ግንቦት 13 ፣ 2014

ለ10 ዓመት እልባት ያላገኘው የልኡል አልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን ኃይለስላሴ /የመርሆ ግቢ/ ቤተ-መንግስት የግቢ አጥር

City: Dessieታሪክወቅታዊ ጉዳዮች

የቤተመንግስቱ አጥር በወቅቱ ባለመታደሱና የውስጥ ቅርሱም ጥበቃ ስለማይደረግለት ለከፋ ጉዳትና ጥፋት እየተዳረገ ይገኛል።

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ለ10 ዓመት እልባት ያላገኘው የልኡል አልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን ኃይለስላሴ /የመርሆ ግቢ/ ቤተ-መንግስት የግቢ አጥር
Camera Icon

Credit: Endris Abdu

ደሴ ከተማ ውስጥ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ለቤተመንግሥት አገልግሎት እንደታነጸ የሚነገርለትና የበርካታ ነገስታት ማረፊያ የነበረው በተለምዶ አጠራር “መርሆ ግቢ” እየተባለ የሚጠራው ታሪካዊው "የመሪዎች ግቢ" ቤተመንግስት በኪነ ህንጻ ውበቱ ቱሪስቶች የሚስብ ስፍራ ነበር። 

ይሁን እንጂ ችግሩ የከፋና የተባባሰ የሚያደርገው ቤተመንግስቱን ኃላፊነት ወስዶ በበላይነት የሚያስተዳድረው ተቋም ያለመኖሩ ጭምር ነው።

አቶ ኃይለማርያም ወዳጆ የደሴ ከተማ ነዋሪና የ78 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ናቸው። በቤተመንግስቱ ላይ ስለሚታየው ችግር ሲገልጹ "መርሆ ግቢ ቤተመንግስት አዲስ አበባ ከሚገኘው የጃንሆይ ቤተመንግስት የአሁኑ 6ኪሎ ግቢ ጋር በተመሳሳይ ኪነ ህንጻ የተገነባ ባለግርማ ሞገስ የነበረ ቢሆንም በመንገድ ማስፋፋትና ልማት ሰበብ በቀድሞ ስርዐት የፈረሰ ቢሆንም አሁን ድረስ የኔነት ስሜት ተሰምቶትና ኃላፊነት ወስዶ የሚያሰራው የመንግስት አካል ያለመኖሩ በጣም ያሳዝነኛል" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት በርካታ ዓመታት በባለቤትነት ጥያቄ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ የነበረው መርሆ ግቢ ቤተመንግስት በደሴ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ እና ወይዘሮ ስኂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በጋራ እንዲተዳደር መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበረ ያስታወሱት የቀድሞ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰይድ አራገው ናቸው። ሁኔታውን ሲያስታውሱ " ቤተ መንግስቱን እንዲያስተዳድር ለደሴ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የክልል ምክር ቤት በአዋጅ አጽድቆ ሰጥቶታል። በተመሳሳይ በክልሉ ምክርቤት በጸደቀ ትእዛዝ ለወይዘሮ ስኂን ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ኃላፊነት ተሰጥቷል። በተጨማሪ ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለወሎ ዩኒቨርሲቲ አሰፋ አባተ ሙዚቃ ት/ቤትን እንዲገነባ እና መርሆ ቤተመንግስቱን እንዲያስተዳድር የባለቤትነት ፈቃድና ካርታ ሰርቶ ሰጥቷል" ሲሉ ገልጸዋል። 

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ያቀረበው  የሙዚቃ ትምህርት ቤት ግንባታ ሃሳብ የሃገር ቅርስ ላይ መሆን እንደማይገባውና ሌላ አማራጭ መፈለግ እንዳለበት ባህልና ቱሪዝም መምሪያው ሃሳብ በማቅረቡና መተማመን ላይ በመደረሱ ለዩኒቨርሲቲው ተሰጥቶ የነበረው ካርታ እና የግንባታ ፈቃድ እንዲሰረዝ መደረጉን አቶ ሰይድ ጨምረው ገልጸዋል። 

የልኡል አልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን ኃይለስላሴ /የመርሆ ግቢ/ ቤተ-መንግስት Photo Credit: Endris Abdu

የደሴ ከተማ ማህበረሰብ ተደጋጋሚ ጥያቄ የሆነው የመርሆ ግቢ አጥር ያለመገንባትና የቤተመንግስቱ ውስጥ ቅርስ በተገቢው ሁኔታ ያለመያዝ ጉዳይ በዋናነት ኃላፊነቱን መውሰድ የሚገባው ማን ነው ሲል አዲስ ዘይቤ ለአቶ ሰይድ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። ሲመልሱም "መስሪያቤታችን ምንም እንኳን የባለቤትነት ጉዳዩ መፍትሄ ባይሰጠውም ከተቋቋመበት አላማ አንጻር ቅርስ ሲወድም ዝም ብሎ ማየት ስለሌለበት የልኡል አልጋወራሽ አስፋው ወሰን ቤተመንግስትን የውጨኛው ክፍል በመፍረስ ላይ የነበረ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ አድሰነዋል" ብለዋል።  ለከተማ አስተዳደሩም ያለውን ችግር በመግለጽ የአጥርና በር ግንባታው ቀድሞ በነበረበት ሁኔታ መገንባት እንዲቻል ጥያቄ ማቅረባቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

በ2014 በጀት አመት ግንባታው እንዲሰራ በክልሉ መንግስት የተወሰነው ውሳኔ በምን ሁኔታ እየተተገበረ እንደሚገኝ አዲስ የተሾሙት የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት አበበ ሲገልጹ "በተያዘው እቅድ መሰረት ወደተግባር እንቅስቃሴ ተገብቶ የነበረ ቢሆንም ደሴ ከተማ በወረራ በመያዙ ምክንያት ሊቋረጥ ችሏል። ከወረራው በኋላም ተመልሶ ግንባታውን ለማስቀጠል የበጀት እጥረት በማጋጠሙ ለደሴ ከተማ አስተዳደርና ለክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተጨማሪ በጀት እንዲፈቀድልን ጠይቀናል" ሲሉ ኃላፊዋ ገልጸዋል።

የቤተመንግስቱ አጥር በወቅቱ ባለመታደሱና የውስጥ ቅርሱም  ጥበቃ ስለማይደረግለት ለከፋ ጉዳትና ጥፋት እየተዳረገ እንደሚገኝ ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ አቤቱታ ያቀርባል። በቦታው ላይ ተገኝተን ለማረጋገጥ የቻልነውም ይሄንኑ ስለሆነ የሚመለከተው የመንግስት የሃገር ቅርስ ከመጥፋቱ በፊት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

አስተያየት