ሰኔ 3 ፣ 2014

በኢትዮጵያ እየወረደ የመጣው የወተት ጥራት

City: Addis Ababaጤናወቅታዊ ጉዳዮች

የወተት ፍላጎት እና አቅርቦቱ ካለመመጣጠን አልፎ የጥራት ጉዳይ የብዙዎች ቅሬታ ምንጭ ሆኗል።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

በኢትዮጵያ እየወረደ የመጣው የወተት ጥራት
Camera Icon

Credit: Social Media

በኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥርና በገቢ መጨመር እንዲሁም በከተሞች መስፋፋት ምክንያት የወተት ተዋጽኦዎች ፍላጎት እየጨመረ መሄዱ ይስተዋላል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የወተት ፍላጎት መጨመር ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የሚገኙ ወተት አምራች ድርጅቶችን መጠን በሶስት እጥፍ እንዲጨምር አድርጓል። የወተት ፍላጎት እና አቅርቦቱ ግን ካለመመጣጠን አልፎ የጥራት ጉዳይ የብዙዎች ቅሬታ ምንጭ ሆኗል። አንዳንድ የወተት ተጠቃሚዎችም ቅሬታቸውን ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

"በሳምንት ሶስት ወይም አራት ጊዜ ወተት እገዛለሁ" የምትለን በላይነሽ የተባለች የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት። ምሬቷን ስትገልፅም “የምገዛው ወተት ወጥነት የለውም፣ አንዳንድ ቀን ይበጣጠሳል ወይም መጠኑ ይለዋወጣል፣ በተጨማሪም ውሃማ ይሆናል። በዚህም ብዙ ጊዜ ብስጭት ይሰማኛል” ትላለች።

ሌላው የወተት ደንበኛ የሆነው አቢይ የተባለ ግለሰብ የወተቱ ጥራት እያሽቆለቆለ ስለመምጣቱ ስጋቱን አጋርቶናል። “ብዙ ጊዜ ጨጓራዬን ስለሚያመኝ ህመሙን ለማስታገስ ወተት መጠጣት አዘወትራለሁ። ሆኖም አሁን አሁን የምገዛው ወተት ውሃነቱ ስለሚያይል ምንም ጥቅም እየሰጠኝ አይደለም”  ሲል ይናገራል።

"የወተት ማሸጊያው እየጠበበ መምጣቱን አስተውያለሁ" በማለት አስተያየቱን ያጋራን ደግሞ ሌላ መደበኛ የወተት ተጠቃሚ ሲሆን ወተቱ ውሃ ውሃ እንደሚለው ተናግሯል።

ከወራት በፊት የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት እንደገለጸው ጥሩ ጥራት ያለው ጥሬ ወተት ከበሽታ አምጪ ተህዋሲያን፣ ከመጥፎ ጣዕም፣ ካልተለመደ ቀለም እና ሽታ የጸዳ መሆን አለበት። እንዲሁም የባክቴሪያ መጠኑ እጅግ ዝቅተኛ መሆን እንዳለበት በመጥቀስ ከልዩ ልዩ ኬሚካሎች የጸዳ እና ልኬቱ የተመጠነ አሲድ እና ቤዝ ሊኖረው እንደሚገባ ያሳስባል።

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብቶች ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛ፣ በዓለም ከ10 አገሮች መካከል አንዷ ብትሆንም ከወተት ሀብቷ ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች ስላለመሆኗ ይወሳል። በሌላ በኩልም ሌላው ዓለም ባለው የእንስሳት ቁጥር ልክ ወተትን በየገበታው በተለያየ መልኩ ሲጠቀም እንደሚታይ በኢትዮጵያ ግን ባሉት እንስሳት ልክ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ አለመሆኑ ይነገራል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ዓመታዊ የወተት ምርት ከአራት ሚሊዮን ሊትር የዘለለ አይደለም።

በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ ለአንድ ሰው በዓመት በአማካይ የሚደርሰው የወተት መጠን 19 ሊትር ብቻ ሲሆን በጎረቤት ኬንያ ከ100 ሊትር በላይ ነው፡፡ ከምክንያቶቹ አንዱ በኢትዮጵያ የሚገኙት የወተት ላሞች እንደብዛታቸው ወተት የሚሰጡ ባለመሆናቸው ነው፡፡ 

ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የእንስሳት እርባታ ንኡስ ዘርፍ ለአርሶ አደሩ ገቢ በማስገኘት፣ የስራ እድል በመፍጠር፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለማህበራዊ፣ ባህላዊ እና አካባቢያዊ እሴቶች የበኩሉን አስተዋፅኦ በማድረግ እና ኑሮን በመደገፍ ለሃገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ይታመናል።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የወተት ምርት አሁንም አነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይነገራል።  በጎንደር ዩኒቨርስቲ የግብርና ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር በእውቀቱ ምናለ “የወተት ችግር በተለይ በከተሞች በስፋት ይታያል፡፡ ምክንያቱም አርቢ ስላልሆነ ነው። 80 በመቶ የሚሆነውን ወተት የሚያመርተው የገጠሩ ሕዝብ ነው፡፡ ከምርቱ አናሳነት እና የሃገራችን የመንገድ አቀማመጥ አስቸጋሪነት ጋር ተያይዞ 70 ከመቶው የሚሆነው ምርት ከሚመረትበት አካባቢ ተነስቶ በንጹሕ ወተትነት ወደ ገበያ አይገባም” ይላሉ።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ገበሬው አብዛኛውን ምርት ለራሱ ይጠቀመዋል፣ ወይ ረዥም ጊዜ እንዲቆይለት ወደ ቅቤ፣ አይብ በመቀየር ያስቀምጠዋል፡፡ ቀሪው ወደ ገበያ ይመጣል፡፡ በዚህም ምክንያት 95 በመቶው ንግድ የሚከናወነው በባህላዊ መንገድ ነው። ዘመናዊ ንግድ የምንለው ደግሞ ከአምስት በመቶ የማይበልጠው በፋብሪካዎች ተመርቶ ለሚወጣው ወተት የሚደረገው ንግድ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከሁለት በመቶ አይበልጥም፡፡ 

“ይህን ስንመለከት በአገራችን የወተት ምርት ገበያ የዳበረ ወይም የሠለጠነ አለመሆኑን እናያለን፡፡ ያለውን 30 በመቶ የሆነውን ምርት ብቻ እንኳን ወደ ዘመናዊ ገበያ ብናመጣው በወተት ገበያው ላይ ትልቅ ለውጥ ይመጣል፡፡ ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል፡፡ ይህም ባለመደረጉ በዓመት እስከ አራት ሚሊዮን ዶላር በማውጣት የውጭ ወተት ወደሃገር ይገባል፡፡  ሌሎች ሃገራት ባላቸው የእንስሳት ቁጥር ልክ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ሁልጊዜም ከገበታቸው በተለያየ ሁኔታ ይቅረብ እንጂ ወተትን አይጠፋም። በዚህም ንግዱ በስፋት ይካሄዳል፣ ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ተቃራኒ ነው ፤ እንስሳት እያሉን ተጠቃሚዎች አይደለንም” በማለት በዚህ ምክንያት የቀነጨረ ማኅበረሰብ እንደሚፈጠር ያስረዳሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር በእውቀቱ።

የኢትዮጵያ የደረጃዎች ባለስልጣን ዳይሬክተር ይልማ ጅሩ “የወተትን ጥራት ደረጃ የምንሰጠው የወተት ላሞችን ምርመራ በማረጋገጥ፣ በወተቱ ውስጥ የሚገኘውን የባክቴሪያ መጠን እና ደረጃ በመገምገም፣ እንዲሁም በወተት ውስጥ የሚገኘውን የስብ እና የፕሮቲን መጠን እና ሌሎችም መስፈርቶች ላይ በመመርኮዝ ነው” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል። 

አቶ ይልማ አክለውም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ከንግድ ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ በወተት ማቀነባበሪያና ምርት ጥራት ላይ የሚሰራ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ መዋቀሩን በመግለጽ በወተት ምርቶች ላይ ከተጠቃሚዎች የሚሰማውን ቅሬታ ለማስተካከል ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

አያይዘውም ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው የወተት ጥራት ደረጃዎችን በአለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጡት ደረጃዎች ጋር በማቀናጀት እንድሚቆጣጠር አስረድተዋል። “ወተት ዓለም አቀፋዊ ምርት እንደመሆኑ መጠን በማይክሮ ባክቴሪያ ስብጥር፣ በአስተሻሸግ እና በስርጭት ሂደት ማሟላት የሚገባው ተመሳሳይ ደረጃዎች አሉት” በማለት ለወተት ጥራት ቁጥጥር ተብለው የተዘጋጁ መመሪያዎችን ያቀፉ ጥራዞች መኖራቸውን አብራርተዋል። 

ከደረጃዎች ባለስልጣን መስርያ ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ማንኛውም ወተት ወደ ገበያ ከመግባቱ በፊት የተቀመጠውን ደረጃ ያሟላ መሆኑን ለማረጋገጥ መሞከር አለበት። የደረጃውን አፈጻጸም የሚከታተሉትን ተቆጣጣሪ አካላት የሚገዛ አስገዳጅ ህግም በቅርቡ ወጥቷል። 

"ሁኔታውን በማስተማር እና በመከታተል ላይ ትኩረት አድርገናል" ያሉት ደግሞ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ አቶ ተከተል ጌታነህ ናቸው። "ወተት አምራቾች በወተት አመራረት ሂደታቸው ውስጥ ያሉትን ደረጃዎች የማክበር ሃላፊነት አለባቸው፣ ነገር ግን ደረጃው በቅርቡ የተሰራ በመሆኑ ወተት አምራቾች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ጥራት ያለው ወተት የማምረት ሂደት የሚከተሉበት መድረክ መፍጠር አለብን። በዚህም ከበጎ ፍቃደኝነት ወደ አስገዳጅ ምዕራፍ እየተሸጋገርን ነው" ሲሉም አክለዋል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የወተት ጥራት እና አጠቃቀም ጉዳይ እንቆቅልሽ መሆኑን የሚናገሩት የዘርፉ ባለሙያዎች መንግሥት ያወጣውን ህግ በአግባቡ ከተገበረ መፍትሔ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይገልጻሉ። ህጉ አንድ እንስሳ እንዴት መርባት አለበት? ጤናውን እንዴት መጠበቅ አለበት? መኖርያው እንዴት ነው? ንግዱስ እንዴት መካሄድ አለበት? ለሚሉት ሃሳቦች አቅጣጫ ያስቀመጠና በጠቅላላው የእንስሳት አረባብና አደቃቀል ላይ ሕግ ስለወጣ ይህ ከተተገበረ ለውጥ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

አስተያየት