በኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድ የሚያስፈልገውን ፍቃድ በማውጣት እና ሕጉን መሠረት በማድረግ የሚሠሩ ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች መኖራቸው ይታወቃል። በተቃራኒው በመንግሥት በኩል እውቅና ሳያገኙ በህገ-ወጥ መንገድ በዚህ ስራ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ባለፈ በመንግስት እውቅና ኖሯቸው በተገቢው መንገድ ስራውን የማይሰሩ በርካታ ድርጅቶች አሉ።
ዓለም ዐቀፍ ድንጋጌዎችም ሆኑ የኢትዮጵያ አሠሪና ሠራተኛ ሕግ፣ አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ለሚሰጡት አገልግሎት ተገቢውን ጥቅም እና ገንዘብ እንዲያገኙ እንዲሁም ወደ እነርሱ ለሚቀርቡ ተገልጋዮችም ምቹ የሥራ ሁኔታ እንዲፈጥሩ ያስገድዳሉ።
ነገር ግን በአዲስ አባባ ከተማ ብቻ እንኳን በየጊዜው የሥራ ፍለጋ ኤጀንሲዎችን በር በሚያንኳኩ ግለሰቦች ላይ የሚፈጸመው ማጭበርበር የተሞላበት ድርጊት እየተበራከተ መጥቷል።
ሥራ እናስቀጥራለን በማለት የመመዝገቢያ ገንዘብ የሚሰበስቡ፣ ከሥራ ቀጣሪዎች ጋር በሚደረግ ምስጢራዊ ውል ለራሳቸው ዳጎስ ያለ የኮሚሽን ክፍያ በየወሩ የሚቀበሉ እና ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ የተሰማሩ በርካታ ኤጀንሲዎች እንዳሉ ይታወቃል። ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ሲያነሱ ይደመጣሉ። አብዛኛዎቹ በኤጀንሲዎች ተጭበርብረው ለአደጋ የሚጋለጡት ደግሞ በዝቅተኛ የስራ መደብ ላይ ለመቀጠር የሚንቀሳቀሱ ዜጎች ናቸው።
ሥራ ፈላጊን እና አሰሪን ማገናኘት ሕጋዊ መንገድ ቢዘረጋለትም፣ በሕጋዊነት ሽፋን ሕገወጥ ኤጀንሲዎች ትርፍ ከማጋበስ አልፈው የብዙ ስራ ፈላጊዎችን ሕይወት እያመሰቃቀሉት ይገኛሉ። ይህም ሊገታ እንደሚገባው በርካታ ሥራ ፈላጊዎች ደጋግመው ያሳስባሉ።
ኤጀንሲዎች የውሸት ክፍት የስራ ቦታ በማውጣት እና በተለያዩ የመንገድ መብራት ፖሎች እና ግድግዳዎች ላይ ማስታወቂያ በመለጠፍ ከስራ ፈላጊዎች በተለይም ከዲግሪ ምሩቃን ከብር 500 እስከ 5ሺህ እንደሚቀበሉ የተለያዩ ስሞታዎች ይሰማሉ።
ታዲያ የዚህ አይነቱ ማጭበርበር ሰለባ የሆኑት ሰራተኞች በሀገር ውስጥ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሚፈጸምባቸውን ዘመናዊ ባርነት ለመሸሽ ለህገ-ወጥ ስደት እየተዳረጉ እንደሚገኙ ብዙዎች ይስማሙበታል። ሰለባዎቹ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ ሰልፍም ሆነ በተለያየ መንገድ ለማሰማት የመደራጀት መብት ተነፍጎናል ሲሉ በተለያየ ጊዜ ቅሬታ እንደሚያነሱ ከአዲስ አበባ ሴቶች ፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ይህንንም ለማስተካከል እና ስርዓት ለማስያዝ ቢሮው የተለያዩ ስራዎችን እንደሚሰራ ተጠቁሟል።
ምንም እንኳን ሕጉን ጥሰው የሚንቀሳቀሱ ኤጀንሲዎች ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሥራ ፈቃድ ወስደው እንደሚሠሩ ቢናገሩም፣ እውነቱና በተግባር የሚታየው ግን ሌላ ነው። በተግባር እንደሚስተዋለው ከሆነ፣ ሥራ ፈላጊዎችን እና ሥራ ቀጣሪ ተቋማትን እናገናኛለን የሚሉት እነዚህ ኤጀንሲዎች በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ሕንፃዎች ላይ ቢሮ ይከራያሉ። በተለያዩ በከተማዋ ዕምብርት ቦታዎችም ‘የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ’ በሚል የሐሰት ማኅተም ያረፈባቸው በራሪ ወረቀቶች ይለጥፋሉ።
ራዲያ ከድር የተባለች አስተያየት ሰጪያችን “የሥራ ቅጥር ማስታወቂያውን የተመለከትን ሥራ ፈላጊ ዜጎች ኤጀንሲዎች በተከራዩባቸው ሕንፃ ቢሮ ተገኝተን እንመዘገባለን፣ በዚህም ለአገልግሎት፣ ለአስተዳደር ወጭ እና ለሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮች እየተባለ ከመቶ ብር ጀምሮ እስከ ስድስት መቶ ብር፣ አንዳንዴም ከዚያ በላይ ቅድመ ክፍያ እንድንከፍል እንገደዳለን” ስትል ትናገራለች።
ታድያ እነዚህ በሥራ ዕጦት በአካልም በመንፈስም የሚቸገሩ ዜጎች፣ ለኤጀንሲዎች የሚከፍሉት ብር እንደወጣ መና ከመቅረቱና ከመበዝበዛቸው ባሻገር ሌላም ችግር ያጋጥማቸዋል። ሥራ የሚያገኙበት ሒደት ካለመመቻቸቱና ከአንድ እና ሁለት ሳምንት በኋላ ለኤጀንሲዎቹ ድጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ አጥጋቢ መልስ ካለማግኘታቸው ባለፈ እንደእድል ሆኖ ስራውን ካገኙ ደግሞ የኮሚሽን ተብሎ የሚቆረጥባቸው የገንዘብ መጠን በእጅጉ ከልክ ያለፈ እና እስከ 50% የሚደርስ ነው።
ሌላኛው ባለታሪካችን አዳም ይሁኔ ይባላል፤ ስራ ለመቀጠር እየፈለገ ባለበት ወቅት ከጓደኛው ባገኘው ጥቆማ መሰረት ‘ጌት ቱ ወርክ’ ወደተባለ ሰራተኞችን የሚያስቀጥር ኤጀንሲ ይሄዳል። "የ10ኛ ክፍል ውጤት እና ዋስ ካመጣህ ስራ መጀመር ትችላለህ" በሚል ለቀጣዩ ቀን ቀጠሮ ይሰጡታል። በቀጠሮው ቀን የተጠየቀውን አሟልቶ ጀሞ አካባቢ በሚገኝ አንድ ሱፐርማርኬት ውስጥ በጥበቃነት እንደሚሰራ ተነግሮት ወደቦታው ይሄዳል።
“በቦታው ስደርስ ግን ስለስራው ገለፃ ሲደረግልኝ የምሰራው ጥበቃነት ሳይሆን እቃ አውራጅነት መሆኑን አወቅኩ" በማለት 'ስራ መፈለጊያ ይሆናል' በሚል በስራው ለመቀጠል መወሰኑን ነግሮናል።
በተመሳሳይ በተመላላሽ የቤት ሰራተኝነት የምትተዳደር እና ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች አስተያየት ሰጪ ምንም እንኳን እሷ የሄደችበት ኤጀንሲ የፈለገችውን ስራ ያስያዛት ቢሆንም ለተወሰኑ ወራት ብቻ በስራው መቆየቷን ትናገራለች። ስራውን ያለመቀጠሏ አንዱ ምክንያት የደሞዝ አከፋፈል ሂደቱ ላይ ቅሬታ ስላደረባት መሆኑን ገልፃለች።
"የገንዘብ መጠኑ በየወሩ ይለያያል" ያለች ሲሆን ይህም ከ1,600 እስከ 1,800 ብር ውስጥ ነበር። ለቅጥር የወጣው የክፍያ መጠን 2 ሺህ ብር እንደነበር የምታስታውስ ሲሆን ከነበረው ልዩነት በተጨማሪ ስራ ያስያዛት ኤጀንሲ የምታገኘውን ገንዘብ ግማሹን እንደሚወስድ ነግራናለች። እንደ ወጣቷ ገለፃ ከስራዋ ለመልቀቅ እንኳን ብታስብ ከመልቀቋ በፊት በተቀጠረችበት ቤት ያለ ክፍያ ለ15 ቀናት ማገልገል ይጠበቅባታል። አሰሪው ለእነዚህ 15 ቀናት የሚከፍላትን ገንዘብ በሙሉ ኤጀንሲው ሙሉ ለሙሉ ይወስዳል።
ቅጥር ከመፈጸሙ አስቀድሞ ''የስራ ማስታወቂያ ያለበትን ቦታ ለመጠቆም ብቻ ኪፕ ታይም ኤጀንሲ 800 ብር አስከፍሎኛል'' የምትለው ደግሞ መቅደስ የኔሁን የተባለች ወጣት ናት። በተማረችበት የሙያ ዘርፍ ማስታወቂያ ያለበትን ቦታ ለመጠቆም ፣ እንዲሁም በማንኛውም የስራ ዘርፍ ስራ ይገኛል ብለዋት ቅድመ ክፍያ መክፈሏን ትናገራለች።
“የተጋነነ የደሞዝ መጠን በመጥራት ክፍት የስራ ማስታወቂያ አለበት ወደ ተባለው ቦታ ገንዘብ አስከፍለው ይጠቁማሉ” የምትለው መቅደስ ወደተጠቆመቻቸው ቦታዎች ስትደርስ ግን አንዳንዶቹ ማስታወቂያዎች የወጡበት ጊዜ ካለፈ ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ ሆነው አግኝታቸዋለች።
ቅሬታ ከቀረበባቸው ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኪፕ ታይም ኤጀንሲ የሽያጭ ባለሙያ “ኤጀንሲው ቀጣሪ እንደመሆኑ ከተቀጣሪዎቹ ጋር የሚኖረው ስምምነት እንደአሰሪ ነው” በማለት ለተቀጣሪዎች ኤጀንሲው ይሆናል ያለውን የገንዘብ መጠን አውጥቶ ቅጥር እንደሚፈጽም ተናግረዋል።
ኤጀንሲው ለሰራተኛው የሚያወጣው ወጪ እንዲሁም የሚከፍለው ደሞዝ በኤጀንሲው እና በአሰሪው መካከል የሚያልቅ እንጂ ከተቀጣሪው ክፍያ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ አለመኖሩን ገልጸው “ክፍያው ለስራው በቂ ነው ወይስ አይደለም?” የሚለውን ተቀጣሪዎቹ ቀድመው አስበውበት መቀጠር ይገባቸዋልም ብለዋል።
'ከተጠቀሰው የደሞዝ መጠን በታች ክፍያ ይፈጸማል' ተብሎ ለተነሳው ቅሬታ ''ያልተጣራ ደሞዝ ከሆነ ለመንግስት ግብር ሊቆረጥ ይችላል፤ ነገር ግን ይሄን ሲቀጠሩ እናሳውቃለን፤ ከቀጣሪው ድርጀት ጋርም የተጣራ እና ያልተጣራ ክፍያ የሚባለውን በውላችን ላይ በግልጽ እናስቀምጣለን'' ብለዋል።
ስለዚህ እንደ ባለሙያው ገለጻ አሰሪው ድርጅት ከሚያወጣው ገንዘብ ላይ 50 በመቶ፣ ከዛ በታች ወይም በላይ ይቆረጣል የሚለው ሀሳብ ኤጀንሲው ከሚያወጣው ወጪ አንጻር ከድርጅቱ ጋር በሚዋዋለው ውል የሚወሰን እንጂ የተቀጣሪዎችን ደሞዝ የሚነካ አሊያም የነሱን ስምምነት የሚፈልግ አይደለም።
ሌላው በኤጀንሲ ስራ ላይ ተሰማርቶ ከሚገኝ እና ስሙ እንዳይጠቀስ ከፈለገ ግለሰብ ባገኘነው መረጃ መሰረት ሰራተኞቹ ውላቸውን የሚፈጽሙት ከኤጀንሲዎች ጋር እንደመሆኑ ክፍያው የሚፈፀመው በኤጀንሲው በኩል ነው። በኤጀንሲዎች በኩል ቅጥር የሚፈፅመው ድርጅት እና አስቀጣሪው ኤጀንሲ በሚኖራቸው ውል መሰረት ተቀጣሪዎቹ የሚከፈላቸው ክፍያ እና ኤጀንሲዎቹ የሚያገኘው የገንዘብ መጠን ይወሰናል። ማለትም አንድ ድርጀት ለአንድ ተቀጣሪ ለመክፈል ካስቀመጠው የደሞዝ እርከን በተጨማሪ ለመንግስት የሚከፈል ቀረጥ፣ ለሰራተኞች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እና ለአገልግሎት ወጪ ያደርጋል።
ኤጀንሲውም ከድርጅቱ የሚቀበለውን ገንዘብ ከሰራተኞቹ ጋር ባለው ውል መሰረት ክፍያ የሚፈጽመው እንዲሁም አንድ ቀጣሪ ሊያደርገው የሚገባውን ለመንግስት የሚከፈል ግብር ጨምሮ ሙሉ ሂደቱ በኤጀንሲዎቹ ይከናወናል። አንድ ኤጀንሲ ከአንድ ድርጀት ጋር ለመዋዋል ለአንድ ተቀጣሪ ይሄን ያህል ገንዘብ ድርጅቱ ቢያወጣ ተብሎ ኤጀንሲው በሚያስገባው የገንዘብ መጠን ተወዳድሮ (በጨረታ) አሸናፊ ለሆነው ማለትም ድርጅቱ አነስተኛ የገንዘብ መጠን ለጠየቀው ኤጀንሲ ስራውን ይሰጣል። ከዚያም ለተቀጣሪዎች የሚከፈለው መጠን እና ሌሎች ወጪዎች ታሳቢ ተደርገው ከሰራተኞቹ ጋር ውል ይፈጸማል።
በተመሳሳይ አሰሪው ድርጀት ተቀጣሪውን ከስራ ማሰናበት ቢፈልግ በአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጅ ላይ እንደተደነገገው የስራ መፈለጊያ ጊዜ ከአሰሪው ጋር የሚፈፀም አይሆንም። ድርጅቱ ያለማስጠንቀቂያ በፈለገበት ጊዜ ቢያሰናብት ለተቀጣሪው ቀጣይ እጣፈንታ ወይም ተቀያሪ ስራ መፈለግ የሚገባው ኤጀንሲው ይሆናል።
የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተርም የቀረቡትን ስሞታዎች በመያዝ ጉዳዩ ወደሚመለከተው የአዲስ አበባ የስራ እና የኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ በማምራት በዚህ ዙሪያ ስላለው የህግ ድንጋጌ እና ቢሮው ህገወጦችን ለመቆጣጠር ስለሚተገብረው ስራ ጥያቄ አንስታለች።
በቢሮው የስራ ስምሪት ማስፋፊያ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ጥላዬ አለማየሁ እንደሚገልጹት የደሞዝ አከፋፈል ስርአቱ የሚወሰነው በኤጀንሲው እና በቀጣሪው ስምምነት ሲሆን ኤጀንሲው የሚያገኘው ገንዘብ ከተቀጣሪው ክፍያ ላይ መሆን አይችልም። ''ከሰራተኛው ላይ 5 ሳንቲም መቀነስ የለበትም'' የሚሉት አቶ በላይ 20 በ 80 በሚባለው አሰራር በሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ በወጣ አዋጅ መሰረት መሆኑንም ገልጸዋል። ይህም አሰሪው ለሰራተኛው ከሚያውለው ገንዘብ ላይ 20 በመቶ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚከፈል እና 80 በመቶው ለተቀጣሪው ክፍያ የሚውል ይሆናል።
500 የሚደርሱ ኤጀንሲዎች ከሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ንግድ ቢሮ እና ፌደራል ፖሊስ ፍቃድ ወስደው እንደሚገኙ ኃላፊው ገልጸው ከዚህ ውስጥ 144 የሚሆኑ ኤጀንሲዎች በአሰራራቸው ችግር ሳቢያ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው እንዲሁም መሰናበት ያለባቸው ኤጀንሲዎች መኖራቸውን ይናገራሉ። 103 ድርጅቶች ብቻ ፍቃዳቸውን አድሰው በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን ያለ ፍቃድ የሚሰሩ ኤጀንሲዎች ካሉ ንግድ ቢሮ የሚከታተለው ይሆናል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት በጥቃቅን እና አነስተኛ እንዲሁም ኅብረት ስራ አመራር ከተደራጁ በኋላ ይህን በራሳቸው ቀይረው በአሰሪ እና ሰራተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች አሉ፤ ይህም ትክክል አይደለም። የሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ አሰራር እና ህግን ተላልፎ የሚገኝን አካል በአዋጅ 618 መሰረት ከ5 ዓመት ባላነሰ ከ10 ዓመት ባልበለጠ እና 100ሺ ብር መቀጮ ይቀጣል በማለት ተናግረዋል።
''ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ የብቃት ማረጋገጫ ከሌላቸው ኤጀንሲዎች ጋር ውል የሚፈጽም አሰሪ በጉዳዩ ኃላፊነት ይወስዳል'' የሚሉት ሀላፊው በስራ ሂደት ለሚያጋጥም ችግር ተቀጣሪዎች ለቢሮው ቅሬታ እንዲያቀርቡ እና መፍትሄ እንዲያገኙ ጠቁመዋል። አያይዘውም ማንኛውም አሰሪም ሆነ ሰራተኛ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር በውል ከመተሳሰሩ በፊት ህጋዊነታቸውን እንዲያረጋግጥ በማሳሰብ ህጋዊ መሆኑን ማሳየት የማይፈልግ ተቋም ካለ ማህበረሰቡ ጥቆማ እንዲያደርግ አሳስበዋል።