መስከረም 22 ፣ 2014

አባ ቦኩ እና ሀዳ ሲንቄ በገዳ ስርዓት ውስጥ

City: Addis Ababaባህል ታሪክ

"ገዳን ባርክ አምላክ አምላክ ገዳን ባርክ... ጊደሩን አርባ ኮርማውን አስባ ምድሪቱን አፅድቅ ጠላትን አድቅቅ" (ጸጋዬ ገ/መድኅን)

Avatar: Naol Getachew
ናኦል ጌታቸው

Naol is a journalist and fact-checker at Addis Zeybe for HaqCheck. He is a professional working in the fields of fact-checking, journalism, online storytelling, and translation.

አባ ቦኩ እና ሀዳ ሲንቄ በገዳ ስርዓት ውስጥ

ኦሮሞ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ከሚኖሩ ህዝቦች በቁጥር ትልቁ ብሔር ሲሆን፤ በደቡብ፣ ማዕከላዊ፣ ምስራቃዊና ምዕራባዊ ኢትዮጵያ የተንሰራፋና የብዙ ባህሎችና እሴቶች ባለቤት የሆነ ሕዝብ ነው።

ይህም ህዝብ የራሱ የሆነ የአስተዳደር ስርዓት ፣ የጊዜ መቁጠሪያ ካሌንደር ፣ የሃይማኖታዊ ስርዓትና ትውፊት ፣ የልጆችና የወጣቶች ጫዎታዎች ፣ የጦርነት ስልቶች ፣ የእርቅና የሽምግልና ስርዓቶች ፣ የሃዘንና የደስታ አገላለፅ ፣ የዘፈንና የጭፈራ እንዲሁም የአለባበስ ባህሎችና ደንቦች አሉት። 

ኦሮሞ በጥንታዊው የእናቶች አስተዳደርና ገዳ ስርዓት ሲተዳደር ኖሯል። ስለዚህ አስተዳደር ድሪቢ ደምሴ 'የኦሮሞ የማንነት ታሪክ' በሚለው መፅሀፋቸው እንዲህ ብለው ጽፈዋል።

"በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ የኦሮሞ ሽማግሌዎች ብዙ የሴት መሪዎች (Motittii) እንደነበሩ በተረት ስለሚናገሩ ፤ ይህ ተረት ያለምክንያት አልተነገረም ብዬ ስላመንኩ ከመሀል ኦሮሚያ የአምስት፣ ከጉጂ ደግሞ የአራት የኦሮሞ የሴት መሪዎችን ስም እንደሚከተለው አቀርባለው። እነርሱም፡- የመጫዋ ንግስት ሀdha ሦንኮሮ፣ የቱለምዋ ንግስት አኮ መኖዬ፣ የኢቱ ሁምበና ንግስት ሞቴ ቆርኬ፣ የቦረናዋ ንግስት ሀdha አባኖዬ እና የከረዩ ንግስት አኮ መኖዬ ሲሆኑ የጉጂ ኦሮሞ ንግስቶች ደግሞ አኮ ቀሮዬ ገሮዬ፣አኮ ለሲ ለሶዬ፣ አኮ ቀዶ ቀሶዬ እና አኮ መኖዬ ናቸው።"

ኦሮሞ ለዘመናት ለአስተዳደር የሚጠቀምበትና የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔሰኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት ያሰፈረው የገዳን ስርዓት ። የገዳስርዓት የማህበረሰብ ባህልና እምነትን ማዕከል ያደረጉ ዝርዝር አስተዳደራዊ መዋቅሮችን አካቶ መያዙን በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይገልፃሉ።
ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን The Oromo of Ethiopia: A History 1570-1860 በሚለው መፅሐፋቸው "በቋንቋው ተናጋሪ ዘንድ ገዳ የሚለው ቃል ሰፊ የሆነና የጠነከረ ትርጓሜ አለው።" ይላሉ። እንደ መሐመድ ሐሰን ገለፃ ኦሮሞ ገዳ ሲል ጊዜን ለመግለፅ Gaafa Gadaa kami? (በየትኛው ገዳ?) ፣ ባስልጣን ለመግለፅ Inni Gadaa (እሱ ገዳ ነው) ፣ እንዲሁም ሌሎች አገላለፆችን ማለትም Gadaa nagayaa (የሰላም ገዳ) ፣ Gadaa quufaa (የጥጋብ ገዳ ) ፣ Gadaa lolaa (የጦር ገዳ) ወዘተ ለማለት ይጠቀምበታል። 

ገዳ ከጥንታዊና ቀደምት ድንቅ የዓለም ዴሞክራሲያዊ ከሚባሉ ስርዓቶች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነ ስርዓት ሲሆን ህዝቡ ዕውቀትንና መረጃን በዋናነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ካስተላለፈባቸው ተቋማት ውስጥ (ቤተሰብንና ሃይማኖትን ጨምሮ) ዋነኛው እንደሆነ ዶ/ር አሰፋ ጃለታ Gadaa (Oromo Democracy): An Example of Classical African Civilization በተባለው ፅሁፋቸው ላይ አስፍረዋል። 

ሌላው የገዳ ስርዓት ያለው ግሩም ነገር "ቼክ ኤንድ ባላንስ" ነው። አስተዳደሩ የተሰጠውን ስልጣን ያለመጠን እንዳይጠቀምና ተጠያቂነት እንዲኖረው የሚያደርግን "የማመዛዘን፣ የመከታተልና ተጠያቂ የማድረግ" ስርዓትን ዘርግቷል። ይህንን አስመሮም ለገሰ (ፕ/ር)  Gadaa: Three Approaches to the Study of African Society በተሰኘ መፅሐፋቸው ላይ ንዲህ"ስለባህሉ የሚደንቀው ነገር … የቼክ እና ባላንንስ ስርዓትን በምዕራባውያኑ ዴሞክራሲ ውስጥ እንደምናገኘው ሁሉ ቀምረውታል።" ሲሉ ገልፀውታል። 

በገዳ ስርዓት ውስጥ አባ ቦኩ መሪ ነው ፤ የከፍተኛ ስልጣን ባለቤት። ልክ እንደ አሜሪካውያን ፕሬዝደንት የሚያስተዳድረው ከ8 ላልበለጠ ዓመት ነው። ከ8 ዓመት በኋላ ለሌላ ተመራጭ አባ ቦኩ ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ ያስተላልፋል።

አባ ቦኩ የሚመረጠው ከቀደምት ጎሳዎች ቀደምት ዘሮች ሲሆን የገዳ ቡድን አባል የመሆኑ ጉዳይ ከጥያቄ የሚገባ አይደለም። አባ ቦኩውና የአባቱ ስም ቤት መምታትና የህብረተሰቡን ሃሳባዊ እሴት መግለፅ አለበት።ይህም የሆነው ማህበረሰቡ ለስም ስያሜ (ሞጋሳ) ትልቅ ቦታ ስለሚሰጥ ነው።

ልክ እንደ አብዛኛው የሀገራችን ባህሎች አባ ቦኩው ለመመረጥ ሚስት ማግባትና ልጆች ሊኖሩት ግድ ነው። በተጨማሪም እርሱ ፣ቤተሰቡና ዘመዶቹ ሁሉ ከየትኛውም አይነት ማህበረሰቡ ወንጀል ነው ብሎ ከተስማማባቸው ወንጀሎች ነፃ መሆንና የጥሩ ስም ባለቤት መሆን አለባቸው። የቅርብ ዘመዶቹ በህይወት ሊኖሩና ቤተሰቡ በሞት አለመጎብኘት አለበት። በጤናው በኩል ደግሞ ጤነኛና ቆዳው ከማንኛውም ቁስለትና ጠባሳ የፀዳ ሊሆን ይገባል።

በሆራ ላይ የሚሰበሰቡት የገዳ ቡድን (ጨፌ) አባላት ያንን ምሽት በተለያዩ ጎሳዎች ውስጥ ስላሉና መስፈርቶቹን ስለሚያሟሉ ሰዎች ከተወካዮች መረጃን ያሰባስባሉ። ከዚያም ተመራጩ በሌለበትና እሱ ባላወቀበት ሁኔታ ይመረጣል። በሆራ በስብሰባውም ላይ ወደ ተመረጠው አባ ቦኩ በመሄድ ሹመቱን አብስረው የተለያዩ ስጦታዎችን የሚሰጡት አባ ሙዳና ካቢኔዎቹ (Miseensa) ይመረጣሉ። 

በሚሰጠው የስጦታ ዓይነትና እያንዳንዱ አባል ለስጦታው ምን ያህል እንደሚያዋጣ በዚሁ ስብሰባ ላይ ውሳኔ ይተላለፋል። ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ “History of the Sayyoo Oromoo of Southern Wallaga, Ethiopia from about 1730 to 1886” ብለው በ1984 እ.ኤ.አ ባሳተሙት መፅሃፋቸው ላይ ለአባ ቦኩው ስለሚሰጠው ስጦታዎች እንዲህ ብለው ነበር፡-

”አባ ሙዳና ካቢኔዎቹ (ሚሴንሳው) ወደተመረጠው አባ ቦኩ ቤት የተለያዩ ስጦታዎችን ይዘው ይሄዳሉ። ስጦታውም ግመልና አገልጋይ ሴትን ያካትታል።”

የገዳ ስልጣን ሽግግር በሚደረግበትም ቀን (በዓለ ሲመት) ኮርማ ይታረዳል፤ አባ ቦኩው የእንስሳቱን ደም ይቀባል። በ“ከለቻ” (Kallacha) (ከለቻ አባ ገዳው ግንባሩ ላይ የሚያደርገው ነው) እና በ“ሜዲቻ” (Meedhicha) ይዋባል። በበዓለ ሲመቱም ላይ ስልጣን አስረካቢው አባ ገዳ ሥልጣን ተረካቢውን እንዲህ እያለ ይመርቀዋል፡-

‹‹እኔ ገዳ ሰጥቼሃለው ፤ገዳው የልማት ይሁን!

ባህልን አሳድጌያለው፤ያንተ ማሳደግ ደግሞ ከኔ ይብለጥ!

ስምህ ከኔ ስም ይብለጥ!

የኔ ገዳ ጥጋብ ነበር ያንተ፤ ከኔ ይብለጥ!

……ያንተ ገዳ ወጣቶች ከኔ ገዳ ወጣቶች ይብዙ!"

በገዳ ስርዓት ውስጥ አባ ቦኩ ጦር እንዲይዝ አይፈለግም፤ ሀገሪቷ ሰላም የምትሆነው ይህ ሲሆን ነው ብሎ ያምናል ማህበረሰቡ።ከዓመት እስከ ዓመት ለምለም ከሆነ ዛፍ (በአብዛኛው ከ'ዋዴሳ' ዛፍ) የተሰራ ቦኩ (በትረ ስልጣን) ሁልጊዜ ይይዛል።

አባ ቦኩ ውሃ መጠጣት አይፈቀድለትም ። በምትኩ ወተት ፣ የወተት ተዋፅዎችን ፣ ጠላና ጠጅ ይጠጣል። በመንገድ ላይ ሲጓዝም ለምለም ሳር በቀኝ እጁ ካልያዘ በስተቀር ወንዞችንና ጅረቶችን አያቋርጥም።

ዛፍ መቁረጥ፣ መሬት መቆፈርና ማረስም አይፈቀድለትም። በተጨማሪም ወደ ጦርነትና ወደ አደን አይሄድም። ከዚህም ባሻገር የበግ ስጋ መብላትን ጨርሶ የማቆም ባህላዊና እምነታዊ ግዴታ አለበት። በቤቱ ውስጥም እሳት በቀጣይነት ሳይጠፋ ይነዳል። የግቢውና የመኖሪያ ቤቱ በር ሁልጊዜም ክፍት ይሆናል። በስልጣን ላይ ሆኖ በሚቆይባቸው ስምንት አመታትም በቤቱ ውስጥ ምግብና መጠጥ ተትረፍርፎ ይኖራል። 

የማያቋርጥ የእንግዳ ጅረትም (ከተለያዩ ስጦታዎች ጋር) ወደ ቤቱ ይፈሳል። በዚህም የተነሳ አባ ቦኩው ከቤት የሚወጣበት ጊዜ ውስን ነው። አባ ቦኩ መሳቅም ሆነ ማዘን አይፈቀድለትም። በየእለቱ የሚደረገው የፀሎትና የግብዣ ስነ-ስርዓትም የሚከናወነው በቤቱ ነው።

ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኀን "እሳት ወይ አበባ" በተሰኘው የስነ ግጥም ስብስብ ውስጥ እንዲህ ብለው ስንኝ ቋጥረው ነበር፦

"ገዳን ባርክ አምላክ 

አምላክ ገዳን ባርክ...

ጊደሩን አርባ

ኮርማውን አስባ

ምድሪቱን አፅድቅ

ጠላትን አድቅቅ"