መስከረም 27 ፣ 2014

የፀጥታው ምክር ቤት ፍጥጫ በኢትዮጵያ ጉዳይ

City: Addis Ababaዜና

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት “Peace and Security in Africa” በሚል የውይይት አጀንዳ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ሁኔታ ለመምከር በትናንትናው ዕለት ክፍት ስብሰባ ተቀምጧል።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

የፀጥታው ምክር ቤት ፍጥጫ በኢትዮጵያ ጉዳይ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት “Peace and Security in Africa” በሚል የውይይት አጀንዳ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ሁኔታ ለመምከር በትናንትናው ዕለት ክፍት ስብሰባ መቀመጡ ይታወቃል። ስብሰባው በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በኖርዌይ፣ በኢስቶኒያ፣ በፈረንሳይ እና በአየርላንድ ጥያቄ መሰረት መዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን ኢትዮጵያ 7 የተመድ ሰራተኞችን ከሀገር በማስወጣቷ ጉዳይ እና የሰሜን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ሁኔታ ላይ ምክር ቤቱ ተወያይቷል።

የተመድ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣው የሰብዓዊ ጉዳይ ችግር ካለፈው ነሃሴ አንስቶ አሳሳቢ ሆኖ መቆየቱን እና እየተስፋፋ መሆኑን በመጥቀስ  በትግራይ ፣ አማራ እና አፋር ክልል 7 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እና የተለያዩ አፋጣኝ ድጋፎች እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች ውስጥም 400 ሺህ የሚሆኑት ረሃብ ተብሎ መጠራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም አንስተዋል።

“በኢትዮጵያ ያለው ችግር በቅርቡ መፍትሄ ካልተሰጠው ሁኔታው ሶማሊያ የዛሬ 10 ዓመት ገጥሟት የነበረው እና 200 ሺህ ሰው ያለቀበትን ረሃብ ሁኔታ ወደሚመስል አደጋ ሊለወጥ ይችላል” ሲሉ ያሳሰቡት ፀሃፊው በኢትዮጵያ ያሉ ወገኖች በአፋጣኝ ለሰላም እና ለድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ከሀገር ያስወጣቻቸውን 7 የተመድ አባላት በአፋጣኝ ወደስራቸው እንድትመልስ የጠየቁ ሲሆን “በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተመሰረተው አዲስ መንግስት ጥሪዬን ተቀብሎ ጠንካራዋን ኢትዮጵያ እንደሚመልስ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉን አካታች ውይይት ለማድረግ ለገቡት ቃልም ምስጋና አቅርበዋል።

በአንቶኒዮ ጉተሬዝ በተነሱት ነጥቦች  ላይ ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ የሀገራት ህግ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት ለውሳኔው ምንም አይነት ማብራሪያ እና ማረጋገጫ የማቅረብ ግዴታ የለበትም በማለት “ሌሎች ሀገራት የተለያዩ የተመድ ሰራተኞችን እና የሀገራት ዲፕሎማቶችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሀገራቸው ማስወጣታቸውን እናውቃለን፤ ነገር ግን ተመድ በእነሱ ላይ ስብሰባ አድርጎ የሚያውቀው መቼ ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

አክለውም የተመድ ሰራተኞች የገለልተኝነት መርሆችን በጣሰ መልኩ ለህወሓት የሚወግኑ መሆናቸውን ሲገልጹ ሰራተኞቹ ያልሞቱ ሰዎችን በረሃብ ሞተዋል የሚል የሀሰት መረጃዎችን ማሰራጨት፤ የመገናኛ መሣሪያዎችን ለህወሓት ወገን ማድረስ፤ ህወሃት መቀሌ ሲገባ ከቡድኑ ጋር ደስታቸውን መግለጽ፤ ከሳዑዲ የትግራይ ተወላጆችን ወደ ሶስተኛ ሀገር በማምጣት ለቡድኑ እንዲዋጉ ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ህወሓትን የሚደግፉ ጹሑፎችን ማዘጋጀት ላይ ተጠምደው ነበር፣ ሆኖም በአንድ ሀገር ውስጥ ማን ይግባ፤ ማን ይውጣ ፣ እና ማን ይቆይ የሚለው የሀገር መሰረታዊ ሉዐላዊ መብት ነው ብለዋል።

አንቶኒዮ ጉተሬዝ በአምባሳደሩ ምላሽ ላይ ተንተርሰው ባነሱት ነጥብ ከኢትዮጵያ ጋር የተዋጣ ግንኙነት እንዲኖር ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን እና አሁንም እንደሚያደርጉ በማውሳት  “እንደውም ለኢትዮጵያ መንግስት ታደላለህ በሚል ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲወቅሱኝ ቆይተዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

አክለውም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን ድረስ ለተመድ የገባ ደብዳቤ የለም፤ ስለክሱም የማውቀው ነገር የለም በማለት ጉዳዩን በተመለከተ በፅሁፍ የተዘጋጀ ሰነድ ካለ እንዲቀርብላቸው ለጠቅላይ  ሚኒስትር አብይ አህመድ ሁለት ጊዜ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልፀው  ኢትዮጵያ የተመድ ባለስልጣናት እና ሰራተኞቹን ያለምንም የጥፋት ማስረጃ የማባረር መብት የላትም በዚህም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግ ጥሳለች ብለዋል። ይሁን እንጂ ማንኛውም የተመድ አባል ከስነ ምግባር ውጭ ያደረገው ጥፋት ካለም ሀገሪቷ እርምጃ ከመውሰዷ በፊት በቂ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባታል ሲሉ ተናግረዋል።

አምባሳደር ታዬም ለቀረበው የሰነድ ይቅረብልኝ ጥያቄ በአፋጣኝ ሰነዱን ለማቅረብ እንደሚሰሩ አጠር ያለ ምላሽ በመስጠት ከዚህ በኋላ ውይይቶች መከናወን ያለባቸው በኢትዮጵያ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መካከል ብቻ እንዲሆን ጠይቀዋል። ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ላሳየው ትብብርም አመስግነዋል።

የቻይና ተወካይ ምን አምባሳደር ዣን ጁን በተነሱት ነጥቦች ላይ በሰጡት ሃሳብ ተመድ እና የተመድ ሰራተኞች ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርሱ የተቋሙን መርህ ተከትለው ሊሆን ይገባል ብለዋል። አክለውም አሁንም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለኢትዮጵያ መንግስት ሊያቀርቡ እንደሚገባ በመግለፅ የኢትዮጵያ መንግስትም ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ድጋፎችን ለማድረስ ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ ላለው ስራ ቻይና እውቅና ትሰጣለች ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተወካዩ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ ቅድሚያ በመስጠት ወደ ሀገር ለሚገቡ ሰራተኞች የቪዛ ሂደቶችን ማቅለሉን፣ የፍተሻ ጣብያዎች ቁጥርን መቀነሱን እና የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኞች አስፈላጊውን የተግባቦት መሳሪያ እንዲያስገቡ መፍቀዱን  በማውሳት ቻይና አዲስ ለተመሰረተው መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልፀው ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ይህንን እንዲያድርግ ጠይቀዋል። አክለውም አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ የተናጠል ማዕቀብ ለመጣል ማሰባቸው ዓለም አቀፍ ህግን መጣስ መሆኑን በማስታወቅ የተጣለው ማዕቀብ በአስቸኳይ ሊነሳ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የሩሲያ ተወካይ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዝያ በበኩላቸው በተናጠል የሚወሰዱ የማዕቀብ እርምጃዎች ችግሩን እንደሚያባብሱ በመግለጽ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ሆኖም ሀገራቸው ለኢትዮጵያ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል በመግለጽ በሀገሪቱ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ቀዳሚ መሆን ያለበት የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘበው ይገባል፣ ሆኖም ቀውሱን ለማስወገድ የተቀናጀ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

የአሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ በጉዳዩ ላይ ሀሳብ ሲሰጡ የኢትዮጵያ መንግስት የተመድ ሰራተኞችን ከሀገር የማስወጣቱ  እርምጃ አሳሳቢ ነው በማለት ኢትዮጵያ ይህንን ላደረገችበት ምንያት ምንም አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ አትችልም ሲሉ አጣጥለዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔውን ሊቀለብስ እንደሚገባ እና በጦርነቱ ላይ የተካፈሉ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አጠቃላይ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በመጠየቅ ይህ የማይሆን ከሆን ግን የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በአፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ  አሳስበዋል።

ተወካይዋ ከስብሰባው በኋላ በሰጡት መግለጫም  “የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃ በምክር ቤቱ ላይ፣ በአባል መንግስታት ላይ እና በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች አቅርቦት ላይ የተፈፀመ ድፍረት ነው” በማለት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ላይ እያደረሱ ያሉት ጉዳት መሆኑን ተናግረው የሀገሪቷ መሪዎችም ህዝቡን ችላ ብለውታል ሲሉ ወንጅለዋል።

አክለውም “ከ3 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተስፋ ሰጪ ሀገር ትሆናለች ብለን ተስፋ አድርገን ነበር የዛሬ ዓመት አካባቢ ግን ለ2 ሳምንት ተብሎ የተጀመረው የህግ ማስከበር እርምጃ ተራዝሞ አሁን ያለበት ደርሷል” ሲሉ ተደምጠዋል።

በተጨማሪም በስብሰባው ላይ ብሪታኒያ ፣ኢስቶኒያ ፣አየርላንድ ፣ ፈረንሳይ እና ኖርዌይ ኢትዮጵያ የተመድ ሰራተኞችን ማባረር አልነበረባትም ያሉ ሲሆን ፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሁሉን አካታች ውይይት ለማስጀመር ለወሰዱት ኃላፊነት ድጋፍ አለኝ ብላለች።

ይህ ስብሰባ የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ከተደረጉት ስብሰባዎች መካከል አስረኛው ነው።

አስተያየት