ወጣት የአብሰራ ይብራ ከጓደኛዋ ጋር በመሆን 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ምሳ በልተው መውጣታቸው ነበር። ከምግብ ቤቱ ብዙም ሳይርቁ መንገድ ዳር ታክሲ በመጠበቅ ላይ ሳሉ ያብስራ የእጅ ስልኳን በሁለት ቀማኛዎች ተመንትፋ ዘራፊዎቹ በቅጽበት ከእሷም ከጓደኛዋም እይታ ተሰወሩ። ሌቦቹን ለመያዝ ያደረጉት ጥረትም ሳይሳካ ቀረ።
ይህ የባለታሪካችን ገጠመኝ የዘረፋ ስልቶቹ እየተቀያየሩም ቢሆን የብዙ ኢትዮጵያውያን በተለይም በከተማ የሚኖሩ ዜጎችን ያማረረ ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው። ይሁን እንጂ መሰል የሞባይል ስልክ ስርቆት የገጠማቸው ብዙኅኑ ተስፋ በመቁረጥ ዝምታን ይመርጣሉ፤ እንደሌሎች ወንጀሎች ለፖሊስ በማመልከት የጠፉ ንብረቶችን ማፈlላለግ አልተለመደም።
“ለ-ሞባይሌ” በተሰኘው የተንቀሳቃሽ ስልክ መድን ዋስትና ተጠቃሚ በመሆኗ የተሰረቀችውን የእጅ ስልክ ከኒያላ ኢንሹራንስ ባገኘችው ካሳ መተካት ችላለች። ወጣት ያብስራ እንደገለጸችው የተንቀሳቃሽ ስልክ መድን ዋስትና አገልግሎት አስተማማኝ አይደለም የሚሉ ሀሳቦችን ከተለያዩ ሰዎች ብትሰማም ከምንም ይሻላል ብላ መመዝገቧን ነግራናለች።
“ስድስት ወር ሆኖኛል መጠቀም ከጀመርኩ፤ መጀመሪያ ጊዜ ላይ የማውቃቸው ሰዎች የሚታመን ነገር አይደለም ስላሉኝ ትቼው ቆይቼ ነበር። ግን ከምንም ይሻላል ብዬ ከተመዘገብኩ በኋላ ስልኬን ተሰርቄያለሁ። አሁን ኒያላ ኢንሹራንስ ካሳ ከፍሎኝ አዲስ ስልክ ገዝቻለሁ።
“ለ-ሞባይሌ” የተንቀሳቃሽ ስልክ መድን ዋስትና ምንድን ነው?
“ለ-ሞባይሌ” የተሰኘው የተንቀሳቃሽ የስልክ መድን ዋስትና ኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር ከኢትዮ ቴሌኮም እና ኤስ. ዜድ. ኤም ኢንጂነሪንግ ጋር በመተባበር በወርሃ መጋቢት 2013ዓ.ም. በይፋ ስራ ላይ የዋለ፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የስልክ ዋስትና አገልግሎት ነው።
የኒያላ ኢንሹራንስ የዲጂታል አገልግሎቶች ኃላፊ አቶ ግርማ ሚልኬሳ ኩባንያው ”ለ-ሞባይሌ”የተሰኘውን አገልግሎትን ኒያላ ኢንሹራንስ የጀመረበት ዋነኛ ምክንያት ሲገልጹ እንደ ባለታሪካችን ወጣት የአብሰራ ያሉ ስልካቸውን የሚሰረቁ ሰዎች መበራከት መሆኑን ያስረዳሉ።
“የመድን ዋስትናዎች ዓላማቸው ሰዎች ለፍተው ለሚያቋቁሙትና ለሚያገኙት ንብረት ከዋስትና አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በጋራ ጥቅም ላይ ተመርኩዞ የሚሰጥ የካሳ አገልግሎት ሲሆን ይህን የመሰረቅ ስጋት ለመቀነስ የሚያስችል ተግባር ለማስጀመርም ከሶስት ዓመታት በላይ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተሰርተው “ለ-ሞባይሌ” አገልግሎትን ስራ ላይ ለማዋል ምክኒያት ሆኗል
እንደ አቶ ግርማ ገለጻ ኒያላ ኢንሹራንስ የሚያቀርበው የተንቀሳቃሽ ስልክ መድን ዋስትና የተሰረቁ የሞባይል ቀፎዎችን ለመተካት እንዲሁም ለጥገና ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቀውን የስክሪን መሰበር ለመሸፈን የቀረበ አገልግሎት ነው።
የመድን ዋስትናውን ለማግኘት የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ወደ “813” አጭር የጽሁፍ መልእክት መቀበያ ላይ “OK” በመላክ አገልግሎቱን እንደሚፈልግ ይገልጻል። ኒያል ኢንሹራንስም አገልግሎቱን ወደጠየቁት ደንበኞች ስልክ “ለ-ሞባይሌ” መተግበርን የሚያገኙበትን መስፈንጠሪያ በመላክ ከ”አፕ ስቶር” አልያም ከ”ፕሌይ ስቶር” ማውረድ ይጠበቅባቸዋል።
መተግበሪያው የሚጠይቃቸውን የደንበኛውን እና የሚጠቀመውን ስልክ ቁጥር፣ አይ.ኤም.ኢ የመለያ ና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች በማስገባት መጠይቆቹን መሙላት አስፈላጊ መሆኑን የዲጂታል አገልግሎቶች ኃላፊው ገልጸዋል።
የስልክ ዓይነት እና የዋጋ ደረጃን ኩባንያው በምን ይለያቸዋል? የክፍያ ስርዓቱስ?
የተንቀሳቃሽ ስልክ መድን ዋስትናን ለማግኘት በቅድሚያ ደንበኞች የስማርት ስልክ ተጠቃሚ መሆን እና አገልግሎቱን ለማግኘት ፍላጎታቸውን በተዘጋጀው የጽሁፍ መልእክት መላኪያ ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው ኒያላ ኢንሹራንስ ገልጾልናል።
በአሁኑ ሰዓት ኒያላ ኢንሹራንስ የመድን ዋስትናውን የሚያቀርበው በሦስት የዋጋ ተመንና የክፍያ ደረጃዎች ሲሆን እስከ 5 ሺህ ብር ለሚያወጡ የእጅ ስልኮች በቀን አንድ ብር፣ ዋጋቸው ከ5 ሺህ እስከ 10 ሺህ ለሆኑ ስልኮች አንድ ብር ከ25 ሳንቲም እንዲሁም ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር ወጪ ለተደረገባቸው ቀፎዎች ደግሞ አንድ ብር ከ50 ሳንቲም በየአእለቱ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ከደንበኛው የአየር ሰዓት ላይ ተቆራጭ የሚደረግበትን አሰራር ይከተላል።
ደንበኞች “ለ-ሞባይሌ” በተሰኝው መተግበሪያ ላይ ከሚያስገቧቸው መረጃዎች አንዱ ስልኩ የተገዛበትን ዋጋ ሲሆን ከእነዚህ ሦስት አማራጮች ውስጥ አንዱን ይመርጣሉ። የክፍያ መጠኑም በመረጡት ዋጋ መስተናገድ ይጀምራሉ።
ደንበኞች ስልካቸው ከተገዛበት ዋጋ በላይ ቢጠይቁ ለምሳሌ ዋጋው 5 ሺህ ብር የሆነ ስልክን የሚጠቀም ግለሰብ 15 ሺህ ብር ብሎ መረጃው ላይ ቢያሰፍር፤ ኩባንያው ተጎጂ አይሆንም ወይ ያልናቸው አቶ ግርማ ሚልኬሳ እስካሁን መሰል ችግሮች አልገጠሙንም ብለዋል።
በተጨማሪም የስልካቸው ዋጋ ከፍተኛ ሆኖ ነገር ግን ደንበኞች በመተግበሪያው ላይ መረጃቸውን ሲያስቀምጡ አነስተኛውን የሚለውን በስህተት ከመረጡ፤ ክፍያ ሲፈጽሙ በቆዩበት ደረጃ ልክ ነው ካሳ የሚያገኙት።
ደንበኞች አገልግሎቱን እንደሚፈልጉ ከገለጹ በኋላ ለአንድ ወር ክፍያውን ከፈጸሙ በኋላ የስልክ መሰረቅ፣ መጥፋት እና መሰበር ሲገጥማቸው በ24 ሰዓታት ውስጥ ለኢንሹራንስ ኩባንያው ማሳወቅ የግድ ቢሆንም መዘናጋቶች ይታያሉ። ይህ ክፍተት በአሰራር ላይ እንቅፋት የሚሆን ስለሆነ ደንበኞች ሊገነዘቡት እንደሚገባ አቶ ግርማ መልእክት አስተላልፈዋል።
ኒያላ ኢንሹራንስ የተንቀሳቃሽ ስልክ መድን ዋስትናን ማቅረብ ከጀመረ ዘጠኝ ወራት ተቆጥረዋል። እስካሁንም 10 ሺህ የሚደርሱ ደንበኞች የመድን ሽፋኑ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። አእስካሁን 280 የሚደርሱ ደንበኞች የካሳ ክፍያ ያገኙ ሲሆን በአእዚህም ከ800 ሺህ ብር በላይ ኩባኛው ክፍያ ፈጽሟል።
የመድን ዋስትና አገልግሎትን ለማጭበርበር አእንደምቹ ሁኔታ የሚያስቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር የሚያግዙ አሰራሮችን ኩባንያው አእየተገበረ ይገኛል። ደንበኞች ለአንድ ወር በቋሚነት አእለታዊ ክፍያውን መፈጸም ዋነኛው ነው።
ስልካቸው ሳይጠፋ ወይም ሳይሰረቅ የሚያመለክቱ ሰዎች ቀፎውን መልሰው ጥቅም ላይ ካዋሉ በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግም የፖሊስ ሪፖርት ማቀረብ ይጠበቅባቸዋል። በተጨማሪም ስልክ የጠፋባቸውና የተሰረቁ ሰዎች ለኩባንያው በ24 ሰዓት የሚያሳውበትን አሰራር በመጠቀም፤ ኢትዮ ቴሌኮም የቀፎውቹን መለያ ቁጥር በመጠቀም ከአገልግሎት የሚያግድበት አሰራር ተዘርግቷል።
10 ሺህ የደረሰው የደንበኞች ብዛት አሰፈላጊው የማሰታወቂያ ስራዎች ሳይሰሩ በመሆኑ ከተጠበቀው በላይ ነው ያሉት አቶ ግርማ ሚልኬሳ፤ በኢትዮጵያ ከ22 ሚልየን በላይ የዘመናዊ (ስማርት) የስልክ ቀፎ ተጠቃሚዎች በመኖራቸው ሰፊ ስራ ይጠበቅብናል ብለዋል።
ስማርት የስልክ ቀፎዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋቸው እያደገ መጥቷል። ገበያው ላይም ከ2 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወይም ከ90 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የስልክ ቀፎዎች ይገኛሉ።
የመድን ዋስትና ሽፋኑን እስከ 120 ሺህ ብር ለሚያወጡ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው። የክፍያ ስርዓቱ ላይም በየቀኑ የሚደረገውን ተቆራጭ የመዘንጋት ሁኔታዎች በመኖራቸው አእንዲሁም ደንበኞች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ዓመታዊ የክፍያ አሰራር ለማዘጋጀት የንድፈ ሀሳብ ስራዎች እየተጠናቁቁ ይገኛሉ።
እነዚህ በሂደት ላይ የሚገኙት አሰራሮች ሲዘረጉ በዓመት ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ሰዎችን የ”ለ-ሞባይሌ” መድን ዋስትና ተጠቃሚ ለማድረግ ኒያላ ኢንሹራንስ ራዕይ ይዟል።
የተንቀሳቃሽ እጅ ስልኮች መድን ዋስትና በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ እምብዛም የተለመደ አይደለም። በአፍሪካ የሞባይል ስልክ መድን ዋስትና በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠቀሙ ሀገራት ደቡብ አፍሪካ ተጠቃሽ ናት። አገልግሎቱ የሚሰጥባቸው ዋጋዎች ተመጣጣኝ አለመሆን እና የመድን ዋስትና ግልጋሎትን አስፈላጊነት ላይ የግንዛቤ ክፍተት መኖሩ ለስራው አለመስፋፋት ዋነኛ ምክንያት ናቸው።