ግንቦት 13 ፣ 2014

የሐረሩ ሸሪፍ የግል ሙዚየም

City: Dire Dawaባህል ታሪክማህበራዊ ጉዳዮች

ሸሪፍ የግል ሙዚየም በሀገራችን ካሉት ሙዚየሞች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር ካለው ኢትኖግራፊክ ሙዚየም በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የሐረሩ ሸሪፍ የግል ሙዚየም
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚዲያ

በኢትዮጵያ ትልቁ የግል ሙዚየም  በሐረሪ ክልል የቀዳማዊ ኀይለስላሴ በወቅቱ የደጅ አዝማች ተፈሪ መኮንን ቤት ይገኛል፡፡ ይህ ሙዚየም ሸሪፍ ሙዚየም እየተባለ ይጠራል፡፡ ሙዚየሙ በባለቤቱ ክቡር ዶ/ር አብዱላሂ አሊ ‹‹ሸሪፍ የግል ሙዚየም›› የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል፡፡ የ70 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት አብደላህ ሸሪፍ በስነ ሰብ እና ህብረተሰብ ሳይንስ ከሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት አግኝተዋል፡፡ 

34 ዓመታትን ያስቆጠረው ሸሪፍ ሙዚየም በውስጡ ሀይማኖታዊ እና ሀገራዊ ቅርሶችን እንደያዘ ይነገራል፡፡ የሸሪፍ የግል ሙዚየም በየዓመቱ ከአስር ሺ በማያንሱ ጎብኚዎች ይጎበኛል፡፡ ይህ የግል ሙዚየም የተጀመረው የሐረሪ የሙዚቃ ስራዎችን ለመሰብሰብ በማቀድ ነበር፡፡

አብደላ ሸሪፍ በልጅነታቸው ታሪክን የማወቅ ጉጉት እንዲሁም የኪነጥበብ ቡድን ተሳትፎ እንደ ነበራቸው ይነገራል፡፡ ‹‹በ1982 የሐይዋን የኪነጥበብ ቡድን 25ኛ አመት  የምስረታ በዓል ላይ ሙዚቃዎቻችንን ማን ይሰበስብልናል የሚል ውይይት ተካሄደ፡፡ በዚህ ጊዜ አብደላህ ሸሪፍ እኔ እሰበስባለሁ ሲሉ ቃል ገቡ፡፡ ከዛም ብዙ ባህላዊና ዘመናዊ ዘፈኖች ከተለያዩ ባንዶች በአደራና በእምነት ጎረፈላቸው፡፡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከ260 በላይ የሀረሪ ሙዚቃ አልበሞችን መሰብሰብ ቻልኩ፡፡›› ሲሉ ይናገራሉ አብደላህ ሸሪፍ፡፡

ይህንን ተነሳሽነታቸውን የተመለከተው ማህበረሰብ የተለያዩ ቅርሶችን በአደራ መልክ ለአብደላህ ሸሪፍ ይሰጣቸው ጀመር፡፡ በዚህ መልኩ መሰብሰብ የጀመረው ቅርስ ቤታቸውን አጣበበው፡፡ ብዙ ሰውም እየመጣ ይጎበኛቸው ስለነበር በ1903 ዓ.ም የተሰራ እንደነበር የሚነገርለት የቀድሞው ኀይለስላሴ መኖሪያ ቤት እንዲሰጣቸው ተወሰነ፡፡ ይህ ቤት በደርግ መንግስት ተወርሶ ለ22 አባ ወራዎች መኖሪያነት እያገለገለ የነበር ቢሆንም ለነዋሪዎቹ ቅያሪ ቤት በመስጠት ሙሉ እድሳት ተደርጎለት ለአብደላህ ሸሪፍ ተላልፎላቸዋል፡፡

ሸሪፍ የግል ሙዚየም በሀገራችን ካሉት ሙዚየሞች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር ካለው ኢትኖግራፊክ ሙዚየም በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

እንደ አብደላህ ሸሪፍ ገለፃ እነዚህን ቅርሶች የሰበሰቡት ከባለቤታቸው ወ/ሮ ሰዓዳ ጋር በመሆን እንደሆነና ታሪክን ለማስቀመጥ ብዙ መሰዋት እንደከፈሉ ይናገራሉ፡፡ የሸሪፍ ሙዚየም ባለቤት ክቡር ዶ/ር አብዱላሂ አሊ ሸሪፍ በመኖሪያ ቤታቸው ለ17 ዓመታት ይህን ቅርስ ማቆየት ችለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አሁንም ድረስ አራት ልጆቻቸውና እና ባለቤታቸው የአስም በሽተኛ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡

በግዢ፣ በስጦታና በአደራ ከ20 ሺ በላይ ቅርሶችን ሰብስበው በሙዚየም ውስጥ ማስቀመጥ እንደቻሉም ይናገራሉ፡፡ መሰብሰብ ብቻም ሳይሆን በተለይ መፀሀፍትን መጠገንም አንዱ ተግባራቸው ነው፡፡ በራሳቸው ልምድ ባካበቱት የዛጉ ብረቶችን ወደነበሩበት ይዞታቸው መመለስ ውሀ፣ አልኮልና ዱቄት ሳሙናን በመጠቀም የተሰበሩ ሸክላዎችና የድሮ ጠርሙሶችን በመጠገን ወደ ነበረው ይዞታቸው መመለስ ቅርሶችን በራሳቸው እውቀት እየጠገኑ ይንከባከባሉ፡፡ ይህንን ልምድ በመጠቀም ወደ ሀርጌሳ በመሄድ ስለመፀሀፍ አጠጋገን የቅርሱን ይዘት ሳይለቅ እረጅም አመትም እንዴት ማቆየት እንደሚቻል ስልጠና እንደሰጡ አጫውተውናል፡፡

ክብር ዶ/ር አብዱላሂ አሊ ሸሪፍ በሸሪፍ ሙዚየም ቤት ምን አይነት ቅርሶች እንደሚገኝ ሲገልፁ የአፄ ሚኒሊክ፣ የአፄ ቴዎድሮስ፣ የኢማም አህመድ (ግራኝ አህመድ)፣ የቀዳማዊ አፄ ኀይለስላሴ እንዲሁም እድሜ ጠገብ ጎራዴዎች፣ በእጅ የተጻፉ ቅዱስ ቁርዓን ጨምሮ ከ1000 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው የአረብኛና በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ መጻህፍት፣ ህገ-መንግስት፣ የጥንት የሐረሪዎች የመገበያያ ገንዘብ፣ ታሪካዊ የሴቶች ዓልባሳት በውስጡ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ በአሁን ወቅት መንግስት ሰጥቷቸው በቀዳማዊ ኀይለስላሴ መኖሪያ ቤት ይገኛል፡፡ 

እንዲሁም አብደላህ ሸሪፍ የ3 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደርጎላቸው የቤት እደሳትና መጻህፍት ጥገና እያደረጉ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡

ዶ/ር አብደላህ ሸሪፍ ቁርዓንና የተለያዩ ኢስላማዊ መፀሐፍትን በቱርክ፣ በታንዛኒያ፣ በኢራንና በሞሮኮ ኢግዚቢሽኖች ላይ አቅርበዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እና የተለያዩ ሀገራት ኢንባሲዎች ለጥረታቸው እውቅና አግኝተዋል፡፡

በሐረሪ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቅርስ ጥበቃ ዋና ሀላፊ አቶ ተወለዳ አብዱሽ የሸሪፍ ሙዚየም ከ 1000 ዓመት በላይ የሆናቸው ቁርዓኖች እና ኢትዮጵያ እስልምናን ከተቀበሉ ቀደምት ሀገራት መካከል እንደምትገኝ የሚያረጋግጡ ቅርሶች እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡

አቶ ተወለዳ አብዱሽ በቱሪዝም ዘርፍ የምስራቁ ክልል ብዙ የቱሪዝም ሀብቶች ቢኖሩትም ብዙ ቱሪስቶች ሲጎበኙት አይታይም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት በሚገባው ልክ የማስተዋወቅ ስራዎች ስላልተሰሩ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ እንደ አቶ ተወልዳ ገለፃ ይህን ችግር ለመቅረፍ በቅርብ ከአምስቱ አጎራባች ክልሎች ከድሬዳዋ፣ሐረር፣ አፋርና ሶማሌ ጋር የምስራቅ የቱሪዝም ክላስተር አቋቁመን የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል ሰነድ ተፈራርመናል፡፡ ይህም ትስስርን በመፍጠር አንዱ ክልል የመጣ ቱሪስት ሌሎች ክልሎች ውስጥ የሚገኙትን ቅርሶችን እንዲጎበኝ የማድርግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ሸሪፍ ሙዚየም በአሁኑ ወቅት ሁለት መጋዘንና አምስት ኤግዚብሽን ክፍሎች ያሉት ሲሆን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካም ሀብት የሆነ ሙዚየም ማድረግ ችለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ1300 በላይ መፀሀፍቶችን ዲጂታላይዝ አድርገው በአሁኑ ስዓት በሀርድ ዲስክ በሙዚየሙ ውስጥ ይገኛል። እረጅም አመት ያስቆጠሩ ከ600 ሰዓት በላይ የሆኑ የጥንት የሀረሪ ሙዚቃዎች በአንድ ላይ በማሰባሰብ አቅርቧል። ለዚህም ቤተሰቦቻቸው እና የቅርብ ወዳጆቻቸው እንደሚያግዟቸው ተናግረዋል።

አስተያየት