የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወዳጅ የዶክተር ምህረት ሹመት

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታመስከረም 28 ፣ 2014
City: Addis Ababaዜናወቅታዊ ጉዳዮች
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወዳጅ የዶክተር ምህረት ሹመት

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በትላንትናው ዕለት ለከፍተኛ የመንግስት ሃላፊነት ቦታዎች ሹመት ከሰጧቸው አመራሮች መካከል ዶክተር ምህረት ደበበ አንዱ መሆናቸው ይታወቃል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ወዳጅ እንደሆኑ የሚነገረው ዶክተር ምህረት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተሾሙ ሲሆን በትምህርት ዝግጅታቸውም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና ዲግሪያቸውን ሰርተው በአሜሪካ ሴንት ሉዊስ ዩኒቨርስቲ በስነ-አዕምሮ ህክምና ስፔሻላይዝ አድርገዋል።

በሌላ በኩል ዶክተር ምህረት የኢትዮጵያውያንን ንቃተ- ህሊና እና ማህበራዊ ትግሎችን በሚዳስስበት የ‘ተቆለፈበት ቁልፍ’ እና ‘ሌላ ሰው’ በተሰኙት መፅሃፎቹ ይታወቃል። ከዛም ባሻገር በዘርፈ ብዙ ማህበረሰብ አንቂነታቸውም በስፋት ይታወቃሉ።

ዶክተር ምህረት ደበበ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር የቅርብ ጓደኛ መሆናቸው ይነገራል። ይህንንም ዶክተሩ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲያረጋግጡ ተደምጧል። በሌላ በኩልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጋቢት 24 2010 ዓ.ም. ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኙበት የማህበራዊ ጉዳዮች ፕሮግራም መድረክ በዶክተር ምህረት ደበበ ባለቤትነት በሚመራው ማይንድ ሴት ድርጅት አማካኝነት በሚሊኒየም አዳራሽ ግንቦት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የተዘጋጀው የአዲስ አስተሳሰብ ዝግጅት ላይ መሆኑም ይታወሳል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛ ፕሮግራም ላይ መገኘት ለታዳሚዎቹ ድንገቴ (ሰርፕራይዝ) እንደነበር መነገሩም ሌላኛው ትዝታ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ “አዲሱን ትውልድ በአሮጌ አስተሳሰብ መምራት አይቻልም” የሚል ንግግር ባደረጉበት መድረክ የተገኙት በሳዑዲ ዓረቢያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ሲመለሱ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በቀጥታ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ መምጣት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለተሰባሰቡት እና በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች ለሚገኙት 6,900 ታዳሚዎች የማይረሳ ገጠመኝ ሆኖ ማለፉ በስፋት ተነግሯል።

በጊዜው ‹‹እኔ ነኝ አዲሷ ኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደውና በዓይነቱ ብዙ ሰዎችን በማሳተፍ የመጀመርያ በሆነው በዚህ ዝግጅት የክብር እንግዳ እንደሚኖር በዶክተር ምህረት ደበበ ሲነገር ቢቆይም ማንነቱ አልተገለፀም ነበር። ይሁንና በዝግጅቱ ማብቂያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ከተሳታፊዎች የተሰማው ፉጨት፣ ጭብጨባና ጩኸት አዳራሹን አናውጦት ነበር። በመድረኩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት የነበሩባቸው አገሮች ስላዩት ነገርና ስላከናወኗቸው ጉዳዮች፣ በተጨማሪም  ስለራዕይ አስፈላጊነት ንግግር ካደረጉ በኋላ መንግሥት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወርቅ ተሸላሚ ሆነው የሚመረቁ ተማሪዎችን በቤተ መንግሥት (በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት)፣ በፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በሌሎች እንደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባሉ የልማት ማዕከላት ተገኝተው ልምድ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለው ነበር፡፡ ተማሪዎቹ በፈለጉበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና አገራቸውን ማገልገል እንዲችሉ የሚያደርግ አዲስ ፕሮጀክትም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንደሚጀመር ተናግረው የትምህርት ጥራቱን ለማሳደግም በትኩረት እንደሚሠራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀው ነበር።

ይህ ዝግጅት በተለያዩ የመንግስት እና የግል ቴሌቭዥን ጣቢያዎች በቀጥታ መተላለፉ የሚታወስ ሲሆን የሁለቱን የቅርብ ወዳጅነት ለማወቅ የያኔው ድባብ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር። ዶክተር ምህረትም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስላላቸው ጓደኝነት ተጠይቆ ምላሽ ከሰጠባቸው መድረኮች መካከል በሸገር ካፌ የሬዲዮ ፕሮግራም በምርጫ፣ በዲሞክራሲ እና በተዛማች ጉዳዮች መካከል ከመዓዛ ብሩ ጋር የነበረው ቃለመጠይቅ ተጠቃሽ ነው።

ዶክተር ምህረት እንዲመራው ሃላፊነት የተጣለበት ተቋም ከዚህ ቀደም “የኢፌዲሪ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ” በመባል ይታወቅ የነበረው እና ባሳለፍነው ሰኔ 15፣ 2013 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ “የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ” በመባል እንዲሰየም የተወሰነበትን ተቋም ሲሆን፣ አካዳሚው የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ሁለንተናዊ ሰላም፣ ዲሞክራሲ እና ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚል መርህ ከሚሰጣቸው አጫጭር ስልጠናዎች ባሻገር “ልማታዊ አመራር” የሚል የትምህርት ካሪኩለም ቀርጾ በማስተርስ ዲግሪ “የልማታዊ አመራር ማስተርስ” በሚል ፕሮግራም እና በፒኤችዲ “የልማታዊ አመራር” ትምህርት እንደሚሰጥ ይታወቃል።

በመሆኑም አዲሱ የተቋሙ ፕሬዝዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ ሹመታቸውን አስመልክቶ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል አብዛኞቹ ለቦታው ብቁ መሆን እንደሚችሉ የሚናገሩ ሲሆን ከሁለት አመት በፊት ዶክተሩ በሰሎሜ ሾው ላይ በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ስለ አመራር ልህቀት ሰፋ ያለ ማብራርያ መስጠታቸውም ይታወሳል።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist works at Addis Zeybe as a reporter while exploring her passion for storytelling and content creation.