ሐምሌ 4 ፣ 2014

የደሴ ከተማ ኢንቨስትመንት ተግዳሮቶች

City: Dessieኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች

ባለሃብቶች የሚገጥሟቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና መሬት ካገኙ በኋላም ቶሎ ወደስራ አለመግባታቸው ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ማነቆ ሆኗል

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የደሴ ከተማ ኢንቨስትመንት ተግዳሮቶች
Camera Icon

Credit: Social Media

ደሴ ከተማ እንደ ቀደምትነቷና እንዳሏት የኢንቨስትመንት አማራጮች በከተማዋ ላይ መዋእለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚመጡት የባለሃብቶች ቁጥር አናሳ መሆን የከተማዋን እድገት ያን ያህል ፈጣን እንዳይሆን አድርጎታል። በዚህም ምክንያት የከተማዋ አምራችና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ቁጥር ውሱን ሲሆን የስራ እድል ፈጠራ አማራጮች ላይም ጫና አሳድሯል።

ሃብታቸውን አውጥተው ወደስራ ለመግባት የሚፈልጉ ባለሃብቶች ጉዳያቸውን በሚፈጽሙላቸው የተለያዩ ቢሮዎች ላይ በሚገጥማቸው ውጣ ውረድና የመልካም አስተዳደር ችግር ቅሬታ ሲያሰሙ ማየትና መስማት የተለመደ ጉዳይ ነው።

ኡመር ሃሰን ባለሃብትና “እነ ኡመር” የተሰኘ የቤተሰብ ንግድ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ነው። በወተት ማቀነባበሪያ ስራ ዘረፍ ለመሰማራት ከከተማ አስተዳደሩ 8 ሺህ ካ.ሜ ቦታ የተፈቀደለት በ2012 ዓ.ም. ነበር። ነገር ግን እስካሁን ወደ ግንባታ መግባት አልቻለም። ምክንያቱንም ሲያስረዳ ፤

"ሁሉን ቅድመ ሁኔታዎች አጠናቅቀን ወደ ግንባታ ለመግባት በዝግጅት ላይ ብንሆንም የከተማ አስተዳደሩ የፈቀደልን ቦታ እስካሁን አልተሰጠንም። ኢንቨስትመንት መስሪያ ቤቱ እንዲያስረክበን ጥያቄ ካቀረብን አንድ አመት ከመንፈቅ ሆኖናል እስካሁን መልስ የለም" ብሏል። 

በተመሳሳይ ሁኔታ በደሴ ከተማ ለኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ቦታ የጠየቁት አቶ መንገሻ ክፍሌም አራት አመት ሙሉ ምላሽ ሳያገኙ እስካሁን ቆይተዋል። "በመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት ባለ 4 ኮከብ ሆቴል ለመገንባት ተጨማሪ የማስፋፊያ ቦታ እንዲሰጠኝ ብጠይቅም ሳይሳካልኝ፣ ካለኝ የካፒታል አቅም በታች የሆነ ስራ ውስጥ ለመቆየት ተገድጃለሁ" ብለዋል። 

አቶ መንገሻ በተጨማሪ እንደገለጹት አብዛኛውን ጊዜ ደሴ መሃል ከተማ ላይ በኢንቨስትመንት የሚሰጡ ቦታዎች ከሶስተኛ ወገን ያልፀዱና ጥያቄ ስለሚኖርባቸው ለሆቴል ተብለው የሚሰሩ ህንጻዎች ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ የአልጋ ኪራይ ብቻ የሚሰሩ ናቸው። 

የሶስተኛ ወገን ጥያቄዎች ደሴ ላይ ለሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ማነቆ ናቸው ማለት ይቻላል። በከተማው ውስጥ ለኢንቨስትመንት የሚሰጡና ማስፋፊያ የሚጠየቅባቸው አብዛኞቹ ቦታዎች ለረዥም አመታት ሌሎች ግለሰቦች የኖሩባቸው ወይም የተገለገሉባቸው የቀበሌ (የመንግስት) ቤቶችና ይዞታዎች ሲሆኑ ነዋሪዎቹን ከቦታው ላይ አስለቅቆና ተመጣጣኝ የሆነ ተተኪ ቦታ አዘጋጅቶ ለመስጠት የሚወስደው ረዥም ጊዜ ነው። ሶስተኛ ወገን የሚባሉትም እነዚሁ ለኢንቨስትመንት ሲባል ከቦታቸው የሚነሱት አካላት (ነዋሪዎች) ናቸው። ቦታው ለባለሃብት ሊሰጥ ነው ሲባል እኛም መስራት እንችላለን የሚሉ ጥያቄዎች ከነዋሪዎች ስለሚነሱ እስከ ፍርድ ቤት የሚደርስ ክርክር ውስጥ መግባት ይኖራል። ይህም ለባለሃብቱ በእቅዱ መሰረት እንዳይሰራ እንቅፋት ይሆንበታል።    

በሌላ በኩል ለፋብሪካ የሚሰጡ ቦታዎች አብዛኞቹ የገበሬ የእርሻ መሬቶች ስለሆኑ፣ ለገበሬው የሚሰጠው የካሳ ክፍያ አናሳ መሆን መሬቱን ከቅሬታ ነጻ አድርጎ ወደ ባለሃብቱ በቀላሉ እንዳይተላለፍ ተግዳሮት ይሆናል።  

የሆቴል ንግድ ዘርፍ ለተጠቃሚው መስጠት የሚገባው አገልግሎት ዘርፈ ብዙ እንደመሆኑ በሆቴል ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የሚሰጡትን አገልግሎት ባማከለ ሁኔታ በቂ የመስሪያ ቦታ ሊዘጋጅላቸው ይገባል ይላሉ ባለሃብቱ አቶ መንገሻ።

በባለፉት 11 ዓመታት በደሴ ከተማ 33.97 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ከ 500 በላይ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ቢያወጡም ከእነዚህ መካከል 134ቱ በተለያየ ምክንያት የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው ተሰርዟል። በግንባታ ላይ የሚገኙት 67 ሲሆኑ፤ ቦታ አጥረው ቁፋሮ የጀመሩ 308 ኢንቨስተሮች አሉ። መሬት አጥረው ምንም እንቅስቃሴ ያልጀመሩ 8 ባለሃብቶች በያዙት መሬት ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ከከተማ አስተዳደሩ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ባለሃብቶች መሬት በስማቸው ወስደው አጥረው በመያዝ ምንም ስራ ሳይጀምሩበት መሬቱን ለጎርፍ ተጋላጭ በማድረግ ፣ እንዲሸረሸርና የመንሸራተት አደጋ እንዲደርስበት ካደረጉት ለአደጋ ተጋልጧል ማለት ነው። ይህም ባለሃብቶቹን ያስጠይቃቸዋል። በወቅቱ ወደስራ እንዲገቡ የሚበረታቱትም መሬቱ ለተጠቀሱት አደጋዎች እንዳይጋለጥ ነው። 

ግንባታ ያልጀመሩ ባለሃብቶች በበኩላቸው እስካሁን ድረስ በምን ምክንያት ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ ሲገልጹ የፕሮጀክት መተግበሪያ ቦታዎቻቸው ከከተማ አስተዳደሩ ቢፈቀድላቸውም አብዛኞቹ ቦታዎች የገበሬ መሬት በመሆናቸው እና ለተነሺ ገበሬዎችም ተገቢ የሆነ ካሳ ባለመከፈሉ ስራቸው መጓተቱን ገልጸዋል። “ሁኔታዎችን እስከምናስተካክል ድረስ ታገሱ እየተባልን ከ1 ዓመት በላይ ልንቆይ ችለናል" ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከገበሬዎች ጋር ያለውን ጉዳይ መጨረስ ሳይችል ቀርቶ ባላስረከበን ቦታ ላይ "መሬት ላይ ጉዳት ያደረሱ" ብሎ እኛን መፈረጁ አሳዝኖናል ሲሉ ቅሬታቸውን አክለው ገልጸዋል።

በጥቃቅንና አነስተኛ አደረጃጀት ውስጥ ገብተው በተለያየ ጊዜ እድገት በማምጣት ወደ ከፍተኛ  በመሸጋገር በመኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በኢንቨስትመንት መሬት  ከተሰጣቸው ውስጥ 11 ባለሃብቶች ግንባታ ጀምረው ያቋረጡ ሲሆን 9 ባለሀብቶች ደግሞ ግንባታቸውን አጠናቀው ማሽን መትከል ያልቻሉ እንዳሉ መለየት ተችሏል። ቦታ ወስደው ምንም አይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያልጀመሩና አሳማኝ ምክንያት ያላቀረቡ ባለሃብቶች ላይ ግን ርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት ማጠናቀቁን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

መሬት ያለስራ ታጥሮ ለረዥም አመታት ከተቀመጠ ስራና ሰራተኛን ሊያገናኙ ይችሉ የነበሩ እድሎችን ያስተጓጉላል፤ ስለዚህ መሬቱ ተነጥቆ ለሌላ መስራት ለሚችል ባለሃብት መተላለፍ አለበት ይላሉ አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች። ብዙ የመስራት ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶች መሬት ከግለሰብ በውድ ዋጋ በመግዛት ለብዙዎች የስራ እድል መፍጠር በሚችል ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ስላሉ እነርሱን ማበረታታት ይገባል ተብሏል። 

አቶ አለባቸው ሰይድ የደሴ ከተማ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው በመንግስት አሰራር ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እና የሚነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን በአጭር ጊዜ ለመመለስ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

ሃላፊው እንደሚሉት ከመካከለኛ ዘርፍ ወደ ኢንቨስትመት ለተሸጋገሩ ባለሃብቶች ተገቢውን ማጣራት ተደርጎ የመሬት ጥያቄያቸውን ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በተጨማሪም “በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የመሬት ጥያቄ ያቀረቡትንም በአዲሱ የመንግስት መመሪያ መሰረት ከመሬታቸው ለሚነሱት ካሳ እየከፈሉ እንዲወስዱ እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል።

የሆቴል ግንባታ፣ የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄ ፣ ከአዋሳኝ መሬቶች ጋር ተይይዞ ችግር ያጋጠማቸው እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የተነሳባቸውን ጉዳዮች ኢንቨስትመንት ኮሜቴው ገምግሞ መፍትሄ እየተሰጠ ይገኛል ያሉት አቶ አለባቸው ሰይድ ናቸው። ከመሬት ጋር ተያይዞ ለተነሱት ቅሬታዎች የከተማው መሬት አስተዳደር ጽ/ቤትና ከተማ ልማት ጽ/ቤት መፍትሄ እንዲሰጡ ትዕዛዝ መተላለፉንም ለማወቅ ችለናል። 

የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው አሳማኝ ባልሆነ ችግር ምክንያት መሬት አጥረው የተቀመጡ ባለሃብቶች ግንባታቸውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መጀመር ካልቻሉ መሬታቸው ተቀምቶ ለሌላ መስራት ለሚችል ባለሃብት እንደሚተላለፍ ገልጸዋል። 

ከንቲባው እንደሚሉት መሬቱ የ3ተኛ ወገን ጥያቄ ሳይኖርበት ያለምክንያት አጥረው የተቀመጡ ባለሃብቶች በፍጥነት ወደ ስራ መግባት ካልቻሉ ቦታውን ይነጠቃሉ። ግንባታ ጀምረው ያቋረጡትን ባለሃብቶች በተመለከተ "እንደ ግንባታው ሁኔታና ባህሪ  በባለሙያ ጥናት  ከተደረገበት በኋላ በሚቀርበው ሪፖርት መሰረት እገዛ የሚያስፈልጋቸው ካሉ ድጋፍ ተደርጎላቸው ግንባታቸውን እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል" ብለዋል።

ግንባታ አጠናቅቀው ማሽን ያልተከሉትና በነበረው ጦርነት ምክንያት ችግር ያጋጠማቸውን ባለሃብቶች በተመለከተ "እንደችግራቸውና በጦርነቱ እንደደረሰባቸው የጉዳት መጠን ብድር በፍጥነት እንዲያገኙና ማሽኖችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ አስፈላጊውን እገዛ እናደርጋለን" ብለዋል።

አስተያየት