የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ወደ መቐለ ሄደው ከዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር ከተወያዩ በኋላ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሰጡት መግለጫ የፌደራል መንግሥቱን ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለማደራደር የሚያደርጉትን ጥረት አልቀበልም ያለ ወገን እንደሌለ ገለፁ።
መግለጫውን የሰጡት በበይነ መረብ በተካሄደ ስብሰባ ሲሆን በስብሰባው የህብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ፣ የህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ በአፍሪካ ህብረት የግብጽ ቋሚ ተወካይ መሃመድ ጋድ እና በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ተሳትፈዋል፡፡
በስብሰባውም ኦባሳንጆ የአፍሪካ ሕብረት ሰላም ለማምጣት እና ለድርድር ልዩ መልዕክተኛ መሰየሙን ሁሉም ወገን በበጎ መቀበሉን በመጥቀስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድም ሆኑ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካዔል ላደረጉላቸው መልካም አቀባበል እና መስተንግዶ ምስጋና አቅርበው በተጨማሪም ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ጋር እና ከኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር መወያየታቸውንም ገልፀዋል።
ድርድሩ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና ቀጣይ ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ ጥቆማ ሲሰጡ "በአሁን ሰዓት የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ስለምገኝ ድርድሩ ወዴት እንደሚሄድ ለመናገር ጊዜው አይደለም" ሲሉ አሁን ያሉበት ደረጃ በተደራዳሪ ወገኖች ዘንድ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ምን እንደሆነ የመለየት እንደሆነ ማስረዳታቸውን ብሉምበርግ በዘገባው አስነብቧል።
ይሁንና በመግለጫቸው ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ኃይል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለድርድር እንዲቀመጡ ፣ ፈጣን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ፣ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች አሁንም አፋጣኝ እርዳታ ማድረሳቸውን እንዲቀጥሉ፣ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ እና አለምአቀፉ ማህበረሰብ ለሰላም የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ግፊት ማድረጉን እንዲቀጥል "ከዚህ በላይ ጊዜ መውሰድ አይገባም ያለን ጊዜ ውስን ነው" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኦባሳንጆን በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛነት ሲሾም የመጀመሪያ ጉዳያቸው አድርገው የወሰዱት የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነትን በመሆኑ እሳቸውም ኃላፊነቱ ሲሰጣቸው መጀመሪያ ያደረጉት ነገር በአፍሪካ ቀንድ እና ከአፍሪካ ቀንድ ውጪ ያሉ ባለድርሻ አካላትን ማማከር መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የኦባሳንጆን መፍትሔ እንደሚጠብቅ መግለፁ እና የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳም ኦባሳንጆ ከደብረጽዮን ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን በይፋዊ ትዊተር ገፁ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
በተያያዘም የሰሜኑ ጦርነት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል በሚል የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሚታወስ ሲሆን ከኦባሳንጆ በተጨማሪ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) ኃላፊ የሆኑት ማርቲን ግሪፊትስም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበርም ተገልጿል።
ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ባለፈው ሳምንት አንድ ዓመት የሞላው ጦርነት ከወራት በፊት ወደ አማራና የአፋር ክልሎች ተስፋፍቶ አሁንም እየተካሄደ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ይህን ጦርነት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ለውይይት ሲቀመጥ ለ12ኛ ጊዜው ነው።
እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለፃ ጦርነቱ በድርድር መፍትሄ እንዲፈለግለት የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም አስካሁን ውጤት ያልታየ ሲሆን በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተጠቅሷል።