ጎንደር ለሱዳን ድንበር ከመሆኑ አኳያ ከወደ ሱዳን ለሚመጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች መተላለፊያ ለመሆን ተጋላጭ ነው። በህጋዊነት ግብር እየከፈሉ የሚነግዱ ነጋዴዎች እንዳሉ ሁሉ በህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ስራ ላይ የሚሳተፈው ህገወጥ ሃይል እየጨመረ መምጣቱና በህገወጦች ላይ ያለው ቁጥጥር አናሳ መሆን ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።
ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ህጋዊ የንግድ ስርዓቱን እያዛባ መሆኑን ሰምተናል። ኮንትሮባንድ ንግድ የሃገር ውስጥ ገቢ እንዳይረጋጋ ህጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ ውጭ እንዲወጡ ከማድረግም ባሻገር መንግስት ከህጋዊ ንግዱ ማግኜት የነበረበትን ቀረጥና ታክስ እንዲያጣ እያደረገ እንደሚገኝ ይነገራል።
የጎንደር ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ ሃላፊ የሆኑት አቶ ወንድሙ አዲስ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ በዘንድሮው 2014 ዓ.ም 11 ሚሊዬን 613 ሺ 144 ብር የሚያወጣ የኮንትሮባንድ እቃ መያዛቸውን ነግረውናል።
አብዛኛዎቹ እቃዎች ከሱዳን መስመር ወደ ጎንደር (ከሃገር ውጭ ወደ ሃገር ውስጥ) የሚገቡ ናቸው ያሉት አቶ ወንድሙ የባጃጅ ኩሽኔታ፣ አልባሳት፣ ኤሌክትሮንኪስ እቃዎች፣ የእርዳታ ስንዴዎች እና የጦር መሳሪያዎች ይዘወተራሉ ብለውናል።
የጎንደር ጉሙርክ መቅረጫ ጣቢያ ኢንተለጀንስና ኮንትሮባንድ መከላከል ቡድን አስተባባሪ አቶ ላቀው ምህረት በበኩላቸው ባለፈው ዓመት 8 ሚሊዬን ብር የሚያወጣ የኮንትሮባንድ እቃ መያዛቸውን ገልጸው በዘንድሮው 2014 ዓ.ም 11 ሚሊዬን ብር በላይ መሰብሰብ መቻላቸውን ነግረውናል።
አዲስ ዘይቤ የጎንደር ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያን መረጃ ይዛ የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ዋና ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረውን ጠይቃለች። እንደ እሳቸው ገለጻ በዘንድሮው ዘጠኝ ወራት ውስጥ 2 ሚሊዬን 65 ሺህ 852 ብር በላይ የሚያወጡ እቃዎችን መያዛቸውን ነግረውናል።
ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ እና ጎንደር የሱዳን ጠረፍ ከመሆኗ አንጻር በርካታ የጦር መሳሪያ ንግድ እና የህገወጥ የሰዎች አልባሳት ንግድ እንደሚዘወተር ገልጸው በዘንድሮው አመት ብቻ 132 ሰዎችን ይዘው በፍርድ ቤት ሂደት ውስጥ እንዳሉ ገልጸውልናል።
በህጋዊነት እና በታማኚነት የሚነግዱ ነጋዴዎች እንዳሉ ሁሉ በህገወጥ መንገድ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉና ሃገርን ለከፋ የኢኮኖሚ ድቀት ሊዳርጉ የሚችሉ ምርቶችን ከሃገር ውጭ ወደ ሃገር ውስጥ እያስገቡ የሚያዙ በርካቶች ናቸው የሚሉት ኮማንደር ዋለልኝ ስንሰለቱ ረጅም የሆነው ይሄ የኮንትሮባንድ ንግድ ከተራ ግለሰቦች እስከ ከፍተኛ ባለስልጣናት ድረስ ሊሳተፉ ይችላሉ።
የኮንትሮባንድ ንግዱ ጥቁር ገቢያን በማስፋት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በመፍጠር የሃገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን እያዳከመ ይገኛል። በሃገር ውስጥ የተመረተውን ምርት ገቢያ በመሻማት አጠቃላይ የንግድ ስርአቱን ፍትሃዊነት እንዲያጣ ማድረጉና መንግስታዊ አሰራሩ በሙስና እንዲዘፈቅና ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዳይነግስ እንቅፋት መፍጠሩን ነግረውናል።
በኮንትሮባንድ ንግድ የሚገቡ እቃዎች የገቢ ደረሰኝ ስለማይቆረጥላቸው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መሰብሰብ እንዳይችል በማድረግ አሉታዊ ሚና እያሳረፈ መሆኑ እና የጎዳና ላይ ገበያ እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ገልጸዋል።
በሰሜኑ ያለው ጦርነት ከጀመረ ወዲህ የተደራጀ የሲጋራና ሺሻ ንግድ፣ ለሃገር ደህንነትና ሰላም አደገኛ የሆኑ መሳሪያዎችን ጭምር በፍተሻ ጣቢያ የመያዛቸው ጉዳይ የእለት ተዕለት ልምድ እየሆነ መምጣቱን ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ነግረውናል።
አዲስ ዘይቤ ከኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ጋር የነበራትን ቆይታ ከጨረሰች በኋላ በከተማዋ የሚኖሩ ነዋሪዎችን ሃሳብ ልትቀበል ስትንቀሳቀስ አቶ ባሻ አስናቀውን አገኜች።የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው። እንደ እሳቸው ገለጻ በኮንትሮባንዱ ንግድ የደህንነት አካላቶች ተሳታፊ ናቸው የሚል እምነት አላቸው። የደህንነት አካላት የህገወጥ ንግድ ጭኖ የመጣን መኪና ተሽከርካሪ አስቁመው ሹፌሩና እረዳቱ አመለጡን ይላሉ። ኮንትሮባንዲስቱ ከሄደ በኋላ የጥይት ተኩስ አሰምተው አመለጠን በማለት ሪፖርት ያደርጋሉ ብለውናል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪያችን አቶ ሳምሶን ዳኛቸው በበኩላቸው የኮንትሮባንድ ንግድ ህጋዊ ነጋዴ በህጋዊ መንገድ ተምኖ እንዳይሸጥ ያረክስበታል። ህጋዊ ንብረቱ አልሸጥለት ሲል እራሱ የኮንትሮባንድ ነጋዴ ይሆናል። በከተማዋ ውስጥና ውጭ ያሉ አመራሮች ከ ኮንትሮባንድ ንግድ የጸዱ አይደሉም የሚል ሃሳባቸውን አጋርተውናል።
የኮንትሮባንድ እቃዎች በአብዛኛው ከወደ ሱዳን መስመር ወደ ከተማዋ በሌሊት ተጉዘው ይገባሉ። ከጦር መሳሪያ እና አልባሳት በተጨማሪ አደንዛዥ እጽና የቁም እንስሳት ንግድ በብዛት እንደሚያዝ ሰምተናል።
የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ግንቦት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዎች ምክርቤት ስለኮንትሮባንድ ሲያብራሩ በዘንድሮው 2014 ዓ.ም ባሉት አስር ወራት ውስጥ የታየው የኮንትሮባንድ ንግድ ከአለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የገቢ የኮንትሮባንድ ንግድ በ 54.26 በመቶ የጨመረ ሲሆን የወጭ የኮንትሮባንድ ንግድ ደግሞ በ 12.15 በመቶ መቀነሱን ተናግረዋል።
በዘንድሮው አስር ወራት ውስጥ 3.5 ቢሊዮን የሚገመቱ የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 492.9 ሚሊዬን ብር የሚገመቱ የወጭ ኮንትሮባንድ እቃዎች በድምሩ 4.04 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተናግረዋል።
ከ ኮንትሮባንድ እቃዎቹ ጎን ለጎን ኮንትሮባንዲስቶቹን ለመያዝ በተደረገው ትንቅንቅ 613 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው በ2013 እና 2014 አመታቶች አስር የኮንትሮባንድ ተቆጣጣሪዎች ህግ ሲያከብሩ መስዋዕትነት መክፈላቸውንና ሌሎች አካላቶችም ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በ2014 በጀት አመት የኮንትሮባንድ ንግድ ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባው ኮንትሮባንድ መጨመሩን የገቢዎች ሚኒስቴር አሳውቋል።