ግንቦት 15 ፣ 2014

በአብዛኛው የሀገሪቱ የመንግስት ሆስፒታሎች የማደዘንዣ መድኃኒት እጥረት የፈጠረው ችግር

City: Addis Ababaጤናወቅታዊ ጉዳዮች

በአብዛኛው የመንግስት ህክምና ተቋማት እጥረት የተፈጠረበት የማደንዘዣ መድኃኒት ከዛሬ ግንቦት 15 ቀን ጀምሮ በሚገቡት መድኃኒቶች እጥረቱ እንደሚፈታ አቅራቢው ገልጿል

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

በአብዛኛው የሀገሪቱ የመንግስት ሆስፒታሎች የማደዘንዣ መድኃኒት እጥረት የፈጠረው ችግር
Camera Icon

ምንጭ- የጤና ሚኒስቴር

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመንግስት የጤና ተቋማት አልፎ አልፎም በግል የጤና ተቋማት የሰመመን ሰጪ /በተለምዶ ማደንዘዣ/ መድኃኒቶች እጥረት መከሰቱ ተገልጿል።

አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው በተለያዩ የመንግስት ህክምና ተቋማት የሚሰሩ ባለሙያዎች እንዲሁም በማህበራዊ ትስስር ገፆች የራሳቸውን ትዝብት ያካፈሉ ባለሙያዎች የተከሰተው የማደንዘዣ መድኀኒት እጥረት በስራቸው ላይ መጉላላት እየፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል። 

ታካሚዎችም በእጥረቱ ሳቢያ ለእንግልት የተዳረጉም አሉ። ጥቂት በማይባሉ የመንግስት ሆስፒታሎች በማደንዘዣ መድኀኒት እጥረት ምክንያት መደበኛ የኦፕሬሽን (የቀዶ ህክምና) አገልግሎት ማቆማቸውን ባለሙያዎች በተለያዩ መንገዶች አስፍረዋል። 

አዳማ፣ ሞጆ እና አሰላ ከተማዎች በአዲስ ዘይቤ ምልከታ የተደረገባቸው ሲሆን ከፍተኛ እጥረት እና ጊዜያቸው ያለፈባቸው የሰመመን መድኀኒቶች መኖራቸውን መታዘብ ተችሏል። ለሜሳ ኃይሉ በአዳማ ከተማ በግል ሆስፒታል ውስጥ በሰመመን መድኀኒት ባለሞያነት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን በስራቸው ላይ የገዘፈ ችግር ባይፈጥርም የማደንዘዣ መድኀኒት እጥረት መኖሩን ገልጿል። ባለሙያው “በእዚሁ ሁደት ከቀጠለ በህክምና ስራችን ላይ ችግር ማምጣቱ የማይቀር ነው” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። 

ከአዳማ ከተማ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሞጆ ከተማ የሚገኘው ሞጆ ሆስፒታል ለከተማውና በዙሪያው ላሉ አካባቢዎች አገልግሎት የሚሰጥ የህክምና ተቋም ነው። በሞጆ ሆስፒታል የአገልግሎት ጊዜያቸው ካለፈ አንድ ወር ያስቆጠሩ የማደንዘዣ መድኀኒቶች መኖራቸውን በሆስፒታሉ ከሚሰሩ ባለሙያዎች ማረጋገጥ ተችሏል። 

አዲስ ዘይቤ ያናገረቻት አንድ ባለሙያ ማደንዘዣ መድሃኒቶቹ ገበያ ላይ ባለመገኘታቸው ከሌሎች ሆስፒታሎች ለማግኘት ጥረት መደረጉን ያስታወሰችው ባለሞያዋ ማግኘት እንዳልተቻለ ትናገራለች። 

"እስካሁን የገጠመን ችግር የለም የማደንዘዣ መድሃኒቶቹ ጊዜያቸው ቢያልፍም እንደመጠባበቂያ ይዘናቸዋል።" የምትለው ባለሞያዋ በቶሎ መድሃኒቶቹ ካልተዘጋጁ በቀጣይ አስቸጋሪ የጤና ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ስትል ስጋቷን ትናገራለች" ብላለች።

በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታልም በተመሳሳይ ስጋቶች አሉ። የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አለፍ አህመድ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት የተወሰነ ውስን ክምችት አለ እስካሁን የህክምና ስራውን አላስተጓጎለም፤ ነገር ግን ወደፊት እጥረት ሊከሰት ይችላል። 

የአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ዘጋቢ ከአካባቢው በሰበሰበው መረጃዎች መሰረት በአማራ ክልል ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል፣ እንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል እንዲሁም ሉማሜ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ላይ ከፍተኛ እጥረት መኖሩን አረጋግጧል።

በተለይም የሉማሜ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. እንዳስታወቀው “የሰመመን መድኀኒት በሀገር አቀፍ ደረጃ እጥረት ስለገጠመና በግዥ ማሟላት ስላልተቻለ ግብዓት እስከሚሟላ ድረስ የአንስቴቲስት ባለሙያዎች ከግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ከትርፍ ሰዓት ስምሪት ወጪ እንዲሆኑ አሳስባለሁ” ብሏል። 

በአዲስ አበባ ምኒሊክ ሆስፒታል የሚሰሩ አንድ የህክምና ባለሙያ የህክምና መረጃዎችን በሚያቀርበው 'ሀኪም' የተባለ የፌስቡክ ገፅ እንዳሰፈሩት በማደንዘዣ መድኀኒቱ እጥረት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎች በተራዘመ የኦፕሬሽን ቀጠሮ እየተጉላሉ ይገኛሉ። 

ባለሙያው በተጨማሪም “እነዚህን መድሃኒቶች ለጤና ተቋማቱ ገዝቶ ማቅረብ ያለበት መስሪያቤት ይህንን ችግር እስቀድሞ በመረዳት ዝግጅት በማድረግ ማቅረብ ነበረበት፤ ኣላደረገም” ሲሉ ሀሳባቸውን ገልፀዋል። 

በሐዋሳ ከተማ በሚገኘው በአዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል ፋርማሲስት የሆነዉ አብርሃም ያለዉ እንደዚህ ቀደም ባይሆንም አሁን ላይ  የማደንዘዣ እጥረት መኖሩን ተናግረዋል። "እንደሀገር የተከሰተዉ እጥረቱ በተለይ በተገቢዉ መንገድ ጥቅም ላይ ሳይዉሉ ቀናቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል የማደንዘዣ መድኃኒት አንዱ ነዉ" በማለት አብርሃም ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

አሰላ ከአዳማ በ100 ኪሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። በአሰላ ከተማ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ስር የአሰላ ሆስፒታል ይገኛል። ሆስፒታሉ አርሲን ጨምሮ ለባሌ ዞኖች የሪፈራል አገልግሎት ይሰጣል።  ሆስፒታሉ በአሁን ወቅት ለሰራተኞቹ በገበያ ላይ የማደንዘዣ እጥረት በመኖሩ ማደንዘዣ መድሃኒቶቹን ሲጠቀሙ በጥንቃቄ እና ቅድሚያ ለሚገባው ቅድሚያ እየሰጡ እንዲሆን መልዕክት ማስተላለፉን በሆስፒታሉ የማደንዘዣ ባለሞያ የሆነችው ሜሮን ለአዲስ ዘይቤ ገልጻለች።

"አሁን ላይ የገጠመን ችግር የለም። ከዚህ ቀደም የነበረ ክምችት በመኖሩ አልተቸገርንም።" የምትለው ሜሮን ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ ድንገተኛ ቀዶ ጥገናዎችን ሊቆሙ እንደሚችሉ ትናገራለች።
አቶ ተዓምር ጥላሁን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ድርጅት የአዳማ ቅርንጫፍ ስርጭት ኃላፊ ናቸው። እጥረቱ መኖሩን ያረጋገጡት  ኃላፊው "እጥረቱ የተፈጠረው ሰክሳሚቶኒየም (Suxamethonium) የተባለው ማደንዘዣ ኤክስፓየርድ በማድረጉ ነው።" ሲሉ ነግረውናል። ችግሩን ለመፍታት ከውጭ ሀገር ለማስገባት እየተሞከረ እንደሆነም ነግረውናል።

በመሆኑም መድሀኒቱን ከሚመረትበት ሀገር በዘላቂነት በማስመጣት እንዲሁም  አሁን የተፈጠረውን የአቅርቦት መቆራረጥ ችግር በአስቸኳይ ለመቅረፍ በአየር ትራንስፖርት   ከጎረቤት ሀገር  ለማስገባት እየተሰራ ሲሆን በዚህ ሳምንት ውስጥ  እጥረቱ ለተከሰተባቸው ጤና ተቋማት እንዲሰራጭ እናደርጋለን  ብለዋል። 

በተጨማሪም በየቅርንጫፎቹ ያለዉን ክምችት ወቅታዊ መረጃ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚያቀርብ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ገልጿል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት 1 ሺህ 20 ዓይነት መሠረታዊ የሆኑ መድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያዎች እና ኬሚካሎችን ወደ ኢትዮጵያ ያስመጣል። ከእነዚህ ውስጥ 262 የሚሆኑት መሠረታዊ መድኃኒቶች ሲሆኑ የማደንዘዣ መድኃኒት ዋነኛው ነው።

የአገልግሎቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት "የማደንዘዣ መድኃኒት ዓይነቶች በርካታ ሲሆኑ መጥፋት የለባቸውም የሚባሉት 12 ናቸው። ከእነዚህ 12 ውስጥ አንዱ ሌላኛውን መተካት የሚችሉ ናቸው። ነገር ግን ሲተካኩ ተመሳሳይ ምጣኔ አይደለም ያላቸው።"

ሱክሳሚቶኒየም (Suxamethonium) ከሚባለው የማደንዘዣ መድኃኒት በስተቀር 11ዱ በቂ ክምችት አለ። 

ሱክሳሚቶኒየም የተባለው መድኃኒትን ለኤጀንሲው የሚያቀርበው አንድ ድርጅት ብቻ መሆኑ ዋነኛው ተግዳሮት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት መድኃኒቶች አራት እና ከዚያ በታች የሆነ አቅራቢ ነው ያላቸው። 

"በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ትልቁ ተግዳሮት ዝቅተኛ የአቅራቢዎች ቁጥር መኖር ነው። እንደ ሱክሳሚቶኒየም ያሉ መድኃኒቶች አንድ አቅራቢ ብቻ ነው ያላቸው። ያ አቅራቢ ከሌለ እጥረት ይፈጠራል።" ሲሉ አቶ ሰለሞን ንጉሴ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ እና በመላው ዓለም ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሌሎች መንስኤዎች ሆነዋል። 

እንደ የአገልግሎቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴ ገለጻ ከሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ሳምንት ውስጥ በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ የመንግስት ሆስፒታሎች ለሁለት ወራት የሚያቆይ 37 ሺህ 500 በላይ የሱክሳሚቶኒየም ማደንዘዣ መድኃኒት ወደ ኢትዮጵያ ይገባል። በቀጣዮቹ ሶስት ሳምንታት ደግሞ ለአንድ ዓመት ከአራት ወራት የሚያቆይ ክምችት ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል። 

አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘይቤ የሰጡ ባለሙያዎች ዘላቂ መፍትሔውን በተመለከተ የመድኃኒት አቅራቢዎችን ብዛት መጨመር፣ በእጥረት ሳቢያ የሚፈጠረውን የኮንትሮባንድ ንግድ መቆጣጠር እንዲሁም በፍራንኮ ቫሉታ ወይም ግለሰቦች እጃቸው ላይ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ መድኃኒቶችን እንዲያስገቡ መክረዋል።

አስተያየት