ባለፈው ሳምንት በተደረገ የእስራኤል ካቢኔ ስብሰባ ላይ አሁን ለዩክሬናውያን ስደተኞች የተቸረውን ሃዘኔታና ድጋፍ ከሀገራቸው ተሰደው ለመጡ ኢትዮጵያዊ ቤተ-እስራኤላውያን ነፍጋችኋል በማለት ትውልደ ኢትዮጵያዊዋ የእስራኤል ፓርላማ አባልና የኢሚግሬሽን ሚኒስትር ፒና ታማኖ ሻታ የካቢኔ ባልደረቦቿ ላይ የሰላ ትችት ሰንዝራለች።
ሚኒስትሯ በካቢኔው ውይይት ላይ የዘር መድልዎን ጉዳይ ያነሳች ሲሆን ከዩክሬንና ከኢትዮጵያ ለመጡት ስደተኞች በእስራኤል በተደረገው አቀባበል ላይ የታየውን የዘር መድልዎ በተመለከተ ባልደረባ የካቢኔ አባላቱን “አስመሳዮች” በማለት በግልፅ ገስፃቸዋለች።
ዋይ ኔት ለተባለው የእስራኤል ሚድያ ሚኒስትሯ በሰጠችው አስተያየት፣ “እውነታው ለሁሉም በግልፅ የሚታይ ቢሆንም አንዳንዴ ሰዎች እውነቱን መስማት አይፈልጉም። እኔ ደግሞ እውነቱን ተናግሬያለሁ። ማስወገድ ያለብን በተወሰነ ደረጃ የሚታይ አስመሳይነት አለ። ለዚህ ደግሞ ብቸኛ መድሃኒቱ እያንዳንዱን ነገር ግልፅ አድርጎ ሁሉም እንዲያየው ማድረግ ነው” ብላለች።
በጦርነቱና በተለያዩ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ የሚሰደዱ ቤተ-እስራኤላውያን የኢሚግሬሽን ጉዳዮችን ለማመቻቸት የእስራኤል መንግስት መስራት እንዳለበት የጠቆመችው ሚኒስትሯ፣ “እንደ ኢትዮጵያዊ ለራሴ ማህበረሰብ እንደማገለግለው ሁሉ በዚያው ልክ ለህንድ፣ ለአሜሪካ፣ ለፈረንሳይ፣ ለሩስያ፣ እና ለዩክሬን ቤተ-እስራኤላውያን እሰራለሁ” በማለት ኃሳቧን በአፅንዖት ገልፃለች።
ጠበቃ፣ ጋዜጠኛና ፖለቲከኛ የሆነችው ፒና ታማኖ ሻታ እኤአ በ 2013 የመጀመሪያዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የእስራኤል ፓርላማ አባል መሆን ችላለች። በተጨማሪም እኤአ በ 2020 የእስራኤል የኢሚግሬሽን ሚኒስትር ሆና በመሾም የመጀመሪያዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የእስራኤል ሚኒስትር ሆናለች።
ፒና ታማኖ ሻታ ጎንደር ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ውዛማ በሚባል ቦታ የተወለደች ሲሆን እኤአ በ 1885 ኢትዮጵያዊ ቤተ-እስራኤላውያንን ወደ እስራኤል ለመውሰድ በተደረገው ኦፕሬሽን ሙሴ ከወላጆቿ ጋር በ 3 አመቷ ወደ እስራኤል ሄዳለች።