ግንቦት 12 ፣ 2014

ከጥናትም፣ ከባለሙያዎች ሀሳብም የራቀው የአዲስ አበባ ህንፃዎችን ግራጫ የማድረግ ውሳኔ

ማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

ባለሙያዎችን ያለማማከር እና ለጥንታዊ የኪነ ህንፃ ውጤቶች ጥበቃ ዋጋ አለመስጠት ያመጣው ውሳኔ ነው። የኪነ ህንፃ አሁን የደረሰበት ዘመን ምንም ዓይነት ገደቦች የሌሉትና ጊዜውን የዋጀ ነው

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ከጥናትም፣ ከባለሙያዎች ሀሳብም የራቀው የአዲስ አበባ ህንፃዎችን ግራጫ የማድረግ ውሳኔ
Camera Icon

ፎቶ፡ አዲስ ዘይቤ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ የህንፃዎች የውጭ ቅብ ግራጫ ቀለም እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ በርካታ ውዝግቦች በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ታይተዋል። በርካቶችም ከስነ ልቦና ጋር በተያያዘ ግራጫ ቀለም ስለሚሰጠው ትርጓሜ ሀሳቦችን አንሸራሽረዋል። 

የቀለም ዘርፍ ባለሙያ የሆነው ጌታሁን ሄራሞ ከዚህ ቀደም በቀለማት ስነ ልቦናዊና አካላዊ ተፅዕኖ ከጋዜጠኛና ደራሲ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ጋር ካደረገው ቆይታ ላይ ሪካርድ ኩለር የተባለ ተመራማሪ እንደ አውሮፓዉያን አቆጣጠር በ1976 ያደረገውን ምርምር ዋቢ አድርጎ የሚከተለውን ሀሳብ በማህበራዊ ትስስር ገፁ አስፍሯል። 

“በጥናቱም መሠረት ግራጫ ቀለም ውስጥ ለሦስት ሰዓታት ያህል የቆዩ ሰዎች የ“አልፋ” የአንጎል ሞገድ እንቅስቃሴ(alpha brain-wave activity) በመሳሪያ በሚለካበት ወቅት በጣም ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል። ለዚህም ምክንያቱ እንደ ግራጫ ያሉ ደብዛዛ ቀለማት ትኩረትን የመሳብ አቅማቸው በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ሰዎቹ አካባቢውን በመርሳት ለራሳቸው ጉዳይ ንቁ (conscious) ለመሆን በመገደዳቸው ነው። ስለዚህም ግራጫ ቀለም በተቀባበት ክፍል የተቀመጠ ሰው ሁሌም ስለ ራሱ ሁኔታ በማጠንጠን ስለሚጠመድ ውጥረቱ ሊጨምርና ራሱን ለማጥፋት ሊነሳሳ ይችላል። በተቃራኒው ሞቃት የሆኑ ቀለማት (ቀይ፣ ቢጫ ፣ ብርቱካናማ) በተቀባበት ክፍል ለተወሰኑ ሰዓታት በምንቀመጥበት ወቅት የሚጨምረው የ“ቤታ” የአንጎል ሞገድ ምት (beta brain wave activity) ነው። እንደዚህ ዓይነት ምት በሚያይልበት ወቅት አንጎላችን ለራስ እንቅስቃሴ ዕውቅናን ይነፍግና (Unconscious state) በአካባቢው ሁኔታ መመሰጥ ይጀምራል። ተመስጦው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ብዙ ደም ወደ አንጎላችን ስለሚላክና ልባችንም በዚሁ ሥራ ስለሚጠመድ በቆይታ የልብ ምታችን እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል። ስለዚህም አካባቢያችንን ዲዛይን በምናደርገበት ወቅት እነዚህን ሁለቱንም ፅንፎች ማለትም ከፍተኛ መደበትና መነቃቃት (understimulation and Overstimulation) ማስወገድ አለብን ማለት ነው” ሲል ባለሙያው ገልጿል።

በዛሬው እለት በከተማ መስተዳደሩ የተወሰነውን ውሳኔ እንዲፈፀም የሚያዙ ደብዳቤዎች ለህንፃ ገንቢዎችና ባለቤቶች መድረሳቸውን ማወቅ የቻልን ሲሆን፣ ደብዳቤውንም የመመልከት ዕድል አግኝተናል። 

ደብዳቤው እንዲህ ይላል፣ “... በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ደረጃ 4 ወለል እና ከዚያ በላይ ያሉ ህንፃዎች ግሬይ ቀለም መቀባት አለባቸው ተብሎ አቅጣጫ ስለወረደ እርስዎም ከዛሬ 10/09/2014 ቀን ጀምሮ የህንፃዎን የውጭ ግድግዳ ግሬይ ቀለም እንዲቀቡ እናሳውቃለን።”  

አቶ ዳዊት በንቲ ከ25 ዓመታት በላይ በህንፃ ንድፍ ባለሙያነት እና የኪነ-ህንፃ መምህርነት እየሰሩ የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። እንደ ባለሙያው ማብራሪያ፣ አዲስ አበባ በዓለም ላይ ካሉ ዋና ከተማዎች መካከለኛ እድሜ ያላት ናት። ከተመሰረተች 136 ዓመታት ገደማ የሆናት ከተማዋ በርካታ አብዮቶችን አስተናግዳለች፣ ውድመቶች ገጥመዋታል፣ የፖለቲካ ርዕዮት ልዩነት ያላቸው የተለያዩ መንግስታት ተፈራቀውባታል። እነዚህ የፖለቲካ ማህበራዊና ታሪካዊ ዳራዎች የከተማዋን እና የነዋሪውን ሁኔታ እንደሚወስኑ አቶ ዳዊት ይናገራሉ። 

በባለሙያው አስተያየት መሰረት በስነ ህንፃ እና ኪነ-ጥበብ ወርቃማ ዘመን የሚባለው በአውሮፓውያኑ ቀመር እኤአ 1960 ዎቹ ናቸው። እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ አዲስ አበባ የተሻለ የሚባል የራሷ የሆነ የኪነ ህንፃ ባህል ነበራት። የጣልያን ወራሪ ኃይል ሲመጣ በኪነ ህንፃው ዘርፍ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ጥሯል። በመቀጠል በደርግ ዘመነ መንግስት ምስራቃውያን ጡብ ላይ የተመሰረተ ግንባታን ሲያስፋፉ፣ በኢህአዴግ ዘመንም በተመሳሳይ የተለየ የግንባታ ሂደት ተከትሏል። የእነዚህ ሁሉ የኪነ ህንፃ ግንባታ መልኮች አዲስ አበባን ጉራማይሌ አድርገዋታል።

“በተለያዩ የአዉሮፓ ሀገራት ወጥ የሆነ የግንባታ ስርዓት እና የቀለም ቅቦች ይታያሉ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ ከተሜነት ሲስፋፋ በአንድ ጊዜ የተገነቡ በመሆናቸው እንጂ የቀለም ቅብ ባለሙያዎች አልያም የህንፃ ገንቢዎች ተመካክረው ያደረጉት አይደለም። ለምሳሌ በኢትዮጵያም ቢሆን በኢህአዴግ ጊዜ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ብንመለከት ሁሉም ተመሳሳይ ናቸው” ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

እንደ ቪየና፣ ፓሪስ፣ ሮም ያሉት ከተማዎች በኢትዮጵያም እንደ ሐረር ጀጎል መንደሮች፣ አርጎባ ሾንኬ ተራራ ላይ ያሉ ከተማዎች ወጥነት ይታይባቸዋል። ነገር ግን ሀገር ውስጥ ያሉትም ሆኑ የውጪዎቹ በጊዜው በነበረው ግብዓትና ሁኔታ ተፅዕኖ ያረፈባቸው በመሆናቸው እንጂ እነዚሁ ከተማዎች ውስጥ የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮችን ራቅ ተብሎ ቢታይ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ የኪነ ህንፃ ውጤቶች አሉ።

ዳዊት በንቲ እንደሚገልፁት “ፈረንጆች ይበልጡናል በሚል እሳቤ ተመሳሳይ ቅብ ያለባቸው ከተማዎችን ተመልክተን እነሱ እኮ ተመካክረው ነው ያደረጉት ብለን ማሰባችን ስህተት ነው፤ ሂደቱን ሲጠብቅ ነው እንደዛ የሆነው።”

ጎንደር እና ላሊበላን በመሳሰሉ ከተማዎች የሚገኙ ጥንታዊ የኪነ ህንፃ ውጤቶችን ብንመለከት ዘመናዊነት የማይታሰብበት ጊዜ በመሆኑ ለኪነ ህንፃ ጥቅም ላይ የሚውሉት ግብዓቶች እንደ ድንጋይ እና ኖራ የመሳሰሉት በመሆናቸው መመካከር ሳያስፈልገው አንድ ዓይነት ቅብ ተፈጥሯል ሲሉ አቶ ዳዊት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በኪነ ህንፃ ዘርፍ የተለያዩ ዘመኖች አሉ የሚሉት ባለሙያው ዘመናዊነት፣ ድህረ ዘመናዊነት፣ የኪነ ህንፃ ቴክኖሎጂ፣ ብተና ወይም ዲኮንስትራክሽን እያለ መጥቶ አሁን ፓራሜትሪክ ወይም የሚሰራው ኪነ ህንፃ ምንም አይነት ገደብ የሌለው መሆን ደረጃ ላይ ደርሷል። 

ኢትዮጵያ ውስጥ ቀለማት ልዩ የሆነ እይታ አላቸው፤ ከምግቡ ጀምሮ እስከ ባህላዊ አልባሳት ድረስ የሚታዩት ጉራማይሌ ቀለማት የሚፈጥሩት ስሜት አለ፤ ታዲያ ግራጫን እዚህ ጋር ምን አመጣው? ሲሉም አቶ ዳዊት በንቲ ይጠይቃሉ።

የዚህ አግባብ ያልሆነ ውሳኔን መነሻ ሲያስረዱም “ምሁራንን ያለማማከር ውጤት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ የቆየ የኪነ ህንፃ ባለሙያዎች ማህበር አለ፣ የቀለም አዋቂዎች አሉ። ባለሙያዎች በአንድ ጉዳይ ላይ በሚቀርቡ ሀሳቦች አለመስማማታቸው 'ያስቸግራሉ' ተብሎ ነው የሚቆጠረው” ብለዋል።

በተጨማሪም ጥንታዊ የኪነ ህንፃ ውጤቶችን አለመጠበቅ ሌላኛው ችግር ነው። አሁን ባለው ሁኔታ በባለሙያዎች ጩኸት ከሚተርፉት ጥቂቶች በዘለለ የጥንት የሚባሉ የኪነ ህንፃ ዉጤቶች በስፋት እየፈረሱ ነው። “አውዳዊ ክስተቶች፣ ስነ ምህዳራዊ፣ የአየር ንብረት ምክንያቶችን ያገናዘበ ውሳኔ ያስፈልጋል” ብለዋል የኪነ ህንፃ ባለሙያው። 

በከተማ ደረጃ በርካታ ቅድሚያ ተሰጥቶ መስተካከል ያለባቸው እንደ ምቹ ያልሆኑ የእግረኛ መንገድ፣ ማረፊያ ቦታዎች፣ የትራፊክ ምልክቶችን የሚከልሉ የመንገድ ዳር መብራቶች እና ተክሎች ያሉበትን ጨምሮ በርካታ ሁኔታዎች ባሉበት ሌላ ሀገር ላይ የታየን ነገር እዚህ ቀጥታ ማምጣት አይቻልም።             

የኪነ ህንፃ ባለሙያዎች ውሳኔውን እንዲህ ቢመለከቱትም የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ተፈፃሚ እንዲሆን ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። አዲስ ዘይቤ አሁን ባለው ገበያ አማካኝ ወጪዎችን ለመገመት ባለሙያዎችን ጠይቋል።

በእዚህ ወቅት በግንባታ ላይ እየሰሩ ከሚገኙ ባለሙያዎች በተሰበሰበው መረጃና ምልከታ መሰረት አንድ ጋሎን ወይም ወደ አራት ሊትር ገደማ የሚሆን ነጭ ቀለም ከፋብሪካ 480 ብር እንዲሁም ከነጋዴዎች በ560 ብር እየተሸጠ ይገኛል። ይህ ነጭ ቀለም መቀመሚያ ኬሚካሎችን በመጠቀም ወደተፈለገው ቀለም የሚቀየር ሲሆን እነዚህ መቀላቀያ መቀመሚያዎች በአማካኝ ከ60 እስከ 180 ብር የሚሸጡ ናቸው። 

የኪነ ህንፃ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት አንድ ጋሎን ቀለም በአማካኝ 16 ካሬ ሜትር ቦታን ይቀባል። ግንባታዎች በወለል ደረጃ እንደየስፋታቸው የሚያስፈልጋቸው የቀለም ብዛት የሚለያይ ሲሆን በአዲስ አበባ አማካኝ ስፋቶች መሰረት ከ70 ሜትር ስኩዌር እስከ 280 ሜትር ስኩዌር የሚሆኑ ግድግዳ ያላቸው ግንባታዎች እንደሚገነቡ የኪነ ህንፃ ዘርፍ ባለሙያዎች ገልፀዋል። እነዚህን አሃዞች ከግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ ቀለም ለመቀየር ለአንድ ወለል በአማካኝ ከ3 ሺህ 400 ብር እስከ 12 ሺህ 240 ብር ድረስ በአማካኝ ወጪ ያስፈልጋል። በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ውሳኔ መሰረት ደግሞ አራት ፎቅና ከዚያ በላይ የሆኑ እንዲቀየሩ የሚያዝ ሲሆን ባለአራት ፎቅና ህንፃን ቀለም ለመቀባት የቀለም ቅብ ባለሙያን ወጪ ሳይጨምር ለግዢዎች ብቻ ከ13 ሺህ 600 ብር እስከ 48 ሺህ 960 ብር ይፈጃል።

አስተያየት