ሐምሌ 5 ፣ 2014

አወዛጋቢው የኮንዶሚኒየም እጣ አወጣጥ እና የመንግስት ምላሽ

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች

የእጣ ማውጫው ሲስተም ማንም እንደፈለገ ገብቶ ማስተካከልንም ሆነ ሌላ ሰው መጨመርና መቀነስን ብሎም ለውጥ ማድረግን የሚከለክል እንደሆነ ተነግሮ ነበር

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

አወዛጋቢው የኮንዶሚኒየም እጣ አወጣጥ እና የመንግስት ምላሽ
Camera Icon

ፎቶ፡ አዲስ ቢዝ

ሐምሌ 01 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በግንባታ ላይ ከነበሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል 25,491 ያህሉን በ14ኛው ዙር የ20/80 እና በ3ኛው ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ለባለ እድለኞች ለመስጠት የዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት መካሄዱ ይታወቃል።

ሆኖም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህ የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ የዳታ ማጭበርበር ድርጊት እንዳጋጠመው ገልጾ ሁኔታውን እያጣራ እንደሚገኝና በድርጊቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑን አስታውቋል። ይህን ተከትሎ የቤት እጣ ይደርሰን ይሆን ብለው ሲጠባበቁ በነበሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ውዝግብ እና ቅሬታ እንዲነሳ ሆኗል።

የከተማ አስተዳደሩ የኮንዶሚኒየሙን ዕጣ አወጣበታለሁ ብሎ የነበረው የቴክኖሎጂ ሲስተም ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በሚፈጥር መልኩ መዘጋጀቱ ተገልጾ ነበር። ይህ ቴክኖሎጂ ወደ ትግበራ ከመምጣቱ በፊት የመረጃ መያዣና እጣ ማውጫውን ከማበልጸግ ሂደት ጀምሮ ብዙ ሙከራዎች የተካሄደበት መሆኑም ተነግሮ ነበር። 

ይሁን እንጂ የከተማ አስተዳደሩ “ፍትሃዊነትን ተደራሽ ለማድረግ ይህ ሁሉ ሂደት ታልፎ ሳለ ከዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት በኋላ የተለያዩ ጥቆማዎች በመቅረባቸው የኦዲት ሥራ ስንጀምር በባንክ የተላከውና ለእጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር የተጫነው ዳታ ልዩነቶች ተገኝተዋል” በማለት፣ በተደረገው የማጣራት ስራ ገንዘብ ላልቆጠቡ ሰዎች እጣ መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ የተዓማኒነት ጉድለቶችን አይቻለሁ ሲል ገለፀ። ይህን ተከትሎም “የቤት ማስተላለፉን ሂደት ግልፅነት ለማስፈን ሲባል እና ውጤቱን የሚያዛባ ተግባር ሲያጋጥም መልሰን ኦዲት እንዲደረግ በገባነው ቃል መሰረት የተፈጠረውን ችግር ከጉዳዩ ገለልተኛ በሆኑ በሚመለከታቸው ተቋማት የማጣራት ስራ በመከናወን ላይ እንገኛለን” ብሎ በሰአታት ልዩነት ውስጥ ጥፋቱ ላይ ተገኝተዋል ያላቸውን ሁለት የስራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስተዳደሩ ይፋ አደረገ።

ነገር ግን ይህ የከተማ አስተዳደሩ ምላሽ ለኮንዶሚኒየም ቤት ገንዘብ በባንክ ሲቆጥቡ የቆዩ ነዋሪዎችን ቁጣ ሊያረግብ አልቻለም። አዲስ ዘይቤም አንዳንድ ቅሬታ አቅራቢዎችን ተዘዋውራ በማነጋገር አስተያየታቸውን ሰብስባለች።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወጣት “ሰዉ ለኮንዶሚኒየም ብር የሚቆጥበው የቤተሰቡን እና የግሉን ፍላጎት ወደ ጎን ብሎ እንዲሁም ከልጆቹ ጉሮሮ ነጥቆ ነው። ሰዉ በየጊዜው ቢጭበረበርም ከዛሬ ነገ ይሻላል ብሎ ጠብቆ ዛሬም ተስፋ የሚያጨልም የማጭበርበር ሙከራ እየተደረገ ነው” ይላል።

የከተማ አስተዳደሩ የቤት እጣ አወጣጡ ላይ ተአማኒነት ስለጎደለ የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው በማለት ያቀረበው ማስተባበያ አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸውን ነዋሪዎች አላሰመነም። ይህን አስመልክቶ አስተያየት ሰጪው ወጣት “የቆጣቢዎችን መረጃ የሚልከው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንግስት የሚዘውረው ንግድ ባንክ ሆኖ፣ እጣውን የሚያወጣው ደግሞ የአስተዳደር ቢሮው ሆኖ ሳለ እንዴት አይጭበረበርም ብለን ልናምን እንችላለን?” ሲል ይናገራል።

ወ/ሪት ማህሌት ፈቃደ የተባለች አስተያየት ሰጪያችን ደግሞ “በመጀመሪያ የእጣ አወጣጡ ከእጅ ንክኪ ነጻ ነው ተብሎ ነበር። ነጻ መሆኑ ይህ ችግር እንዳይፈጠር ካላደረገ ምን ዋጋ አለው?” ስትል ትችቷን ሰንዝራለች። አክላም “መጀመሪያም ለኮንዶሚኒየም እጣ እጩ የሆኑት ሰዎች ስማቸው ይፋ ሊደረግ ይገባ ነበር፣ የትኞቹ ከየትኞቹ በእጣ ተለይተው እንደደረሳቸው ማወቅ እስካልተቻለ ድረስ ግልጽነት የሚባል ነገር አለ ብዬ አላምንም” በማለት አስረድታለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተማ አስተዳደሩ መረጃዎቹን በኦዲት አጣርቶ ሳይጨርስ እና በይፋ የእድለኞችን ዝርዝር ከማስታወቁ ቀደም ባሉ ቀናት፣ የ40/60 ባለሁለት እና ባለሶስት መኝታ አሸናፊዎች ዝርዝር እንዲሁም 100% የከፈሉ የ40/60 ቅሬታ አቅራቢ ከሳሶች ስም ዝርዝር የቴሌግራም ገጽ ላይ ተለቅቆ እንደነበር አቶ ጥላሁን ግርማ የተባሉ ምንጫችን ጠቁመውናል። አቶ ጥላሁን ከዚህ ጋር በተያያዘ ያላቸውን አስተያየት ሲያጋሩም “የተወሰነ ሙስና ካለ ሙሉ ሂደቱን ያዛባዋል፣ ከአሁን በኋላ ውጤቱ ተቀባይነት እንዲኖረው ቀን ተቆርጦ ለእጣው ብቁ የሆኑ ቆጣቢዎች ስም ዝርዝር ለህዝቡ ይፋ መደረግ አለበት” ይላሉ። አያይዘውም እጣው ከመውጣቱ በፊት ወደ ኮምፒውተር ቋት የሚገባው ዝርዝር በገለልተኛ መርማሪ ሊረጋገጥ እንደሚገባ ይመክራሉ።

እንከን ተገኝቶበታል የተባለውን ዕጣ ያወጣው ቴክኖሎጂ ለአራት ዙር ሙከራ ተደርጎበት፣ አምስተኛውና የመጨረሻ ዙር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና የቁጠባ አስፈፃሚ ተቋም ተወካዮች በተገኙበት ሙከራው ተካሄዶ እንደነበር ተገልጿል። የተዘረጋው የጋራ መኖርያ ቤቶች የእጣ አወጣጥና የመረጃ የቴክኖሎጂ ስርዓት ልዩ የሚያደርገው ዋና ዋና ጉዳዮች ተብለው ያሉት ብቃቶችና ተመራጭ የሚያደርጉት ሁኔታዎች ተዘርዝረዋል። ከነዚህም እንደ ከዚህ ቀደሙ ለተለያየ ህገወጥ ድርጊት እንዳይጋለጥ ለማድረግ ከሰው ንክኪ ነፃ ሆኖ የተሰራ መተግበርያ በመሆኑ አስተማማኝና ግልፅነት እንዲሁም ፍትሃዊ አሰራር የዘረጋ መሆኑ፣ መተግበርያው በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መበልጸጉ እና ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የፌደራል  ጨምሮ ይሁኝታን ያገኘና በግል  ተቋማት ታዛቢዎች ጭምር ታይቶ የተረጋገጠ መሆኑ፣ ሲስተሙ የቅድሚያ ተጠቃሚነት አወሳሰንን በፍትሃዊነት የሚተገብር መሆኑ ተጠቅሰዋል። በተጨማሪም ልዩ ትኩረት የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመለየት በእጣው ላይ በፍትሃዊነት አካቶ ሊያወጣ በሚችል መንገድ የተሰራ መሆኑም ተነግሯል።

ከዚህም ባለፈ ሲስተሙ ማንም እንደፈለገ ገብቶ ማስተካከልንም ሆነ ሌላ ሰው መጨመርና መቀነስን ብሎም ለውጥ ማድረግን የሚከለክል እንደሆነም ተብራርቷል። ሂደቱን በመቆጣጠር ረገድ ደግሞ ስርዓቱን ራሱ ከህገወጥ ድርጊቶች የሚጠብቅ መሆኑን በመጥቀስ አንዴ እጣው ከወጣ በኋላ ለሌላ ንክኪ እንዳይጋለጥ ራሱን ዝግ የሚያደርግ ሲስተም መሆኑንም አስተዳደሩ አስታውቋል።

የከተማ አስተዳደሩ እንዳስታወቀው ከዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓቱ በኋላ የተለያዩ ጥቆማዎች በመቅረባቸው በተደረገው የኦዲት ሥራ በባንክ የተላከውና ለእጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር የተጫነው ዳታ ልዩነት ተገኝቶበታል። እንዲሁም ላልቆጠቡ ሰዎች እጣ መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ የተዓማኒነት ጉድለቶች ታይተዋል። 

ይህን በተመለከተ የአዲስ ዘይቤ የዝግጅት ክፍል “በዚህ ልክ ጥንቃቄ ተደርጎበታል የተባለው የእጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት እንዴት በባንክ የተላከውና ለእጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር የተጫነው ዳታ ላይ ልዩነቶች እስከማግኘት የደረሰ የመጭበርበር ችግር ሊጋረጥበት ቻለ?” ስንል ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ቢሮ ጥያቄ አቀረብን።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሀላፊ አቶ ሽመልስ ታምራት፣ ይህን ስህተት እንዲፈጠር አመቻችተዋል የተባሉት ግለሰቦች በምርመራ ላይ በመሆናቸው፣ እንዴት እና ለምን የሚለው ጥያቄ ከምርመራው በኋላ ይፋ ይሆናል ብለዋል። እንደ ኮርፖሬሽኑ ማብራሪያ ችግሩ ለምን እንደተፈጠረ እያደረገ በሚገኘው ምርመራ ለተፈጠረው ስህተት መፍትሔ ለማግኘት ተቃርቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዕጣ ያቀረባቸው ቤቶች የሚገኙባቸውን ሳይቶች ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ያቀፋቸው ቤቶች በአያት 2፤ በቦሌ በሻሌ እና በቡልቡላ ሎት 2 ይገኛሉ።

የ20/80 ቤት ልማት ፕሮግራም ያቀፋቸው ቤቶች ደግሞ በበረከት፣ በቦሌ አራብሳ (ሳይት 3፤5፤6)፣  በወታደር፣ በየካ ጣፎ፣ በጀሞ ጋራ፣ በጎሮ ስላሴ፣ በፉሪ ሃና እና በፋኑኤል ይገኛሉ።

ባለ ሶስት መኝታ ኮንዶሚኒየሞችን በተመለከተ የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት እንደነገሩን፣ በዚህ ዙር የ20/80 ነባር ባለ ሶስት መኝታ በ12ኛው ዙር ዕጣ ዝቅተኛ የቁጠባ መጠን ተወስዶ ለማጠናቀቅ የተቻለ በመሆኑ፣ ነባር ባለ 3 መኝታ ቁጠባ ላይ ብቁ ሆነው የተገኙ ነዋሪዎች በቦርድ ውሳኔ የተቀመጠውን ላለመጣስ በዚህ ዕጣ የማይካተቱ ሲሆን በቀጣይ በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱ ይሆናል። 

በዚህ የእጣ አወጣጥ ሂደትም በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም የ1997 ተመዝጋቢዎች ብቻ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል።

አስተያየት