በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የተፈጥሮ ሀይቆች መካከል የሀዋሳ ሀይቅ (በተለምዶ አጠራሩ ፍቅር ሀይቅ) አንዱ ነው። ለከተማዋ የቱሪዝም መስህብ እና የውበት ምንጭ ሆኗል። ሀይቁን ተንተርሰው የተገነቡት ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች እና መዝናኛ ማዕከላት ደግሞ የጎብኚዎችን ምቾት አስጠባቂ ናቸው። ሀዋሳ የሚለው ስያሜ አመጣጥ ከሀይቁ መኖር ጋር የተያያዘ ነው የሚሉ መዛግብት አሉ። መዛግብቱ ለአባባላቸው የሚያቀርቡት ማስረጃ ‘ሀዋሳ’ የሚለውን ቃል ትርጓሜ ነው። “ሀዋሳ” የሲዳምኛ ቃል ሲሆን የአማርኛ አቻ ትርጓሜው “ሰፊ የውሃ አካል” ማለት ነው።
የውጭ ምንዛሬን የሚያመጡ ጎብኚዎችን በማብዛት፣ የሐገር ውስጥ ቱሪዝምን በማበረታታት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያበረከተው የፍቅር ሀይቅ አሁን ታሟል። ከፋብሪካዎች የሚለቀቁ ኬሚካሎች፣ ከከተማዋ ነዋሪዎች እና ሀይቁን ከከበቡት ድርጅቶችና ማኅበራት የሚለቀቁት ተረፈ ምርቶች የቀደመ ውበቱን በእጅጉ ቀንሰውታል። በእረፍት ቀናት እና ከስራ ሰዓት በኋላ ያለውን የምሽት ክፍለ ጊዜ ሐይቁ ዳር በመዝናናት የሚያሳልፉ የሐገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ አሽቆልቁሏል።
በተለይ በሳምንቱ የመጨረሻ ባሉ የእረፍት ቀናት ቁጥሩ የበዛውን ጎብኚ ለማስተናገድ የተደራጁ ከ5 በላይ ማኅበራት አሁን ስራ አቋርጠዋል። የጀልባ ሽርሽር፣ የአሳ ጥብስ አቅርቦት እና መሰል በሐይቁ ዙርያ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ተቋርጠዋል።
“ገበታ ለፍቅር ሀይቅ” የሀዋሳ ሐይቅን የማዳን ዓላማ ያለው የቅርብ ጊዜ ፕሮጀክት ነው። ሀይቁ የተጋረጠበትን የመጥፋት አደጋ ለመከላከል እና ከፍቅር ሀይቅ (ሀዋሳ ሀይቅ) አንስቶ እስከ ፒያሳ የሚገኘውን የእግረኛ እና የተሽከርካሪ መንገድ ማስዋብ የፕሮጀክቱ ትኩረት ነው። ከሀዋሳ ሀይቅ ተነስቶ ሐይቁን መሀል ለመሀል በማቋረጥ እስከ ሀዋሳ አየር መንገድ ድረስ እንደሚሰራ የሚጠበቀው ፕሮጀክት አምስት ዓመታት አስቆጥሯል።
አሳ አስጋሪ መሆናቸውን የነገሩን አቶ ጥላሁን ካሳ በሥራው ለይ 10 ዓመታት አስቆጥረዋል። ከ10 ዓመት በፊት በሚያውቋት ፍቅር ሀይቅ እና በአሁኗ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲህ ያብራራሉ። “ፍቅር ሀይቅ ማራኪ ገጽታ ያለው፣ ማንም ሀይቁ ዳር ውሎ ጦሙን የማያድርበት ነበር። አሁን ግን የፕላስቲክ ኮዳ እና የአሳ ተረፈ ምርት እንዲሁም ሌሎች ቆሻሻዎች ሞልተውታል። የውሃ መጠኑም እየቀነሰ ነው። አሁን ባለበት ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ መጨረሻውን ማሰብ ይከብዳል” አቶ ጥላሁን በስጋት እንደሚናገሩት የሐይቁ ጤንነት ወደነበረበት እንዲመለስ የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ መፍትሔ ካላመጣ ቀጣዩ ጊዜ አደገኛ ነው።
ፍቅር ሀይቅ አካባቢ ከምሽት 12፡00 አካባቢ ጀምሮ በመንሸራሸር ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ ለአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር የተናገሩት ወጣቶች ቃልአብ እና ቤተልሄም ይባላሉ። ጓደኛሞቹ ፍቅር ሐይቅ ቀዳሚ የመዝናኛ ምርጫቸው እንደሆነ እና ጥሩ የፍቅር ጊዜ እንዳሳለፉበት አልሸሸጉም። “የሐይቁ ሁኔታ ስጋት ውስጥ የሚጥል ነው” የሚሉት ወጣቶቹ የጥገና፣ የማጽዳት እና የማስዋብ ሥራው በቅርብ ጊዜ ቢጠናቀቅ በርካቶችን ይጠቅማል” የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል። ከዚህ በፊት እንደተጓተቱት ሐገራዊ እና ክልላዊ ፕሮጀክቶች እንዳይሆን የሚል ስጋት እንዳለባቸውም ነግረውናል።
ሀዋሳ ሐይቅ የልዩ ልዩ አእዋፋት መኖርያ ነው። በርድ ላይቭ የተባለ አእዋፋትን የሚያጠና ተቋም በአንድ ወቅት ባወጣው ሪፖርት በሀዋሳ ሐይቅ ዙርያ በሳይንሳዊ መጠሪያቸው ‘ፓይቶፕላክቶን’ የተባሉ ከአንድ መቶ በላይ የአእዋፋት ዝርያዎች እንደሚገኙ እና ‘ዞፓላክቶን’ የሚል መጠሪያ የተሰጣቸው ወደ ስድስት የሚጠጉ የዓሳ ዝርያዎች እንደሚገኙ አስቀምጧል።
አቶ በኃይሉ ሰለሞን የሀዋሳ ሀይቅ ጀልባ መዝናኛ ሁለገብ ሕብረት ስራ ማኅበር ዋና ሰብሳቢ ነው። “ሀዋሳ ሀይቅ ከዛሬ አምሳ እና አርባ ዓመት በፊት የወንጀለኞች መደበቂያ፣ የከብት አዛባ መጣያ እና የቁጥቋጦዎች መገኛ ነበር። ከጊዜው መዘመን ጋር ሐይቁ የከተማዋ የቱሪስት ዋነኛ መስህብ ሆኗል። በዚህም ለበርካቶች የሥራ እድል ፈጥሯል። ትልልቅ ሆቴሎች እና ሪዞርቶችም ተገንብተዋል። ስንጠቀምበት ነገን አስበን መጠቀም ባለመቻላችን ግን አሁን ለሚገኝበት ችግር ዳርገነዋል” ብሏል።
በከተማ አስተዳደሩ የተቀረጸው “ገበታ ለፍቅር ሀይቅ” ፕሮጀክት በታቦር ተራራ ላይ የመሰረት ድንጋዩ ተቀምጧል። ለፕሮጀክቱ መሳካት በፍቅር ሀይቅ ዙሪያ ምግብ እና መጠጥ ለማቅረብ ተደራጅተው ሥራ ላይ የነበሩ ወጣቶች እንዲነሱ ተደርጓል። በአሁን ሰዓት የሚገኝበትን ደረጃ በተመለከተ የገበታ ለፍቅር ሐይቅ ፕሮጀክት አስተባባሪዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ባለመሳካቱ ሐሳባቸውን በጽሑፉ ላይ ማካተት አልቻልንም።