ሰኔ 23 ፣ 2014

የአማራ ከልል ወሳኝ ኩነት ምዝግባ በሰሜኑ ጦርነት ከ252 ሺህ በላይ የክብር መዝገቦች እንደወደሙበት ገለጸ

City: Bahir Darዜናወቅታዊ ጉዳዮች

የጠፉት መረጃዎች ወደ ዲጂታል አሰራር የተቀየሩ ባለመሆናቸው መልሶ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል ተብሏል

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

የአማራ ከልል ወሳኝ ኩነት ምዝግባ በሰሜኑ ጦርነት ከ252 ሺህ በላይ የክብር መዝገቦች እንደወደሙበት ገለጸ
Camera Icon

Credit: Social Media

በሰሜኑ ጦርነት ቀጣና ውስጥ በነበሩ ተቋማት 251 ሺህ 905 የክብር መዝገቦች እንደወደሙ የአማራ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት አሳውቋል።  

የወደሙት የክብር መዝገቦች የደንበኞች የማይተኩ መረጃዎች ከመሆናቸው በተጨማሪ በአገልግሎት ጽ/ቤቶች ውስጥ የነበሩ ግምታቸው ከ36 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁሶች አብረው መጥፋታቸውና መዘረፋቸውን የአገልግሎቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ማስተዋል አለባቸው ገልጸዋል። 

ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ለፖሊስ ግብዓት እና ለመሰረተ ልማት ግንባታ ፍትሃዊ ክፍፍል ወሳኝ ሚና የነበራቸው እነዚህ መዝገቦች የጠፉት በአማራ ክልል ጦርነቱ በተካሄደባቸው ስምንት ዞኖች እና 67 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የወሳኝ ኩነት መመዝገቢያ ጣቢያዎች ላይ መሆኑ ታውቋል። 

የጠፉት መረጃዎች ወደ ዲጂታል አሰራር የተቀየሩ ባለመሆናቸው መልሶ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል የተባለ ሲሆን የቁሳቁስ ውድመቱን ግን እንደገና ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ተገልጿል።

በጦርነቱ ማግስት የከተማው ወሳኝ ኩነት ፅ/ቤት መረጃዎችና ቁሳቁሶች የወደሙ በመሆኑ የልደት ካርድ ለማውጣት መቸገራቸውን የነገሩን የደሴ ከተማ ነዋሪው አቶ ቢራራ ፍቃዱ ናቸው። በዚህም ምክንያት ብዙ ጉዳዮች መፈጸም በነበረባቸው ጊዜ ሳይፈፅሙ መቅረታቸውን አጋርተውናል። 

ወ/ሮ ፋጡማ መሀመድ ሌላዋ የደሴ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በጦርነቱ የቀበሌ ፅ/ቤት የወሳኝ ኩነት መረጃዎችና ቁሳቁሶች በመውደማቸው የተለመደውን አገልግሎት ለማግኘት ረዘም ላለ ጊዜ መጉላላታቸው ተናግረዋል።

የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሯ እንደሚሉት በተዘረፉት መረጃዎች ክፍተት ተጠቅመው በማጭበርበርና በተሳሳተ ማንነት ወደ አማራ ክልል ሰርገው የሚገቡ አጥፊዎችም እየተያዙ ነው። ይህም የመረጃዎቹ መጥፋትና መውደም ያስከተለው ሌላው ችግር ነው ተብሏል። 

የአማራ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት የወደሙ ቢሮዎችን መልሶ በመገንባትና ወደ ሥራ በማስገባት፣ በወረራው ተቋርጦ ወደቆየው መደበኛ ሥራ ለመመለስ ባለፉት ስምንት ወራት በርካታ ስራዎች እንዳከናወነ ተገልጿል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እና አሰራሩን ለማዘመንም ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር የትብብር ውሎችን ፈጽሟል።በዚህም በ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የመረጃ አያያዙን ወደ ዲጂታል አሰራር ለመለወጥ እየተሰራ እንደሆነ ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ማስተዋል ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት በሕግ ከተቋቋመበት 2008 ዓ.ም ጀምሮ የማህበረሰብ ግንዛቤ እየተሻሻለ መምጣቱን የተናገሩት ዳይሬክተሯ በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም ቀበሌዎች በወሳኝ ኩነት ምዝገባዎች በኔትወርክ ለማስተሳሰር እቅድ እንዳለ ጠቁመዋል። ለዚህ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ትስስርም 70 ሚሊዮን ብር የሚስፈልግ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራበት በአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጥያቄ ቀርቧል። 

በወሳኝ ኩነት መረጃዎችና ቁሳቁሶች መውደምና መዘረፍ ምክንያት በአለፉት ስምንት ወራት 487 ሺህ 430 ኩነቶችን ለመመዝገብ ያቀደው አገልግሎቱ 29 በመቶ (144,826) በመቶ ኩነቶችን ብቻ መመዝገብ መቻሉን ከመስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል። 

ሁሉም አይነት ኩነቶች ተመዝግበውና የመረጃ ምንጭ ሆነው ማየትን ራዕይ ያደረገው ተቋሙ የልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ፣ ፍቺና የጉዲፈቻ ዋና ዋና ኩነቶችን የመመዝገብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ነገር ግን ህዝቡ ለዘርፉ ያለው የግንዛቤ እጥረት ፣ የአጋር ተቋማት ድጋፍ እንደተፈለገው አለመሆን፣ የቴክኖሎጂ አለመሟላት እና የሰው ኃይል እጥረት የተቋሙ ችግሮች መሆናቸው ተዘርዝሯል። 

ወይዘሮ ማስተዋል በሀገር ደረጃ ለኩነቶች ምዝገባ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው በአማራ ክልል ያለው አፈጻጸም በሀገር ደረጃ ካለው ጋር ተቀራራቢ ለማድረግ ማኅበረሰቡ ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መረጃዎች አንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሊያዘገይ የሚችል በቂ ምክንያት ከሌለ በስተቀር ከልደት ውጪ ያሉት ኩነቶች ማለትም ሞት፣ጋብቻ፣ፍቺና ጉዲፈቻ ከተፈፀሙበት ቀን ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ መመዝግብ አለባቸው። ልደት ደግሞ በ90 ቀናት ወስጥ መመዝግብ አንዳለበት በአዋጅ ቁጥር 760/2004 ተደንግጓል።

በአዋጁ መሰረት የወሳኝ ኩነት መረጃዎች የሚመዘገቡበት መዝገብ “የክብር መዝገብ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን አዘጋጃጀቱም በቋሚነት ለማገልገል በሚያስችል፣ ለአያያዝ በሚያመች በጥራዝ መልክ ነው። ለእያንዳንዱ የወሳኝ ኩነት ዓይነት የተለየ  የክብር መዝገብ እንደሚኖረው ተደንግጓል። የእነዚህ የክብር መዝገቦች መጥፋትና መውደም በጦርነት ቀጣናው ውስጥ በነበሩት የምስራቅ አማራ አካባቢዎች ውስጥ የተከሰተ ነው።  

አስተያየት