ሰኔ 25 ፣ 2014

በሐዋሳ "ሎቄ" በተባለው ስፍራ የተካሄደዉ እልቂት ሲታወስ

City: Hawassaታሪክማህበራዊ ጉዳዮች

የመንግስት ታጣቂ ኃይል ፊሽካ በመንፋት በሰልፈኞቹ ላይ ተኩስ ከፈተ፤ በተከፈተው ተኩስ ማምለጥ ያልቻሉት በቦታው ህይወታቸው ሲያልፍ የቀሩት ደግሞ የአካል ጉዳት ደረሰባቸው

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በሐዋሳ "ሎቄ" በተባለው ስፍራ የተካሄደዉ እልቂት ሲታወስ
Camera Icon

ፎቶ፡ ሳሙኤል በላይነህ (የሲዳማ ሽማግሌዎችና ወጣቶች ግንቦት 16, 2011 ዓ.ም ከ17 ዓመት በኋላ ለሃውልት የመታሰቢያ ድንጋይ ሲያኖሩ)

የሲዳማ ብሔር እራሱን በመቻል የኢትዮጵያ አስረኛው ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ጥያቄ የተጀመረው የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ነበር። በ1994 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ፣  በተለምዶ "ሎቄ" ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ ይህንን ጥያቄ ይዘው አደባባይ ከወጡ የብሔሩ ተወላጆች ውስጥ ከ 60 በላይ የሚሆኑት በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች መገደላቸው በሲዳማ ማህበረሰብ ዘንድ የማይረሳ ትውስታ ነው። 

በሲዳማ ገጠራማ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋለው የዘመናዊ ህክምና አገልግሎት እጥረት ፣ ወጣቱ ተምሮ ስራ ማጣቱና ሌሎችም የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በክልል መዋቅር ውስጥ ከሆነ ምላሽ ይገኝበታል በሚል ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ሲቀርቡ ቆይተዋል። 

ከመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተጨማሪ በወቅቱ የሲዳማ ዞን እና የደቡብ ክልል ማዕከል የነበረችውን ሐዋሳ ከተማ ለክልሉ ሙሉ በሙሉ በመተው የዞኑ ዋና ከተማ ወደ ይርጋለም እንዲዛወር በአመራሮቹ የተጀመረው እንቅስቃሴ (ዉሳኔዉን በሚመለከት በመንግስት ይፋዊ የሆነ መግለጫ በወቅቱ ባይሰጥበትም) በህዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት እያሰፋው መጥቶ ነበር። 

በዚህ ወቅት ነበር የብሔሩ ተወላጆች ይህን ቅሬታቸውን ለመንግሥት ለማሰማት በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የተዘጋጁት። ይህን ሰልፍና መዘዙን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) "በሐዋሳና በአካባቢዉ በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ የደረሰ አስከፊ የመብት ረገጣ" በሚል ርእስ በ51ኛ ልዩ ዕትሙ ዘግቦታል። 

ኢሰመጉ ያወጣዉ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በወቅቱ ሰላማዊ ሰልፉ መቼ እንደሚደረግ ፣ ቀኑ እና ሰዓቱ እንዲሁም ቦታዉን በመወሰን አዘጋጆቹ ለሚመለከተዉ የመንግስት አካል በደብዳቤ አሳውቀው ነበር።  

ሰላማዊ ሰልፉ መነሻዉን ከሐዋሳ ከተማ በስተደቡብ ከሚገኘዉና ሎቄ ተብሎ ከሚጠራዉ አካባቢ አድርጎ መዳረሻዉን ደግሞ በሐዋሳ ከተማ መስቀል አደባባይ እንዲሆን መታቀዱን የኢሰመጉ ሪፖርት ያመለክታል።  

እለቱ አርብ ግንቦት 16፣ 1994 ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የመጡ ከ7 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች የእንሰት ተክል ዝንጣፊ እና እፍኝ ሳር፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓለማ በመያዝ በሎቄ አደባባይ ተሰብስበዋል። ሰልፈኞቹ “ሲዳማ ክልል የመሆን ህገመንግስታዊ መብቱ ይጠበቅለት፣ የኢሕአዴግን ዓላማ አንቃወምም ፣ ሐዋሳ የሲዳማ ዞን ዋና ከተማ እንዳትሆን ለምን ተፈለገ?” የሚሉ መፈክሮችን ይዘዉ ድምፃቸውን ማሰማት ጀመሩ ይላሉ በወቅቱ ሰልፉ ላይ የተፈጠረውን የሚያስታውሱ ሰዎች።

የሰልፈኞችን መምጣት ይጠባበቅ የነበረው የመንግስት ታጣቂ ኃይል ወዲያዉ ፊሽካ በመንፋት በሰልፈኞቹ ላይ ተኩስ ከፈተ። ሰልፉ ከሎቄ አደባባይ ብዙም ሳይንቀሳቀስ በተከፈተው ተኩስ ማምለጥ ያልቻሉት በቦታው ህይወታቸው ሲያልፍ የቀሩት ደግሞ የአካል ጉዳት ደረሰባቸው። ከሞትና ጉዳት የተረፉት ደግሞ ለእስር ተዳረጉ። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አገኘሁት ባለዉ መረጃ የዚያን እለት በሎቄ በተካሄደው ጭፍጨፋ 25 የብሔሩ ተወላጆች ሲሞቱ 26 የሚሆኑት ደግሞ በጥይት ሰዉነታቸዉ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል፤ 36 የሚሆኑትም ለእስር ተዳርገዋል በማለት አስፍሯል።

የኢሰመጉ ሪፖርት የሟቾቹን ቁጥር አሳንሷል በማለት የሚሟገቱት በሐዋሳ የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ የቋንቋ መምህር የሆኑት አቶ ሳሙኤል በላይነህ በጉዳዩ ላይ የዳሰሳ ጥናት እንደሰሩ ይናገራሉ። "በወቅቱ ህይወታቸዉን ያጡ ከ60 በላይ የሚሆኑ አርሶአደሮች፣ ተማሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ የፀጥታ አባላትና የመንግስት ሰራተኞች ነበሩበት። ከ40 የሚልቁት ደግሞ የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉ ናቸው" በማለት ያብራራሉ።  

ከአዲስ ዘይቤ ጋር በሎቄ ስለተካሄደዉ ግድያ በሚመለከት ቃለምምልስ ያደረጉት አቶ ሳሙኤል "ከህግ አግባብ ዉጪ በሆነ መልኩ ከታጠቁ የመንግስት ኃይሎች በተከፈተ ተኩስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን አስክሬናቸውን እንኳን በግዜ መቅበር እንዳይቻል መደረጉ እስካሁን ድረስ በህብረተሰቡ ዉስጥ ጥቁር ጠባሳ ማሳደሩን ታዝቤያለሁ" ብለዋል። ሆኖም እንደ መምህሩ ገለፃ በሰላማዊ መንገድ ህገመንግስታዊ መብታቸዉን ለመጠየቅ በወጡ የብሔሩ ተወላጆች ላይ የተደረገዉ ጭፍጨፋ ሲዳማ ክልል እንዲሆን መሰረት ሊጥል ችሏል። 

ይህ ታሪክ ተዳፍኖ መቅረት እንደሌለበትና ህይወታቸዉን በወቅቱ ላጡት ሰዎች ቤተሰቦች ተገቢዉ ካሳ መሰጠት እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ፀሐይ አብርሃም ናቸው። ወይዘሮ ፀሐይ በሰልፉ ላይ ተሳታፊ የነበሩትን ባለቤታቸውንና ተማሪ ልጃቸውን በሞት አጥተዋል። “ይህ እስካሁን ድረስ ህመም እንደሆነብኝ አለሁ። በወቅቱ አልቅሼ እርሜን ማውጣት እንዳልችል መደረጌ ጠባሳው እስካሁን በልቤ ውስጥ አለ” በማለት በሀዘን ስሜት ነግረዉናል። 

በሲዳማ ክልል ወጣቶች እና አባቶች በሎቄ የተፈፀመዉ ሁነት እንዲታወስ እና ሐውልት እንዲሰራ በማሰብ በ 2011 ዓ.ም የመሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል ። 

የሎቄ ሰልፈኞች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ለማሰብ ከተሰሩ ስራዎች አንዱ በቅርቡ በደራሲ ተመስገን ተሰማ ተፅፎ ለአንባቢያን የበቃው ረጅም ታሪካዊ ልብወለድ ነው። ከዚህ ቀደም "ኤልዙላ" የሚል ረጅም ልብወለድ እና  እና "ጤት" የተባለ የግጥም መድብል ያሳተመው ደራሲ ተመስገን ተሰማ “ሎቄ” በሚል ርዕስ የታተመው ተራኪ ልብወለድ ሶስተኛ መፅሐፉ መሆኑን ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። 

"ሎቄን በደም ሳይሆን በቀለም አሰብናት " የሚል መሪ ቃል የያዘዉና በእዉነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተዉ መፅሐፉን ለመፃፍ ያነሳሳዉን ምክንያት ደራሲው ተመስገን ተሰማ ሲናገር "በልጅነት እድሜዬ የተመለከትኩት ሁነት ነው። በተጨማሪም በዕለቱ በሰልፉ ላይ የተሳተፉ እንዲሁም ስለተፈጠረዉ ሁኔታ በጥልቀት የሚያዉቁ ትልልቅ ሰዎችን በመጠየቅ እዉነታዉን በመፅሐፉ አስፍሬአለሁ" ብሏል። 

ድርጊቱ ለታሪክ እንዲቀመጥና በሎቄ የተሰዉት ሰዎችም ተረስተው እንዳይቀሩ ይህን መጽሃፍ እንደጻፈ ተመስገን አጫውቶናል። 296 ገጾች ያሉት ይህ መፅሐፍ እሁድ ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ የሲዳማ ባህል አዳራሽ ተመርቋል ። በመፅሐፍ ምረቃዉ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሐይማኖት አባቶች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ሌሎች ተሳታፊዎች የታደሙ ሲሆን የሎቄን ታሪክ የሚያሳይ የተለያዩ የቲያትር ስራዎች በእለቱ መቅረባቸዉን ለማወቅ ችለናል።

አስተያየት