የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ በሀይል እጥረት ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ያልገቡ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ ነው ቢልም የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተለዩትን ፕሮጀክቶች በተመለከተ ዕውቅናው የለኝም ብሏል፡፡
በሀይል መቆራረጥ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ያልገቡ ከ300 በላይ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም ከነዚህ ውስጥ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በክልሉ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶች በሀይል አቅርቦት ምክንያት በሙሉ አቅማቸዉ ወደ ምርት ስራ መግባት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ በኃይል ዕጥረት ወደ ስራ ያልገቡትን ፕሮጀክቶች ችግር ለመፍታት እስከ ሰኔ 30/2014 ዓ.ም ድረስ የጊዜ ገደብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን በቅርቡ ለዜና ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይሄነው አለም ለአዲስ ዘይቤ አንደገለፁት በክልሉ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የሀይል እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት የአጭር እና ረጀም ጊዜ ዕቅድ መቀመጡን ገልፀው የእነዚህ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ መመለስም የአጭር ጊዜ ዕቅዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ክልሉ ከፍተኛ የኃይል ዕጥረት ያለበት በመሆኑ በርካታ ፕሮጀክቶችን ወደ ማምረት ለማስገባት መቸገራቸውን ገልፀዋል።
"በክልሉ ከሚገኙ 27 የኃይል ማከፋፈያዎች (ሰብስቴሽኖች) ወስጥ አስራ አንዱ ያረጁና ከአቅም በላይ የተሸከሙ በመሆናቸውና ተገቢውን አገልግሎት እየሠጡ ባለመሆኑ በክልሉ በሚገኙ ፕሮጀክቶች ላይ የኃይል ዕጥረት ለመከሰቱ አንዱ ምክንያት ነው" ብለዋል አቶ ይሄነው፡፡
እንደ ህዝብ ግንኙኘት ኃላፊው በአጭር ጊዜ እቅዱ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ከማስገባት በተጨማሪ ኃይል ሊሸከሙ የሚችሉ የኃይል ማከፋፋያዎችን (ሰብስቴሽን) አቅም ማሳድግ እና የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶችን (ፖልና ትራንስፎርመር) በሟሟላት የኃይል ዕጥረቱን በአጭር ጊዜ ለመፍታት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በክልሉ ፕሮጀክቶችን ወደስራ ለማስገባትና ያለውን የኃይል ዕጥረት በዘላቂነት ለመፍታት ካሉት የኃይል ማከፋፈያዎች (ሰብስቴሽኖች) በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ የኃይል ማከፋፈያዎች እንደሚያስፈልጉ በጥናት መለየቱን ገልፀዋል፡፡
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የስርጭት ስርአት ቴክኒካል ድጋፍ ክፍል ኃላፊ ሽመላሽ ግርማው በበኩላቸው የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማሳደግ ከኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር እየሰሩ እንደሆነ አስረድተው ነገር ግን "እስከ ሰኔ 30/2014 ዓ.ም ድረስ የኃይል ዕጥረቱን ፈተን 200 ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ እናስገባለን የሚለው ዕቅድ መረጃ በክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘንድ እውቅና የለውም" ብለዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ኤሌክትሪክ አገልግሎቱ በክልሉ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ደንበኞችን የኃይል ችግር ለመቅረፍ ከኃይል ማከፋፋያዎች (ሰብስቴሽኖች) በቀጥታ መስመር በመዘርጋት በደብረ ማርቆስ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ኮምቦልቻና ደብረ ብርሃን ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ኃይል ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ ከተሞች የሚገኙ የኃይል ማከፋፈያዎች አዲስ በመሆናቸው ተጨማሪ አቅማቸውን የማሳደግ ስራ በመስራት እና አዲስ መስመር በመዘርጋት ኢንዱስትሪዎች ኃይል አንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
እንደ ሽመላሽ ማብራሪያ በሌሎች ከተሞች ለምሳሌ ደሴ፣ ዳንግላ፣ እንጅባራ፣ ቡሬ እና ሌሎች ከተሞች የሚገኙ የኃይል ማከፋፈያዎች የአረጁ በመሆናቸው ተጨማሪ ኃይል መሸከም ስለማይችሉ በእነዚህ ከተሞች የሚገኙ የኢንዱስትሪ ደንበኞችን ችግር በጊዜያዊነት ለመፍታት እንዳልተቻለ ተናገረዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ክልሉ ከፍተኛ የኃይል ዕጥረት ያለበት ሲሆን ለምሳሌ "እንደ ቡሬ አግሮ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አይነት ከፍተኛ ኃይል የሚጠይቅ ፓርክ በክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል ሊፈታ የማይችል ነው" ብለዋል፡፡
የክልሉን የኃይል ዕጥረት በቋሚነት ለመፍታት አሁን ካሉት 28 የኃይል ማከፋፈያዎች በተጨማሪ 32 አዳዲስ የኃይል ማከፋፈያዎች እንደሚያስፈልጉ በጥናት መለየቱን የገለፁት ኃላፊው ሽመላሽ ግርማው ከሚያስፈልጉት 32 ኃይል ማከፋፈያዎች መካከል ስድስቱ ቅድሚያ ተሰጧቸው ግንባታቸው መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ስድስት የኃይል ማከፋፈያዎች መካከል ኮምቦልቻ፣ ጭልጋ፣ ደጀንና ወልድያ ከተሞች ውስጥ የሚተከሉት ይገኙበታል፡፡