ግንቦት 12 ፣ 2014

"የቃልኪዳን-ቤተሰብ" ፕሮጀክት ተማሪዎችን እንዴት ይጠቅማል?

City: Gonderወቅታዊ ጉዳዮች

ይህ ፕሮጀክት ቀጣይነት ያለው ፕሮጀክት ስለሆነ አዲስ ገቢ እና ነባር ተማሪዎችን የቃልኪዳን-ቤተሰብ እንዲኖራቸው በማድረግ ከክልሎች ጋር ያለንን ወንድማማችነት ለማጠናከር ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ" እንደሚገኙ ተነግረዋል

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

"የቃልኪዳን-ቤተሰብ" ፕሮጀክት ተማሪዎችን እንዴት ይጠቅማል?
Camera Icon

Photo Credit: University of Gondar, 2013.

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስቱና በትግራይ ሃይል መካከል የተካሄደው ጦርነት ትግራይን ተሻግሮ ሌሎች የሃገራችን ክልሎችን የገፈቱ ቀማሽ እንዲሆኑ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ መካከል በዋናነት ደግሞ በአማራ ክልል በሚገኙ አከባቢዎች ላይ መሆኑ ይታወቃል። 

ከሰሞኑ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር በጦርነቱ ምክንያት የተስተጓጎለዉን  የመማር ማስተማሩን ስራ እንዲቀጥል በሚል ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸዉን እንዲቀበሉ እና የተቋረጠዉን የትምህርት ስርዓት እንዲያስቀጥሉ አድርጓል ። 

በሀገሪቷ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ዉስጥ ከዚህ ቀደም እምብዛም ያልተለመደዉ እና ከጦርነቱ ወዲህ ግን በመንግሥት ደረጃ ተጠናክሮ የቀጠለዉ አንድ ቤተሰብ አንድ ከሌላ ማህበረሰብ ለትምህርት የመጣን ልጅ እንደራሱ በማድረግ ትምህርቱን ጨርሶ እስኪመረቅ ድረስ መንከባከብ እንዲችል በሚል የተጀመረዉ "የቃልኪዳን-ቤተሰብ" ፕሮጀክት በዋነኝነት ይጠቀሳል። 

ይህ የቃልኪዳን ቤተሰብ  "በጎንደር ዩኒቨርስቲ" ከተጀመረ ሶስት ዓመታትን ማስቆጠሩን ሰምተናል። ትኩረቱም ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ዩኒቨርስቲ የተመደቡ ተማሪዎች የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማቸዉ ለማድረግ እንደሆነ ነዉ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች የሚናገሩት። 

የቃልኪዳን-ቤተሰብ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ታደሰ ወልደ ገብርኤል  " ዘንድሮ ሶስተኛ ዓመቱን የያዘዉ ፕሮጀክቱ እስካሁን ከ 10 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸዉን " ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ተናግረዋል ። ዶክተር ታደሰ አክለዉ "በ 2013 ዓ.ም  የትምህርት ዘመን በጦርነቱ  ምክንያት የተስተጓጎለዉ  የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲቀጥል እና ከዚህ ቀደም የነበረዉ አሰራርን በማጠናከር  ከ 2 ሺህ በላይ የከተማዋ በጎ ፈቃደኛ ወላጆችን መመዝገብ መቻላቸዉን  " ያስታዉሳሉ ።

በአሁን ወቅት በዩኒቨርስቲዉ እየተተገበረ የሚገኘዉ የስምምነት ዉል የሚካሄደው በተማሪው እና ፍቃደኛ በሆነዉ ቤተሰብ መካከል ሲሆን በሶስት ቅጅ የሚሞላ ነው፤  አንዱ ቅጅ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛው ቅጅ ለቃልኪዳን ቤተሰብ፣ ሶስተኛው ቅጅ ለቃልኪዳን ተማሪ የሚሰጥ ነው ተብሏል ።

በሁለቱ አካላት መካከል የሚደረገዉ ስምምነት ሃገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለዉ የሚናገሩት  የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት  ዶክተር አስራት አጸደወይን  የስምምነቱ ዓላማ " ተማሪዎች በትምህርት ላይ ቆይታቸው የብቸኝነት ስሜት  እንዳይሰማቸው ለማድረግ፣ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ያለውን የወንድማማችነት ትስስር ለማጠናከርና የባህልና የቋንቋ እንዲሁም የታሪክ እሴቶችን ለማዳበር ያግዛል " ብለዋል።

በዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ተማሪ ጌታሰው እውነቱ አንዱ ሲሆን የኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ነዉ ፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት በዩኒቨርስቲዉ ቆይታዉ የሚያጋጥመዉን ክፉ ደጉን ከቃልኪዳን ቤተሰብ ወላጆቹ ጋር ማሳለፉን ያስታዉሳል " ለእኔ ወላጆቼ ናቸዉ ማለት እችላለሁ የቸገረኝን ማንኛዉንም ነገር በቅንነት ይሰጡኛል እስካሁን ያለ ምንም ስጋትና ብቸኝነት ትምህርቴን እየተከታተልኩ እገኛለሁ"። 

አቶ ቻላቸው መኮንን የጎንደር ከተማ የ አራዳ ክ/ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ የፕሮጀክቱ አንድ አካል ናቸዉ። በዩኒቨርሲቲው የተሰጣቸው  አንድ ልጅ አላቸው።እርሳቸዉ እንደሚሉት "ከዩኒቨርሲቲ ልንከባከበው የተቀበልኩትን ተማሪ እርዳታዎቼ ሲያስፈልገዉ ይነግረኛል ፤ ቤተሰቡን ለመጠየቅ ሲሄድ እና ከዚያም ሲመለስ በምችለዉ ልክ አግዘዋለሁ" የሚሉት አቶ ቻላቸዉ ልጁንም እንደልጃቸው በማየት እንደ ወላጅ በመንከባከብ የተጣለባቸዉን ኃላፊነት በፈቃዳቸዉ እየተገበሩት እንደሚገኙ ነግረዉናል ። 

ጎንደር ዩኒቨርስቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ 5 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች የተቀበለ ሲሆን አሁን ላይ ከ 49 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል ። ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን  "ይህ ፕሮጀክት ቀጣይነት ያለው ፕሮጀክት ስለሆነ አዲስ ገቢ እና ነባር ተማሪዎችን የቃልኪዳን-ቤተሰብ እንዲኖራቸው በማድረግ ከክልሎች ጋር ያለንን ወንድማማችነት ለማጠናከር ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ" እንደሚገኙ ነግረዉናል።

አስተያየት