ጳጉሜ 5 ፣ 2014

የኑሮ ውድነት የተጫነው የአዲስ ዓመት የበዓል ገበያ

ኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

ዳግም በተቀሰቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት የዘንድሮውን የዘመን መለወጫ በዓል በጦርነት ስጋት እና እሱን ተከትሎ በተባባሰው የኑሮ ውድነት ምክንያት በደሴ ከተማ የበዓል ገበያው ተቀዛቅዞ ይታያል።

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የኑሮ ውድነት የተጫነው የአዲስ ዓመት የበዓል ገበያ
Camera Icon

ፎቶ፡ አዲስ ዘይቤ (አሳሳቢው የሸቀጦች ዋጋ ንረት በበዓላት ሰሞን ይበልጥ ይጨምራል)

“በእግዚአብሄር ቸርነት እና በረከት እንጂ ሰው በደሞዝና በገበያው አይደለም እየኖረ ያለው”ይላሉ በፒያሳ አትክልት ተራ ለበዓል ሸመታ ሲዘዋወሩ ያገኘናቸው ወ/ሮ ጥሩነሽ። “ምንስ ያልጨመረ ነገር አለ?!” በማለት በበአል ገበያ የሸቀጦችን የዋጋ ንረት በምሬት ይናገራሉ። 

በአዲስ ተሰፋና መንፈስ፣ በአደይ አበባ፣ በቄጠማው፣ በቂቤ፣ በእንቁላል እና ዶሮ ግብይት የሚደምቀው የእንቁጣጣሽ የበዓል ገበያም በፈጣን የዋጋ ንረት ታጅቦ አዲሱ ዓመት 2015 ዓ.ም ደርሷል። 

የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተሮች መዲናችንን አዲስ አበባን ጨምሮ በድሬዳዋ፣ በአዳማ፣ በባህር ዳር እና በሐዋሳ ከተሞች ያለውን የገበያ ሁኔታ ቃኝተው እንዲሁም በጦርነት ስጋት ውስጥ ባሉት በጎንደር እና በደሴ ከተሞች ተዘዋውረው የበዓል ገበያውን ድባብ ተመልክተዋል። 

የአዲስ አበባን የበዓል ገበያ በፒያሳ፣ በቄራና በሾላ የገበያ ስፍራዎች ተዘዋውረን ጎብኝተናል። በአዲስ አበባ ቄራ የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል ባደረግነው ቅኝት በሬ በአማካኝ ከ30 ሺህ እስከ 110ሺህ ብር ይሸጣል። የፍየል ዋጋ እንደየመጠኑ የተለያየ ሲሆን በአማካኝ ከ 6ሺህ እስከ 15ሺህ ብር፣ በግ እንደየደረጃው ከ8ሺህ እስከ 25 ሺህ ብር እንዲሁም ዶሮ ከ600 እስከ 900 ብር ሲሸጥ ተመልክተናል።

የሽንኩርት ዋጋ ከቦታ ቦታ ይለያያል። በፒያሳ አትክልት ተራ በኪሎ እስከ 45 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ ነጭ ሽንኩርት እስከ 180 ብር፣ ቲማቲም እስከ 60 ብር በኪሎ ሲሸጥ፣ እንቁላል ከ 8 እስክ 12 ብር እየተሸጠ ነው። ዘይት ባለ 5 ሊትር ደግሞ እስከ በ950 ብር በስፋት ይገኛል።

ድሬዳዋ

ከክፍለሃገር ከተሞች በድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያ ቅኝታችን ያደረግነው በድሬዳዋ እድሜ ጠገቡና በቅርስነት በተመዘገበው የቀፊራ የገበያ መዕከል ነው። በዘንድሮው አዲስ አመት በድሬዳዋ ከተማ የአቅርቦት ችግር ባይስተዋልም አዲስ ዘይቤ ባደረገችው ምልከታ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የተከሰተው በቲማቲም ላይ ነው። ኪሎው እስከ 30 ብር ይሸጥ የነበረው ቲማቲም 100 ብር ገብቷል።

የበዓሉ ዋና ማድመቂያ የሆነው የሐበሻ ዶሮ ከ350 እስከ 500 ብር ሲሽጥ፣ ቀይ ሽንኩርት 60 ብር፣ ቅቤ ከ 600 እስከ 700 ብር፣ ጤፍ በየደረጃው ከ 52 እስከ 58 ብር በኪሎ እየተሸጠ ይገኛል።

ሌላው ድሬዳዋ የምትታወቅበት የእጣን ገበያን ስንመለከት የባህር እጣን በኪሎ 400 ብር፣ የኡጋዴኑ 200 ብር እንዲሁም የቅርፊት እጣን 150 ብር በኪሎ እየተሸጠ ነው። 

በቀፊራ የገበያ ስፍራ ያገኘናቸው ወ/ሮ መብራት ጉልላት የአቅርቦት ችግር በሌለበት ሁኔታ የቲማቲም ዋጋ በዚህ ደረጃ መወደዱ ግራ እንዳጋባቸው ይገልጻሉ። የጤፍ ነጋዴዋ ወ/ሮ ፋይዛ መሀመድ በበኩሏ ለበዓሉ በጤፍ ላይ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንዳልተደረገ እና የገበያ ሁኔታውም የተረጋጋ እንደሆነ ትናገራለች። 

ቀጣዩን ቅኝት ያደረግነው 'ጀላባ' ተብሎ በሚጠራው የድሬዳዋ ትልቁ የከብቶች መሸጫ ስፍራ ነው። በጀላባ በግ ከ3ሺህ ብር እስከ 5ሺህ፣ ፍየል እስከ 6ሺህ ብር ሲሸጥ፤ ሰንጋ በሬ ከ70ሺህ እስከ 100ሺህ ብር በመሸጥ ላይ ይገኛሉ። ከበሬ ዋጋ ጋር በተያያዘ አንድ መደብ ቅርጫ 8ሺህ ብር እንደደረሰም በከተማዋ ይነገራል። 

አቶ ለገሰ ሀይሉ ለረዥም ዓመታት በበዓላት ቅርጫ በማከፋፈል ይታወቃሉ። የበሬ ዋጋ ከበዓሉ ቀደም ብሎ ስለተወደደ ቅርጫ የሚገባው ሰው ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ይገልፃሉ።

ጎንደር

በጎንደር ከተማ ባለው የበአል ገበያ ዘይት በ5 ሊትር 1,050 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን ከአለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የ100 ብር ጭማሪ አሳይቷል። 

በጎንደር ለበዓሉ ከፍተኛ የዋጋ ጨማሪ ያሳየው የዶሮ ገበያው ሲሆን በዚህም አንድ የሐበሻ ዶሮ እስከ 850 ብር እየተሸጠ ይገኛል። ሽንኩርት በኪሎ 65 ብር ሲሸጥ ከአለፈው ሁለት ወር ጋር ሲነፃፀር የ25 ብር ጭማሪ አሳይቷል። ቲማቲም በኪሎ 70 ብር፣ ስኳር ካለፈው ወር 50 ብር ጨምሮ በኪሎ 100 ብር እየተሸጠ ነው። 

በጎች ከ6 ሺህ እስከ 12 ሺህ እንደየመጠናቸው ለገበያ የቀረቡ ሲሆን የፍየል ዋጋ ደግሞ እስከ 14ሺህ ብር ደርሷል። በከተማው ለሚታየው የሸቀጦች ጭማሪ ቁጥጥር አለመደረጉ እና የአቅርቦት እጥረት መኖሩ እንደሆነ እዋሪዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። 

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ለዋጋ ንረቱ ትልቅ ምክንያት እንደሆነ እንደሚገምቱ የሚናገሩት ደግሞ ለበዓል ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወ/ሮ ስለእናት ዘሪሁን ናቸው። “ጦርነቱ እንደገና በማገርሸቱ በጎንደር እና በአካባቢው የተፈናቃዮች መብዛት የሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል” ብለው እንደሚያምኑ ወ/ሮ ስለእናት ይናገራሉ። 

ሐዋሳ

ለ 2015 ዓ.ም አዲስ ዓመት መግቢያ እንደወትሮው ደምቃ በምትታየው ሐዋሳ፤ ከከተማዋ ነዋሪዎች በተጨማሪ በዙሪያዋ ከሚገኙ ወረዳዎች ለበዓል ግብይት ብዙዎች ወደ ሐዋሳ ይመጣሉ።

በሐዋሳ የቁም እንስሳት ገበያ ፍየል እስከ 7ሺህ ብር ድረስ እየተሸጠ ሲሆን የሐበሻ ዶሮ ከ400 እስከ 900 ብር፣ 'የፈረንጅ ዶሮ' ደግሞ እስከ 600 ብር ይሸጣል። እንቁላል በ9 ብር፣ ባለ 5 ሊትር ዘይት 1 ሺህ ብር፣ ሽንኩርት በኪሎ 42 ብር፣ ቲማቲም 60 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 150 ብር፣ በርበሬ 400 ብር እንዲሁም ጤፍ በኩንታል 5ሺህ 500 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛሉ።

የአካባቢው ምርት የሆነው ቡና እንደ ደረጃው በኪሎ ከ300 እስከ 400 ብር ሲሸጥ፣ ቅቤ በኪሎ 800 ብር፣ አይብ እስከ 500 ብር ሲሸጥ ይታያል። በአብዛኛው ሽቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ስላለ ገበያው መቀዛቀዙን ገበያተኛው ሲናገር ይደመጣል። 

ዶሮ ሲገዙ ያገኘናቸው አቶ ወገኔ ደሱ የዋጋ ልዩነቱን ሲያስረዱ ከፋሲካ በዓል አንፃር የመቶ ብር ጭማሪ መኖሩን ገልፀው አንድ የሐበሻ ዶሮ በ700 ብር መግዛታቸውን ተናግረዋል። በነጋዴዎቹ በኩል ለዶሮዎች የሚቀርበዉ መኖ መወደዱ ለዋጋ ጭማሪው ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።

ደሴ

ከሲዳማ ወደ ወሎ ስንሻገር በደሴ ከተማ ዳግም በተቀሰቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት የዘንድሮው የዘመን መለወጫ የበዓል ገበያው ተቀዛቅዞ ታይቷል። በጦርነት ስጋት እና እሱን ተከትሎ በተባባሰው የኑሮ ውድነት ምክንያት የደሴ ገበያ የቀድሞ ድምቀቱን አጥቷል።

በአካባቢው ካለው የጦርነት ስጋት በተጨማሪ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ በመጣው የፍጆታ እቃዎች ከመጠን በላይ መወደድ ምክንያት እንዳንዶች “ስለ በዓል ደስታ ማሰብ ይቅርና በልቶ ማደርም አስቸጋሪ ሆኗል” ሲሉ በምሬት ይናገራሉ። 

በደሴ ገበያ ያለውን የዋጋ ተመን ስንመለከት 1ኪሎ ቲማቲም 90 ብር ሲሸጥ የሐበሻ ዶሮ እስከ 1ሺህ ብር እየተባለ ነው። የቀንድ ከብትም በጣም ከመወደዱ ጋር ተያይዞ በፊት ጊዜ ለ12 ሰው የነበረው የአንድ በሬ ቅርጫ አሁን ላይ 20 ሰዎች ሆነው ሊካፈሉ እንደተዘጋጁ ሪፖርተራችን ታዝቧል።

አዳማ

አውደ ዓመት ሲደርስ የበዓል ድባብ በጉልህ ከሚታይባቸው ከተሞች መካከል አንዷ አዳማ ናት። በዙሪያዋ ካሉት የወንጂ፣ የአዋሽና የወለንጪቲ ከተማ ነዋሪዎች ለበዓል ግብይት ወደ አዳማ ይመጣሉ። በተጨማሪም አዳማ የሀገሪቱ ወጪ ገቢ መተላለፊያ ከመሆኗ አንጻር ለበዓሉ የሚደረገው እንቅስቃሴ የተለየ ድባብ ይፈጥራል።

የ2015 ዓ.ም ዘመን መለወጫ ካሁኑ ዝግጅቱ ቢጀመርም በፈጣን ሁኔታ የሚቀያየረው የዋጋ ንረት ግን በአሉ ላይ ጥላ አጥልቶበታል። ገበያውም የወትሮው የበዓል ሰሞን ግርግር አይታይበትም። የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር በአዳማ የአመዴ ገበያ፣ የ17 ገበያ እንዲሁም በአራዳ የገበያዎች ተዘዋውሮ ቅኝት አድርጓል። 

በሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው አቶ ሽኩር እንደሚለው የኑሮ ውድነቱ የበዓል ገበያውን አደብዝዞታል። “ከፋሲካ በዓል አንጻር እንኳን ገበያው ተቀዛቅዟል” የሚለው ሽኩር በሸቀጦች ላይ ከሌላው ጊዜ የተለየ የዋጋ ልዩነት እንዳለ ይናገራል። “አምና በዚህ ጊዜ ዘይት 500 ብር ነበር። በአሁን እስከ 1 ሺህ 100 መቶ ብር ነው” ይላል።

በአዳማ ከሳምንታት በፊት ቅናሽ ያሳየው ዘይት በድጋሚ መጨመሩ ታውቋል። በዚህም 5ሊትር ዘይት እስከ 1ሺህ 100 ብር ሲሸጥ፣ ዛላ በርበሬ በኪሎ 250 ብር፣ ኮረሪማ 140 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

የአዘቦት እና የበዓል ማድመቂያ የሆነው ቡና በኪሎ 400 ብር፣ ፈንዲሻ 120 ብር እንዲሁም በከባድ ፍለጋ የሚገኘው ስኳር አዳማ ላይ በኪሎ እስከ 110 ብር እየተሸጠ ነው። በዚህ ሳምንት ከፍተኛ የዋጋ ጫማሪ ካሳዩ ሸቀጦች መካከል ነጭ ሽንኩርት ከ100 ብር ወደ 180 ብር እንዲሁም ቲማቲም ከ25 ብር ወደ 70 ብር ጭማሪ አሳይቷል።

"ገበያው እጅግ ቀዝቅዟል" የሚሉት ወ/ሮ ድርቤ ጉርሙ በአዳማ ከተማ የቅቤ ነጋዴ ናቸው። በፋሲካ እና በኢድ በዓላት ወቅት ከነበረው ጋር በማነፃፀር የቅቤ ዋጋ እንደቀነሰ ይናገራሉ። “ቅቤ ለፋሲካ የሸጥነው 800 ብር ነበር አሁን ከ650 ብር እስከ 700 ብር ድረስ እየሸጥን ነው” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

ከበዓሉ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ተፈላጊነት የሚኖራቸው የእህል ዘሮች ግብይት በ17፣ በአመዴ እና አራዳ ገበያዎች በሚገኙ መጋዘኖች ይከናወናል። በእነዚህ ገበያዎች ኩንታል ማኛ ጤፍ  5600 ብር፣ ነጭ ጤፍ 5500 ብር እና ጥቁር ጤፍ 5200 ብር እየተሸጡ ይገኛሉ።

በአዳማ የዶሮ ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል። “ለፋሲካ እስከ 900 ብር ድረስ ተሸጦ ነበር” የሚሉት ነጋዴዎቹ አሁን ግን እስከ 700 ብር ድረስ ለገበያ ማቅረባቸውን ይናገራሉ። እንቁላልም የፈረንጅ 11 ብር እንዲሁም የሐበሻ እንቁላል 12 ብር እየተሸጠ ነው።

በአዳማ ከተማ ሙገር አካባቢ፣ 09 አካባቢ፣ እሮብ ገበያ፣ አመዴ ኬላ አካባቢ የበግ፣ የፍየል ግብይት የሚከናወን ሲሆን እሮብ ገበያ በዋናነት የከብት ሽያጭ ረቡዕ እለት ብቻ ይከናወንበታል። በዚህም በግ እስከ 12ሺህ ብር፣ ፍየል እስከ 15ሺህ ብር ድረስ ዋጋ እንደወጣላቸው ቃኝተናል። “ፍየል ተፈላጊነቱ እየጨመረ ስለመጣ ዋጋውም የበለጠ እየተወደደ ነው” ሲሉ ነጋዴዎቹ ይገልጻሉ። 

ባህላዊው የስጋ መከፋፈያ የሆነው ቅርጫ ከኑሮ ውድነት እንዲሁም ከበግ እና ፍየል ዋጋ መወደድ አንጻር ተመራጭነቱ ከፍ እያለ መጥቷል። አንዱን መደብ ቅርጫ በ 5ሺህ ብር እንደገባ የሚናገረው አቶ ዘመዴ ከወዳጆቹ ጋር ስለሆነ እንጂ አሁን ላይ ከ6ሺህ ብር በታች ቅርጫ እንደማይገኝ ይገልጻል። 

በአዳማ በሚገኙ ልኳንዳ ቤቶች ኪሎ ስጋ ከ600 እስከ 1200 ብር እየተሸጠ ይገኛል። በዕሮብ ገበያ የበሬ ዋጋ ከ30 ሺህ እስክ 60 ሺህ ብር ሲሸጥ ውሏል።

ባህር ዳር

በህብረተሰቡ ዘንድ ለበዓል በአንድ አካባቢ ሰዎች በጋራ ከሚከወኑ ተግባራት አንዱ ቅርጫ ነው። በባህር ዳር ከተማ የቅርጫ ስጋ መግባት የፈለገ ሰው ወደ ከብት ገበያ ሄዶ ከሚያገኘው ሰው ጋር ተመዝግቦ በጋራ ከብት በመግዛት እርድ ያካሄዳል። በመጨረሻ የድርሻውን ስጋ ተከፋፍሎ “ለዓመቱ ያድርሰን” በማለት ተመራርቆ ይለያያል።

በባህር ዳር ገበያ በሬ እሰከ 80 ሺህ ብር እየተሸጠ ይገኛል። እንደ ሸማቾች ገለፃ የበሬ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። የበግ እና የፍየል ገበያውን ስንመለከት የአቅርቦት ችግር የሌለበት ሲሆን በግ እስከ 13 ሺህ ብር ሲሸጥ ፍየል ደግሞ እስከ 16 ሺህ ብር ድረስ ዋጋ ወጥቶለታል። 

በዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል በባህር ዳር ከተማ ደማቅ የበዓል ግብይት ይስተዋላል። የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር በባህር ዳር ከተማ ያለውን የከብት ገበያ እንደቃኘው ለበዓል ከሚስፈልጉ ነገሮች መካከል የዶሮ፣ የእንቁላል፣ የዘይት እና የሽንኩርት ዋጋ ከጎንደር ገበያ ጋር ተመሳሳይ እንደሆን ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ ከቀረው ዓለም ተለይታ የራሷ ብቻ የሆነ የ13 ወር የዘመን መቁጠሪያ ቀመር መሰረት በመጨረሻዋ ወርሃ ጷጉሜ ላይ ሆነን የበዓል ገበያ እንዲህ ዳሰነዋል። ልጓም አልባው የዋጋ ንረት በቀጠለበት ሁኔታ ሁሉም እንደአቅሙ በዓሉን ማሳለፉ እንዳለ ሆኖ፤ ከበዓል በኋላ ደግሞ ትምህርት ቤት ስለሚከፈት የደብተር፣ የቦርሳ እና የመፅሐፍ ገበያው ከወዲሁ አሳሳቢ እንደሚሆን ይታሰባል።

አስተያየት