ጎንደሮች እስክስታ ለማቅረብ ከውዝዋዜ በፊት ባለባበሳቸው፣ በጌጣጌጣቸውና በጸጉር አሰራራቸው ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። እስክስታ ሲቀርብ መሰረታዊ አላማዎቹ ደስታን ማብሰር፣ በአላት ማድመቅ፣ ባህልና ትውፊትን መግለፅ፣ የጀግኖችን የጦርነት ውሎ መዘከርና ጥበብን ማስተላለፍ ነው።
በውዝዋዜ ጊዜ ወንዶች በአብዛኛው የተዋጊዎችን እንዲሁም የመሳፍንቱንና የመኳንንቱን አለባበስ የሚወክሉ አልባሳትን ይጎናፀፋሉ። ተዋዛዋዦቹ የጀግና ተዋጊ ፋኖ ማሳያ የሆነውን ቀይ ምልክት በግንባራቸው አስረው እጀ ጠባብ ለብሰውና ባተሁለት (ከጉልበታቸው ዝቅ ብሎ ባታቸው ላይ ጥብቅ አድርጎ የሚይዝ ሱሪ) ታጥቀው በወገባቸው ድግ አደግድገው፣ ዝናር ታጥቀው ውዝዋዜውን ሊከውኑ ይችላሉ። ድግ ማለት ወንዶች ወገባቸውን የሚያስሩበት ቀይ ጥለት ነው፤ ለጎራዴ ወይም ሽጉጥ መያዣነትም ያገለግላል።
ሴቶች በውዝዋዜ ጊዜ ከራስ ጸጉራቸው እስከ እግራቸው በልዩ ልዩ ማስጌጫዎች ይዋባሉ። ይህም ቁንጅናቸውን ከማጉላትም በተጨማሪ የሙያ ደረጃቸውንና የጥበብ ባለቤት መሆናቸውን ያሳዩበታል።
ጥበብንና ጀግንነትን ለመግለጽ ጸጉራቸውን ጎፈሬ ወይም ሹርባ (ቁንዳላ) ተሰርተው ጥልፍ ቀሚስ ለብሰው በጀርባቸው አገልግል ወይም በጉንፋቸው (በክንዳቸው) ስንቅ ተሸክመው ሊወዛወዙ ይችላሉ።
የጎንደርን ሙዚቃ ስንመለከት ከሌሎች የሙዚቃ ውዝዋዜውች ለየት የሚያደርጋቸው እያንዳንዱ የውዝዋዜ አይነቶች ትርጉም አዘል መሆናቸውን ነው።
አዲስ ዘይቤ ወደ ጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አቅንታ የባህልና ቱሪዝም እሴት ቡድን መሪ የሆኑትን አቶ ልዕልና አበበን በማነጋገር የሚከተለውን ይዛ ተመልሳለች።
ሽብሻቦ
ሙዚቃው ሲጀመር እንደ እስክስታ መግቢያ የሚጠቀሙት ሽብሻቦ ይባላል። የሽብሻቦ ዋና መልዕክት ጠላት መጣ ሃገር ተወረረ ሲባል ጎራዴውን ፣ ጦርና ጋሻውን እንዲሁም ጠመንጃውን ከግድግዳው አውርዶ፣ ወልውሎ፣ ፈረሱን ጭኖ፣ ስንቁን ቋጥሮ፣ እንደሚዘምተው ሁሉ በሽብሻቦ ጊዜ ወንዶች የጦር፣ የጋሻ፣ የጎራዴና የነፍጥ ውልዋሎ ዓይነት ትዕይንት ሲያሳዩ፣ ሴቶች ደግሞ ስንቅ የማዘጋጀት ዓይነት ትዕይንት ያሳያሉ።
ወንዶች የእጃቸውን መዳፍ በግንባራቸው ትይዩ ወደላይ አድርገው መዳፋቸውን እያፋጩ ሲያሸበሽቡ ትርጉሙም ትጥቃቸውን የመወልወልና ለጦርነት የማዘጋጀት ምሳሌ ነው። ሴቶች ሲያሸበሽቡ የመቀነታቸውን ጫፍና ጫፍ በእጃቸው ጨብጠው ከአንገታቸው ሰበር ከወገባቸው ዘንበል በማለት ግራ ቀኝ እያማተሩ ይወዛወዛሉ። ይህም እንደፉከራ ጀግና ነኝ ለማለት የሚጠቀሙበት ነው።
የሴቶች ጎንደርኛ የውዝዋዜ አይነቶች ከሚባሉት ውስጥ ጥቂቶቹን ስንመለከት ጉች ጉች ፣ ዶሮ ውሃ ሲጠጣ ፣ ስክስክ ፣ ድስቅ ፣ ቅቤ መናጥ ፣ እንዝርት ፣ ማንጠርጠር ፣ ዋንጫ ልቅለቃ ተጠቃሽ ናቸው።
ሴቶች ይሄን እስክስታ ሲያቀርቡ ሊያስተላልፉት የፈለጉት መልዕክት ጨዋ ሴት ልትተገብረው የምትችላቸውን ነገሮች በአቋቋማቸው ፣ በአለባበሳቸው ፣ በዓይን አጣጣላቸው ፣ በፈገግታቸው ፣ በጸጉር አሰራራቸው ፣ በጌጣጌጦቻቸው እንዲሁም ክብራቸውን ፣ ማዕረጋቸውንና ሞያቸውን በሚያንጸባርቅ መልኩ ደምቀው ያቀርባሉ።
ጉች ጉች
በውዝዋዜ ወቅት ከሚያሳዩት የእስክስታ ትዕይንት አንዱ ጉች ጉች ይባላል። ይህ እስክስታ አንዲት ሴት ጥበበኛና ባለሙያ ከሚያሰኟት ነገሮች ውስጥ አንዱ እንጀራ መጋገር በመሆኑ ይህ ውዝዋዜ ሲጨፈር ሴቷ በእግሯ መዳፍ ቁጢጥ በማለት እየተሽከረከረችና ክብ በመስራት ዙሪያውን በመዞር የሴት ወይዘሮ መሆኗን እና የእንጀራ መጋገር ሙያ እንዳላት የምትገልጽበት የእስክስታ አይነት ነው።
ዶሮ ውሃ ሲጠጣ
ሁለተኛው የእስክስታ አይነት ዶሮ ውሃ ሲጠጣ ይባላል። ይህ አይነት ውዝዋዜ ዶሮ ውሃ ሊጠጣ ከሚያደርገው የዶሮ ተፈጥሮ የተወሰደ የእንቅስቃሴ አይነት ሲሆን በታዳሚው አዕምሮ ውስጥ እንዲቀረጽ የተፈለገው ዋና ቁም ነገር የሴቷን የዶሮ ወጥ ሙያ ለመግለጽ ነው። ሲጨፈርም ሴቷ የመቀነቷን ጫፍና ጫፍ በመያዝ እጆቿን ወደ ጎን በመዘርጋት ቀስ በቀስ ከወገቧ ዘንበል እያለች ወደ ታች በመውረድ ልክ ዶሮ ውሃ ሊጠጣ ሲል እንደሚያደርገው ተወዛዋዧም አንገቷን ዝቅ ከፍ እያደረገች የምትወዛወዘው ውዝዋዜ አይነት ነው።
ሰክስክ
ሶስተኛው የእስክስታ አይነት ሰክስክ የሚባለው ሲሆን በዚህ የእስክስታ አይነት ሊተላለፍ የተፈለገው መልዕክት የሴቷን አሳ የመስራት ሞያ ነው። አንድ አሞራ ወደ ወንዝ አሳ ለመያዝ ሂዶ ከያዘ በኋላ አንገቱን ዝቅ ያደርግና ከወደ አፉ ቀና በማለት አሳውን ለመዋጥ የሚያደርገውን ትግልና ትዕይንት መሰረት ተደርጎ የተቀዳ የውዝዋዜ አይነት ነው። አጨፋፈሩም የመቀነቷን ጫፍ እና ጫፍ በመያዝ ከአንገቷ ሰበር ከወገቧ ዘንበል በማለት ልክ አሞራ አሳ በማንቁሩ እንደሚያነሳው አንገቷን ወደላይ ቀና በማድረግ በአንገትዋና በትከሻዋ ወደ ላይና ወደ ታች እየወዘወዘች ትጨፍራለች።
ድስቅ
ጌጣጌጦችን አሳምረው መስራት እንደሚችሉ ለማሳየት ደግሞ ድስቅ የሚባለውን የውዝዋዜ አይነት ይጠቀማሉ። ውዝዋዜው የሚጨፈረው በደረትና በትከሻ ሲሆን በሰርግ እና በተለያዩ ሃይማኖታዊ በአላቶች ላይ ሴቶች ለመልካቸው ውበት የሚያላብሳቸውን የሞያ እና የእመቤትነት ማዕረግ የሚያጎናጽፋቸውን ጌጣጌጦች በጸጉራቸው፣ በእጃቸው እና በ አንገታቸው አድርገው ይሄዳሉ።
እነዚህን ጌጣጌጦች የሚያዘጋጁዋቸው ራሳቸው መሆናቸውን ለማሳየት ድስቅ የተሰኘውን ውዝዋዜ ይጨፍራሉ። ይህ እስክስታ ሲመታ በደረታቸውና በትከሻቸው በሃይል ስለሚመታ አንገታቸው ላይ ያለው ጌጣጌጥ ዕርስ በእራሱ እየተላተመ ድምጽ ያሰማል። የብዙ ሰዎችን ቀልብም ይገዛል። የሰሯቸው ማጌጫዎች ጥራትና ውበት ይታያል። የሞያ ደረጃቸውን ከፍ አድርጎ ያሳያል።
ቅቤ መናጥ
አምስተኛው የውዝዋዜ አይነት ቅቤ መናጥ ይባላል። ይህ ውዝዋዜ ሴቷ ስትወዛወዝ በርከክ ብላ የመቀነቷን ጫፍና ጫፍ በእጆቿ በመያዝ እጆቿን ወደፊት እና ወደኋላ እየዘረጋችና እያጠፈች የምትወዛወዘው ሲሆን ሊተላለፍ የተፈለገው ጉረና (ወተት የሚያዝበት እቃ) እየገፋች እና እየናጠች ቅቤ ለማውጣት የሚደረገውን ትዕይንት ለመግለጽ ነው። እንዲሁም የነጠላዋን ጫፍና ጫፍ በትከሻዋ እንዲወርድ አድርጋ በሁለት እጆቿ ጫፍና ጫፉን ከያዘች በኋላ ረጋ ብላ በቀስታ በመነቅነቅ አይነት ትወዛወዛላች። ይህም የወተት መናጫውን ማሰሪያ ገመድ ይዛ ወተቱ እንዳይደፋባት (እንዳይሸፍትባት) ቅቤው እንዲወጣ የመሰብሰብ አይነት ውዝዋዜ ነው።
እንዝርት
ፈትል፣ ጥልፍና የተለያዩ አልባሳት አስጊጠውና አሳምረው መስራት እንደሚችሉ ለማሳየት ደግሞ እንዝርት የሚባለውን የእስክስታ ትዕይንት ሴቶች ይከውናሉ። የእንዝርት አሿሿርን መሰረት አድርገው በእጆቻቸው ቀሚሳቸውን ከጎንና ከጎን በመለጠጥ ልክ እንደ እንዝርት እየሾሩና እየተሽከረከሩ ይጨፍራሉ። እንዲሁም ቀጭን ፈታይ ባለሙያ ስለመሆናቸው ለመግለጽም ይጠቀሙበታል።
አቀራረቡም ልክ እንዝርት እንደያዙ በማስመሰል በጣቶቻቸው የመቀነታቸውን ጫፍ ይዘው እጃቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት የላይኛውን መቀነታቸውን ጫፍ በጣቶቻቸው ጥጥ እንደያዙ በማስመሰል በመፍተል አይነት እንቅስቃሴ ይወዛወዛሉ። ቁጭ ብለው ሲወዛወዙ በ አንደኛው እግራቸው በኩል ያለውን ቀሚሳቸውን ሰብሰብ አድርገው እንዝርት እያሾሩ የሚፈትሉ በማስመሰል ይወዛወዛሉ። እንዝርትና ጥጥ ይዘው እየፈተሉ ሊወዛወዙም ይችላሉ።
ዋንጫ ልቅለቃ
ሰባተኛው ዋንጫ ልቅለቃ የተባለው የውዝዋዜ አይነት ነው። የሴቷን የወይን አዘገጃጀት የጠጅ አጣጣል የጠላ አጠማመቅና ልዩ ልዩ መጠጥ ማዘጋጀት እንደምትችል እና ባለሙያ መሆኗን ለማሳየት ዋንጫ ልቅለቃ የውዝዋዜ አይነትን ይጠቀማሉ።
በዚህ ውዝዋዜ እሷ ያዘጋጀችውን ወይን፣ የጠመቀችውን ጠላ ፣ የጣለችውን ጠጅ ማንም ቀምሶ አይተወውም። የተሰጠውን መጠጥ ከመጣፈጡ የተነሳ ልቅልቅ (ጭልጥ) አድርገው እንጠፍጣፊ ሳያስቀሩ እንደሚጠጡት ማሳያ ነው። በሌላ ጎን ደግሞ ከላይ በተጠቀሰው ሃሳብ በተቃራኒ የጠላ ወይም የጠጅ መጠጫውን ሌላ ቃና እንዳይኖረው በጠጅ ወይም በጠላ ያለቀልቁ ስለነበር ነው ዋንጫ ልቅለቃ የተባለው የሚሉም አሉ።
ይህ የእስክስታ አይነት ሴቷ የመቀነቷን ጫፍና ጫፍ ከቀሚሷ ጋር ደርባ በመያዝና ወገቧ ላይ እጆቿን አድርጋ አንገቷን በእርጋታ ከግራ ወደ ቀኝ ፣ ከቀኝ ወደ ግራ ልክ ዋንጫ እንደሚለቀለቅ ተደርጎ በመነቅነቅ በማሽከርከር የሚጨፈር የእስክስታ አይነት ነው።
ማንጠርጠር
ስምንተኛው የጎንደር እስክስታ አይነት ማንጠርጠር ሲሆን ይሄ ውዝዋዜ ተወዛዋዧ በአንድ እጇ የአንደኛውን መቀነት ጫፍ በመያዝ የተወሰነ ከፍታ ከፍ በማድረግ፣ በሌላኛው እጇ የሌላኛውን መቀነቷን ጫፍ በመያዝ ዝቅ በማድረግ ልክ ሰፌድ ይዛ እህል እንደምታጣራ ሴት ትወዛወዛለች።
በሃገራችን በእርሻ ፣ በቤት ስራ ፣ በሰርግ ፣ በድግስ ወንፈል በመግባት መረዳዳት የተለመደ ነው። ሴቶችም በልዩ ልዩ ሞያ ለምሳሌ በጥጥ ፈተላ ፣ በጥልፍ ፣ በወቀጣ ፣ በእንጀራ ጋገራ በመሳሰሉት ይረዳዳሉ። ይሄን መረዳዳታቸውን አንድነታቸውን ለማሳየት ወገብ ለወገብ ተያይዘው የሚወዛወዙት እስክስታም ተጠቃሽ ነው።
መንጠቅ
ከሴቶች በተጨማሪ ወንዶች የሚጨፍሯቸው የውዝዋዜ አይነቶም አሉ። ከእነዚህ አንዱ መንጠቅ ይባላል። ይህ ውዝዋዜ ከፈረስ ግልቢያ ጋር የተያያዘ እንቅስቃሴ ያለው የውዝዋዜ ዐይነት ሲሆን ውዝዋዜውም የሚቀርበው በጦር ሜዳ ጊዜ ግንባር ቀደም ጦር አብሳሪው በሆነው የፈረስ ግልቢያ ዓይነት እንቅስቃሴ ነው።
በዚህ የውዝዋዜ አይነት ሊተላለፍ የተፈለው መልዕክት ጥሩ ፈረስ ጋላቢና የጠላትን ጦር በፈረስ ሸምጥ ግልቢያ ሰብረው በመግባት ጠላትን ደምስሶና ትጥቅ ነጥቀው መውጣት የሚችሉ ልበ ሙሉዎችና ደፋሮች መሆናቸውን ማሳያ ነው።
በእስክስታ ጊዜ ሊታዩ ከሚችሉት ነገሮች ውስጥ ቀረርቶ ሽለላና ፉከራ በዋነኝነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ ቀረርቶ በአንድ ጉልበታቸው በርከክ በማለት ጠቋሚ ጣታቸውን ጆሯቸው ላይ አድርገው አንገታቸውን በቁጭት መልክ እየነቀነቁ የሚያሳዩት ትዕይንት ነው። ይህም ሃገር ተወረረ ደንበር ተደፈረ በተባለ ጊዜ በንዴት እያቅራሩ “ያልሰማህ ተነስ ስማ” በሚል አይነት ለጦርነቱ ሌሎችን የማንቃት ምሳሌ ነው። ስለዚህ ጣታቸውን ጆሯቸው ላይ ማድረጋቸው "ስማ ተነስ" የሚል ትርጉም አለው።