ሰኔ 20 ፣ 2014

“ዱብሻ’’ የጋሞዎች ባህላዊ የፍትህ አደባባይ

City: Hawassaባህል የአኗኗር ዘይቤ

በዚህ አደባባይ ጋሞዎች ፈጣሪ በመካከላችን አለ ብለው ስለሚያምኑ ውሸት አይናገሩም

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

“ዱብሻ’’  የጋሞዎች ባህላዊ የፍትህ አደባባይ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማቴዎስ ኦሶ

እዉነትና ንጋት እያደረ ይጠራል የሚል ብሂል በጋሞዎች ዘንድ አይሰራም ። ማንኛውም ቅሬታ እና አለመግባባት ዱብሻ በተሰኘው ባህላዊው የፍትህ ጉባኤ ላይ በግልጽ ቀርቦና ቀጥታ ውይይት ተደርጎበት ምላሽ ያገኛል። 

ህገ-ደንብ የሚወጣበት እና የሚሻሻልበት ፣ ቃለ-መሃላ የሚፈፀምበት ፣ የእርቅ ስነስርዓት የሚከወንበት በአጠቃላይ በማህበረሰቡ ዉስጥ የተፈጠሩ አለመግባባቶች አልያም ቅራኔዎች በባህላዊ ስርዓት መፍትሄ የሚያገኙበት ሸንጎ ነው፣ ዱብሻ።

“ዱብሻ’’  የጋሞ  ቃል ሲሆን ትርጉሙ የመሰብሰቢያ አደባባይ ማለት ነዉ ። ይህ የመሰብሰቢያ ቦታ ተፈጥሯዊ በሆኑ ዛፎች እና ሳሮች እንዲሁም ለስርዓቱ ተብለው በተዘጋጁ መቀመጫዎች የተሞላ ሰፊ ስፍራ ነዉ ። የህዝቦች አንድነት ላይ የተመሰረተን ጥንካሬ ያሳያል ተብሎ የሚታመነውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ቀለሙን ሳይለቅ እስካሁን ድረስ የዘለቀው የጋሞዎች ለፍትህ የመሰባሰብ ባህል በአደባባይ የሚከናወንና በህብረተሰቡም ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ስርዓት ነው። 

ፎቶ፡ ማቴዎስ ኦሶ

“የዱብሻ ባህላዊ የፍትህ ስርዓት ላይ ጋሞዎች ከሀገር ሽማግሌዎችና ከአለቆች ጋር በቀጥታ ተገናኝተው ህግ ያወጣሉ፣ መተዳደሪያ ደንብም ያፀድቃሉ” ያሉን የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙናዬ መሰለ ናቸው። ሃላፊው እንደሚሉት በህብረተሰቡ መካከል ያሉ አለመግባባቶችና ግጭቶችም በድጋሚ እንዳይፈጠሩ ሰዎች በዚሁ አደባባይ መሐላ ይፈጽማሉ። 

በጋሞ ዞን ውስጥ የሚገኙ 16 ገጠራማ ቀበሌዎችና 4 ከተማዎች ሲኖሩ እነዚህ ቀበሌዎችና ከተሞች በኦቼሎ ፣ ጋንታ ፣ ጋቾ፣ ጪንቻ ፣ ኩቻ ፣ ቦሮዳ ፣ ባባና ኢልጎ ወረዳዎች ውስጥ ይገኛሉ። በእነዚህ ወረዳዎች በአጠቃላይ ከ600 በላይ ዱብሻዎች ሲገኙ እነዚህ ዱብሻዎች ከእነሱ በላይ ለሆነውና ደሬ ተብሎ ለሚጠራው መዋቅር ተጠሪ ናቸው። 

ደሬ ማለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት (supreme court) ከሚባለው ዘመናዊ የፍትህ መድረክ ጋር የሚመሳሰል ሲሆን በጋሞ ውስጥ የሚገኘው ታላቁ ባህላዊ ሸንጎ እንደሆነም አቶ ሙናዬ መሰለ ይናገራሉ። ዱብሻ ፣ ንዑስ ደሬ ከዚህ መዋቅር በታች ደግሞ የጎሳ እና የመንደር ( የጉታ) ዱብሻዎችን አቅፎ ይዟል ። የደሬ ዱብሻ ፣ በታችኛው የዱብሻ እርከኖች ሊፈቱ ያልቻሉ ትልልቅ ጉዳዮች ፍትህ የሚያገኙበት ታላቁ ጉባኤ ነዉ ።

ንዑስ ደሬ ዱብሻ ተብሎ በሁለተኛነት የተቀመጠዉ የፍትህ መድረክ በቀበሌዎች የተከሰቱ ቅሬታዎች እና አለመግባባቶች የሚዳኙበት አደባባይ ነዉ። ሌላዉ ብዙም ስራ ላይ የማይውለው “ጎሳ ዱብሻ’’ ተብሎ የሚጠራዉ የደሬ አይነት ነዉ ። የጎሳ ዱብሻ በአንድ ቦታ የተወሰነ አይደለም ፤ አንድ የጎሳ አባል ከሌላ ጎሳ አባል ጋር ቅሬታ ዉስጥ ገብቶ ሲገኝ በመሐከላቸው እርቅ እንዲወርድ የሚነጋገሩበት ቦታ ነዉ ።

በዱብሻ መዋቅር ዉስጥ ተካቶ የሚገኘዉ እና የመጨረሻው ትንሹ የእርከን ደረጃ የሆነዉ “የመንደር ( የጉታ)” ዱብሻ የሚባለዉ ነዉ ። በቤተሰብና በጎረቤት መካከል እንዲሁም በሰፈር ዉስጥ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ የአካባቢው ሰዉ የሚሳተፍበት የፍትህ ስርዓት እንደሆነ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል ።

የጋሞ ዞን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙናዬ መሰለ “ማንም እማኝ በሌለበት ቦታ የተፈፀሙ የግድያ ወንጀሎች ፣ በድብቅ ስርቆት የፈፀመ እና ሌሎች ከህዝብ የተሰወሩ ድርጊቶች በዱብሻ ባህላዊ የፍትህ ስርዓት እዉነቱ እንዲወጣ ይደረጋል’’ ይላሉ። 

በ2013 ዓ.ም. የተከናወነ የዱብሻ ዳኝነት ስርዓት ያጫወቱን አቶ ሙናዬ ይህ ባህላዊ ሸንጎ በጋሞ ማህበረሰብ ዘንድ ምን ያህል እምነት እንደሚጣልበት ያሳያል። 

በጋሞ ዞን በሚገኝ በአንድ ወረዳ የመብራት መስመር ሲዘረጋ መብራት ያልተዘረጋበት ተጎራባች ወረዳ ውስጥ የሚኖሩትን ወጣቶችን አስቆጣ። ጥያቄአቸው እኩል አገልግሎት ልናገኝ ይገባል የሚል ተገቢ ቅሬታ ነበር። ነገር ግን ምሽትን ተገን በማድረግ እነዚህ ቁጡ ወጣቶች ወደጎረቤት ወረዳ ሄደው የኤሌክትሪክ ፖሎቹን በመነቃቀል ከጥቅም ዉጪ አደረጓቸው። መረጃ የደረሰው የአካባቢው ፖሊስ ወንጀሉን ፈፅመዋል በሚል የጠረጠራቸውን 50 ልጆች በማሰር በእርግጥ ማን ድርጊቱን እንደፈጸመ በተለያዩ መንገዶች ለማወጣጣት ቢሞክርም ሊሳካለት አልቻለም ። ይህን የተመለከቱ በወረዳዉ ያሉ ካዎ (ባህላዊ መሪ) ፣ አለቆች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት መሪዎች፣ ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ አደባባይ (ዱብሻ) እንዲወጡ አደረጉ። በዚህ ዱብሻ ላይ በወንጀሉ ተሳትፈዋል ተብለዉ የተጠረጠሩት 50 ወጣቶች መሐላ ከፈፅሙ በኋላ እውነቱን እንዲያወጡ ተጠየቁ። መሃላውን በመፍራትና በማክበር ዘጠኝ ልጆች ወንጀሉን ፈፅመናል በማለት እዉነታዉን ከ 4 ሺህ ህዝብ በላይ በተሰበሰበበት አደባባይ ላይ ተናገሩ። “በስተመጨረሻም ፖሊስ ሊፈታው ያልተቻለዉን ጉዳይ ዱብሻ መፍትሄ ሰጠው” ብለዋል ሃላፊው አቶ ሙናዬ። 

ፎቶ፡ ማቴዎስ ኦሶ

በዱብሻ አደባባይ ላይ የፍትህ ስርዓቱን በዳኝነት፣ በተጠያቂነት እንዲሁም በታዳሚነት ለመሳተፍ የተሰየመ ማንኛውም ግለሰብ በዚያ ስፍራ፣ በሰዎቹ መካከል ፈጣሪ አለ፣ የሚዳኘውም እርሱ ነዉ የሚል እምነት ስላላቸዉ ዉሸትን ፈፅሞ አይናገሩም ። 

ለእነርሱ ሐሰትን መናገር በቤተሰባቸው እንዲሁም በራሳቸዉ ላይ ያልተጠበቀ የሞት አደጋ ይደርሳል፣ ሀብት እና ንብረት ሊያጠፋ ይችላል የሚል እምነት ስላላቸዉ ለእዉነት ብቻ ይቆማሉ ። 

የባህላዊ ሸንጎ ስርዓቱን ለመታደም ወደ ዱብሻ የሚመጡ አባላት በጋሞኛ ጫምባሮ ተብሎ የሚጠራዉን በብር ወይም በነሃስ ጥምዝ የተጌጠዉን አንካሴ መሰል ምርኩዝ የክብር ዘንግ ይዘዉ ይመጣሉ ። ይሁን እንጂ ወደ እርቅ አደባባዩ የሚገቡት ሁሉም ታዳሚ ፀምባሮዉን በዱብሻ ፊት ለፊት መሬት ላይ ሰክተው ነው። 

“ይህን ባህላዊ የፍትህ ስርዓት በአለም አቀፍ ደረጃ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የዞኑ አስተዳደርና ቱሪዝም ቢሮ የተለያዩ ስራዎች እየሰሩ ነው ነገር ግን በቂ አይደለም” የሚሉት አቶ ሙናዬ፣ መጀመሪያ ግን ስርዓቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲታወቅ እንዲሁም ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲቆይ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል። 

አስተያየት