታመንበታል። የወሎ ጭስ ለቁርጥማት፣ ቁስልን ለማድረቅ፣ ለፊት ጥራትና ለእናቶች ከወሊድ በኋላ ጥቅም ላይ ይውላል። 

ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ ሲጓዙ ደሴ መዳረሻ ላይ የሀረጎን ጠመዝማዛ መንገድ ተጉዘው የንጉስ ሚካኤል ቤተመንግስትንና የአይጠየፍ አዳራሽን ሽቅብ እያዩ አራዳ ገበያ ሲደርሱ መንፈስን የሚያድስና ጠረኑ የሚያውድ መዓዛ ባሸተቱ ጊዜ በእርግጥም በጦሳና አዝዋ ተራሮች ከተከበበችው የወሎ መዲና ውቧ ደሴ ከተማ ደርሰዋል።

እግር ጥሎት የወሎን ምድር በመስከረም ወር የረገጠ ሰው አራዳ ገበያ አካባቢ የመንገዱ ግራና ቀኝ በውብ ቀለማት አሸብርቆ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት የተሰደሩ የወሎ ጭስ ግብአቶች ለደንበኛ ቀርበው መመልከቱ አይቀሬ ነው።

የኢትዮጵያዊ ብዝሃነት ምልክት፣ የነላስታ ላሊበላ የጥንት ስልጣኔ ምድር፣ ከአንድ ዐለት ተፈልፍለው የታነፁ ድንቅ ቤተመቅደሶችን የያዘች፣ የአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች- የአንቺሆዬ፣ ትዝታ፣ ባቲና አምባሰል መፍለቂያ፣ የታላቁ ደብር የግሸን ደበረከርቤ ገዳም መገኛ፣ የአያሌ ባህልና እሴቶች መኖሪያ፣ የታላላቅ የኃይማኖት አባቶች የእነ ሼኽ ሁሴን ጂብሪል ሀገር፣ የቆነጃጅቶችና የጎበዛዝቶች መናኸሪያ ናት ወሎ ላኮመልዛ።

በክረምቱ ዝናብ የራሰው መሬት በመስከረም ያብባል። አረንጓዴው መስክ በተለያዩ ተክሎች አምሮና ደምቆ የተፈጥሮን ውበት ያለ ስስት አጉልቶ ያወጣል። ያኔ በብዛት ከሚገኙት ተክሎች የሚወጣው ግሩም መዓዛ አፍንጫንም፣ መንፈስንም ደስ ያሰኛል። በአካባቢው ከሚገኙ በመዓዛቸው ከሚመረጡ ተክሎች በተለያየ ዝግጅት የጭሳጭስ ውጤቶች ይዘጋጃሉ። 

የወሎ ጭስ በአብዛኛው የሚገኘው ሰሜን ወሎ ራያ ቆላማው አካባቢና በኦሮሚያ ልዩ ዞን ከሚሴና ባቲ አካባቢዎች ነው። ከወሎ ጭሳጭሶች መካከል ወይባ፣ ቡክቡካ፣ ቅጥቅጥ፣ ስምቡል፣ ቆቦ ጭስ፣ ደውሌ፣ ሶርሳ፣ አርቲ፣ አሽኩቲ፣ ጠጅ ሳር፣  አደስ፣ ሚጢ፣ ከርቤ፣ ድኝ፣ ወገርትና ቀበርቾ ተጠቃሾቹ ናቸው።

ለመድኃኒትነት አገልግሎት ይውላሉ ተብለው ከሚታሰቡት ጭሳጭሶች መካከል የወይባ እንጨትና ቀበርቾ ይገኙበታል። በወሎና አካባቢው የወይባን ጭስ በአብዛኞቹ ወላድ ሴቶች ይሞቁታል። ይህም የሚሆንበት ምክንያት ጭሱ ማህፀን አካባቢ በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ቁስለት ቶሎ እንዲደርቅና እንዲድን ከማድረጉ ባሻገር ለመልካም ጠረንና ለሰውነት ጥራት እንደሚጠቅም ይታመናል።

የወይባ ዛፍ ወደ ቢጫ የሚጠጋ ቀለም አለው። አርሶ አደሮች ዛፉን ቆራርጠው ለገበያ፤ ነጋዴዎቹ ደግሞ ለተጠቃሚው በሚያመች መልኩ አዘጋጅተው ያቀርቡታል። እንጨቱ ሳይላጥ እርጥበቱን እንደጠበቀ ቢሆን ይበልጥ ይመረጣል። እርጥበቱ ከበዛና የመሻገት ምልክት የሚያሳይ ከሆነ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት መታጠብና መጽዳት ይኖርበታል። እንጨቱ የሚፈለጠውም ለመሞቅ ዝግጁ ሲሆኑ ብቻ ነው።

የወይባ ጢስ የሚሞቁ ሴቶች በየቤታቸው የወይባ ጢስ መሞቂያ ጉድጓድና ልዩ ልዩ መጠቀሚያ አላቸው። በባህሉ መሰረት አንዲት ሴት ወይባ ለመሞቅ ስትዘጋጅ ማሟላት ያለባት ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ጭሱን ከመሞቋ በፊት በዛ ያለ ቅቤ አናቷን መቀባት የሚኖርባት ሲሆን የወይባው ጢስ ጉድጓዱ ውስጥ ከተደረገ በኋላ ማንኛውንም ያዘቦት ልብስ መልበስ ትችላለች። ሆኖም ጢሱ ወደ ውጭ እንዳይወጣ ቆዳ ወይም የብርድ ልብስ ከላይ መደረብ ተገቢ ነው።

ሌላው የወሎና አካባቢው ማህበረሰብ ለመድኃኒትነት አገልግሎት ከሚጠቀምባቸው የጭስ አይነቶች አንዱ ቀበርቾ ነው። ቀበርቾ ከስራ ስር የተክል ዓይነት የሚመደብ ነው። በአብዛኛው ክፉ መንፈስ ይዞት እንደታመመ የሚታሰብ ሰው ቀበርቾውን ለተከታታይ ሶስት ቀን ሲታጠን ይፈወሳል /ክፉው መንፈስ ይለቀዋል/ ተብሎ ይታመናል። በሌላ በኩል በከባድ የሆድ ቁርጠትና ውጋት ለታመመ ሰው ቀበርቾውን በሚያኝክበት ጊዜ ከህመሙ እንደሚድን ይነገራል።

የደሴ ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ አሚናት መሀመድ የወሎ ጭስን ላለፉት 30 ዓመታት በመነገድ ላይ ይገኛሉ። የሚቀምሙት ጭስ ተፈጥሯዊ ከሆኑና በዋነኝት ከራያ ቆቦና ከሚሴ አካባቢ ከሚመጡ ዛፎች ከሚገኝ ውጤት እንደሆነ ይገልጻሉ። ቅመማው ላይ ስለሚቀላቀሉት ነገሮች ሲገልጹም ሚስክ፣ የተፈጨ ሰንደል፣ ጃዊ፣ ሽቶና ሰይፈል ከመሳሰሉ ነገሮች እንደሆነና ለጭሱ የበለጠ መልካም መዓዛ እንደሚሰጡት ይናገራሉ። 

በተለያየ አጋጣሚ የወሎን ምድር የረገጠ ሰው ማስታወሻ ይሆነው ዘንድ ከሚቋጥራቸው ነገሮች አንዱ የወሎ ጭስ ነው። ወ/ሮ አሚናትን ደንበኟቾ እነማን እንደሆኑ አዲስ ዘይቤ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ከአዲስ አበባ፣ ከጎንደርና ባህር ዳር የሚመጡ ደንበኞቼ በብዛት የሚወስዱለኝ ሲሆን ደሴ ከተማ ላይም በርካታ ደንበኞች አሉኝ” ይላሉ። የመሸጫ ዋጋውን በተመለከተም “በሰሃን ተሰፍሮ ከ 5 ብር ጀምሮ እስከ 70 ብር ድረስ እንደየሰዉ የመግዛት አቅም እንሸጣለን”ይላሉ።

ወቅቱ የበዓል ሰሞን እንደመሆኑ መጠን ለበዓሉ ማድመቂያ ይሆን ዘንድ ደንበኞች ከወ/ሮ አሚናት የተቀመመ የወሎ ጭስ ሲገዙ ተመልክተናል።

ወ/ሮ የሺወርቅ ማስረሻ ደሴ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ናቸው። “በዓል ሲደርስ ተደስቶ ለማሳለፍ በደሴና አካባቢው ቤት ውስጥ ከሚደረጉ ዝግጅቶች የወሎ ጭስ ለበዓሉ ማድመቂያ የማይቀሩ ከሚባሉት ዋነኛው ነው። ዘመድ ጎረቤት ተሰባስቦ ቡና ተፈልቶ ሲጠጣ በወሎ ጭስ ልዩ መዓዛ ካልታጀበ ቡና መጠጣትህ ስለማያስደስትህ ጭሱ ቤታችን ውስጥ መኖሩ መሰረታዊ እንደሆነ እናስባለን" በማለት ያስረዳሉ።

በደሴና አካባቢው በአብዛኛው ግለሰቦች መኖሪያ ቤት ቡና ሲፈላ የወሎን ጭስ ማጨሱ የተለመደ ነው። ከተማ ላይ በጀበና ቡና ንግድ ላይ የተሰማሩ ለደንበኞቻቸው ቡና ሲያቀርቡ በወሎ ጭስ አጅበው ማስተናገድ የአገልግሎቱ አንድ አካል ነው። 

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወ/ሮ ሰላማዊት ግርማ “በዘመን መለወጫ የእንቁጣጣሽ በአል ጠጅ ሳር፣ አርቲ፣ ከሴ ከመሳሰሉት መልካም መዓዛ ያላቸው ተክሎች ጋር ቤትሽን በቄጤማ ሳር ስታሳምሪና የወሎ ጭስንም ስናጨስ ቤታችን ውስጥ በአል መሆኑን የሚገልፅ የተለየና የማይረሳ ድባብ ይፈጠራል” ትላለች። 

“እነዚህ ልዩ ጭሶች የወሎየነቴ አንዱ መገለጫ በመሆናቸው ለራሴ ከመጠቀም ባሻገር ለሌሎች ወዳጅ ዘመዶቼ በስጦታነትም አበረክታቸዋለሁ” የምትለው ደግሞ ጭሶቹ ለሚሸጡበት ገበያ እንደፍላጎቷ ስትሸምት ያገኘናት ወ/ሮ መይሙና ኢብራሂም ናት። “የዘንድሮውን የዘመን መለወጫ በዓል ምንም እንኳን በጦርነት ስጋት ውስጥ ሆነን ብናከብረውም ወትሮም እንደማደርገው ወዳጆቼ ቤት 'እንኳን አደረሳችሁ' ለማለት ስሄድ በስጦታነት የወሎ ጭስ ይዤ ስለምሄድ በርከት አድርጌ እየገዛሁ ነው” በማለት በገበያው የተገኘችበትን ምክንያት ትናገራለች።

ወሎ ውስጥ ማህበረሰቡን የሚጎዳ በሽታ ሲከሰት፣ ዝናብ ሲጠፋ፣ ግጭትና ጦርነት ሲከሰት፣ ሀገር ላይ ችግር ሲመጣ የየአካባቢው የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች ተሰባስበው ለፈጣሪያቸው ጸሎትና ልመናቸውን በሚያሰሙበት ጊዜ በአካባቢው ባህል መሰረት መልካም መዓዛ ያለውን የወሎ ጭስ እያጨሱ በጋራ ጫት መቃም የሚዘወተር ባህላዊ ልምድ ነው። 

ሼኽ ሀሰን አመዴ መርሳ ከተማ ውስጥ ነዋሪና የእስልምና ኃይማኖት መምህር ናቸው። የወሎ ጭስ በማህበረሰቡ ዘንድ ስላለው ተቀባይነት ሲናገሩ “በወሎ አካባቢ ጫት ሲቃምና ቡና ተፈልቶ ከመጠጣቱ በፊት የወሎ ጭስ ማጨስና ቡና ያፈላችውን ወይም ያፈላውን ሰው መመረቅ የተለመደ ተግባር ነው። ይህ ልማድ ከኃይማኖት ጋር የሚያያዘው ምንም አይነት ነገር የለም፣ የአካባቢ ባህል እንጂ” በማለት ያስረዳሉ።

በወሎ እና በአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተሰባስበው ዱዓ (ጸሎት) በሚያደርጉበት ሰዓት የወሎ ጭስ ሲጨስ ከመልካም መዓዛው ባሻገር የተለየ ደስታና ኃሴት እንደሚያጎናፅፍ ሼኽ ሀሰን አመዴ ይገልጻሉ።

የወሎ ጭስ በወሎ አካባቢ ብቻ የሚገኝ ሀገር በቀል ተክሎች /Endemic plants/ ስለመዘጋጀቱ በወሎ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የእውቅና ምስክር ወረቀት ተስጥቶታል።

አስተያየት