ሐምሌ 3 ፣ 2014

ፔዦ አውቶሞቢልና ድሬዳዋ

City: Dire Dawaየአኗኗር ዘይቤ

ፔዦ 404 ሞዴል የጊዜንና የቴክኖሎጂን ለውጥ ተቋቁማ በድሬዳዋ እስካሁን ብትቆይም በተለያዩ የአለም ሃገራት አገልግሎት አቁማ እንደ ተፈላጊ ቅርስ ለጨረታ ትቀርባለች

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ፔዦ አውቶሞቢልና ድሬዳዋ
Camera Icon

ፎቶ፡ ዱንካን ሙር

ፔዦ መኪና ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ከታየባቸው ከተሞች መካከል ድሬዳዋ አንዷ ነች። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በፈረንሳዮች አማካኝነት ወደ ድሬዳዋ የገባችው ፔዦ ሙቀት የመቋቋም ብቃቷ ለከተማዋ ተመራጭ ተሽከርካሪ አድርጓታል። በፈረንሳይና የኢትዮጵያ መንግስታት ጥምረት በተዘረጋው የኢትዮ- ጅቡቲ ምድር ባቡር ግንባታ የፈረንሳይ ዜጎች ሰፊ ተሳትፎ አድርገዋል። የዚህ ምድር ባቡር አገልግሎትም ድሬዳዋ ዋነኛዋ ማዕከል ነበረች። በወቅቱ በድሬዳዋ ይኖሩ የነበሩት ፈረንሳዮች በድሬዳዋ ትተው ካለፏቸው አሻራዎች የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር፣ ፈረንሳይ ሆስፒታል፣ አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴ የመሳሰሉት ተጠቃሾቹ ናቸው።

በዚህ ረገድ የፈረንሳይዋ ፔዦ አውቶሞቢል እስካሁንም በከተማዋ ጥቅም ላይ እየዋለች የምትገኝ አይነተኛ ምሳሌ ናት። በወቅቱ የፈረንሳይ ምርቶች በቀላሉ ድሬዳዋ መግባት ችለዋል። ከአንደኛው የአለም ጦርነት ጀምሮ ፈረንሳይ መኪናዎችን በማምረት ረገድ ቀዳሚ ሀገር ነበረች። ፔዦ መጀመሪያ ያመርት የነበረው ብስክሌት ሲሆን ከዚያም ቀስ በቀስ መኪና ማምረት ጀመረ። 

ፔዦ ካመረታቸውና እስካሁንም በድሬዳዋ ከሚታዩት እድሜ ጠገብ ተሽከርካሪዎች በብዛት የሚገኙት ፔዦ 404 የተባሉት ሞዴሎች ናቸው። ፔዦ 404 ሰፊ የቤተሰብ አውቶሞቢል ስትሆን እ.አ.አ ከ1960-1975 ባለው ጊዜ የተመረተች ሞዴል ናት። በአለም ላይ በአብዛኛው ለታክሲ አገልግሎት የዋለችው ይህች ሞዴል፣ ረጅም ጊዜ መቆየት በመቻሏና በጥንካሬዋ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘች ምርት ናት። ፔዦ 404 ከአውቶሞቢል ጀምሮ እስከ አነስተኛ ጭነት መኪና ድረስ በተለያዩ ቅርፆች ስትቀርብ ቆይታለች። የሞዴሏ ምርት እስከቆመበት እ.አ.አ 1975 ድረስም በጠቅላላው 2,885,374 ፔዦ 404 መኪናዎች ተመርተው በአለም ዙሪያ ተሰራጭተዋል። ይህች የፔጆ ሞዴል በድሬዳዋ ደግሞ አስከ አሁን ድረስ ለመነዳት በቅታለች። 

በድሬዳዋ ከመኪኖቹ በተጨማሪ ፔዦ ብስክሌቶችም ይገኛሉ። በወቅቱ የምድር ባቡር ሰራተኞች በጊዜ ወደስራ እንዲገቡ በማሰብ ድርጅቱ የፔዦ ብስክሌቶችን ለሰራተኞቹ በየወሩ ከደሞዝ በሚቆረጥ ብድር መልክ አቅርቦላቸው ነበር። እስካሁንም ከምድር ባቡር ጡረታ ከወጡ ረጅም አመት ያስቆጠሩ ሰዎች በፔዦ ብስክሌት በከተማው ሲንቀሳቀሱ ይታያል።

የፔዦ መኪኖች በድሬዳዋ ከተማ ሰፊ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ከድሬዳዋ ሀረር መንገደኞችን ያጓጉዙ ነበር። ፋሚሊ ፔዦ የሚባሉትና ሰባት ሰዎች መጫን የሚችሉት መኪኖችን ከድሬዳዋ እንደ ሐረር፣ ቁልቢ፣ ቀርሳ እና ጋራሙለታ ወዳሉት ለድሬዳዋ ቅርብ የሆኑ ከተሞች ለመሄድ በተለይ ነጋዴው ማህበረሰብ ይጠቀምባቸው እንደነበር ይነገራል። በጊዜ ሂደትም ሚኒባስ የሚባል አዲስ የመኪና አይነት ሲመጣ ቀስ በቀስ ፋሚሊ ፔዦ መኪኖች ከገበያ ወጡ።

በድሬዳዋ በአሁኑ ወቅት የታክሲ ፔዦ መኪኖች ከገበያ ውጪ ቢሆኑም መንገደኞችን ከአየር ማረፊያ እየተቀበሉ ወደሚፈልጉበት ያደርሳሉ። ከተመረቱ ከ50-60 አመት ያለፋቸው ፔዦ መኪኖች አሁንም አገልግሎት ሲሰጡና ጥንካሬያቸውን ያየ ገና ብዙ አመት እንደሚያገለግሉ መገመት አያዳግተውም። ፔዦ መኪኖች ያሏቸው ግለሰቦች “ኤርፖርት ታክሲ ማህበር’’ በሚል ስያሜ ከ 16 አመት በፊት ማህበር አቋቁመው እየሰሩ ይገኛሉ። በማህበሩ ውስጥም 50 አባላት ይገኛሉ። 

በኤርፖርት ታክሲ ማህበር አስተባባሪ የሆኑት አቶ ግዮን አበጀ አሁን የያዟትን ፔዦ መኪና ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ነበር ከሰው ላይ የገዟት። “ስገዛት ራሱ አንድ 20 አመት አገልግላ ነበር” በማለት አቶ ግዮን ይናገራሉ። በአሽከርካሪነት 30 አመታትን ሲያገለግሉ አደጋ የሚባል ባለማድረሳቸው ሽልማት ማግኘት የቻሉት አቶ ግዮን ስለመኪናቸው አውርተው አይጠግቡም። ሆኖም እያሽከረከሯት የምትገኘው ፔዦ መኪና መለዋወጫዋ ገበያ ላይ እንደተፈለገው አይገኝም። ምክንያቱም ፋብሪካው ይህን የፔዦ ሞዴል ማምረት አቁሟል። የተበላሸ የመኪናዋን እቃ መቀየር ግድ ከሆነባቸው አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ አሮጌ የመኪና መለዋወጫ የሚሸጥበት ቦታ ያውም ከከባድ ልፋት በኋላ እንደሚያገኙ ያስረዳሉ።

“መኪናዬ ልክ እንደ ዘመን አመጣሾቹ ፎርስና ባጃጅ ብትሆን ኖሮማ አልቆልኝ ነበር፤ ነገር ግን ፔዦ ይሄ ሁሉ ዘመን አገልግላም የመበላሸት ሁኔታ እንኳን የሚያጋጥማት አልፎ አልፎ ነው” ይላሉ አቶ ግዮን። ሌላው የማህበሩ አባል ከ30 አመት በላይ የፔዦ መኪናን እያሽከረከሩ የሚገኙት አቶ ቃኘው ወርቁ ናቸው። አቶ ወርቁ በድሬዳዋ የታክሲ ሹፌር ሆነው ያገለግሉ ነበር። የታክሲ አገልግሎቱ በባጃጅና ፎርስ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች እየተተካ ሲመጣ ወደ አየር ማረፊያ ስራ ገብተዋል። መጀመሪያ አካባቢ ስራው ከብዷቸው የነበረው አቶ ወርቁ ታክሲዋን ከገዟት ጥቂት አመታቸው ስለነበር ለመሸጥ አስበውም ነበር። ቀስ በቀስ ግን አየር ማረፊያ ከገቡና ማህበር መስርተው መንቀሳቀስ ከጀመሩ በኋላ ነገሮች እየተስተካከሉ ስለመምጣታቸው ይናገራሉ። 

ሌላው በድሬዳዋ ከተማ በፎርስ ሹፌርነት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት አቶ ሀይሉ በለው የፔዦ ታክሲ ሹፌር ነበሩ። አቶ ሀይሉ አምስት ልጆች ያላቸው ሲሆን የመጀመሪያ ልጃቸው 40 አመቱ ነው። ልጆቻቸውን የፔዦ መኪና እያሽከረከሩ በሚያገኙት ገቢ እንዳሳደጉ ይናገራሉ። አቶ ሀይሉ፣ “ልክ ፔዦ ተፈላጊነቷ ሲቀንስና ከገበያ ስትወጣ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገባሁ። የልጆች አባት ስለነበርኩ ግራ ገባኝና በ10 ሺህ ብር ሸጥኳት። አሁን ላይ ግን ይቆጨኛል። ምክንያቱም የእቃው ጥንካሬ በአሁን ዘመን አንዳሉት ተሸከርካሪዎች አይደለም። ከዚያም በተጨማሪ የሸጥኩበት ገንዘብ ይቆጨኛል” በማለት ለመኪናዋ የሚሰጧትን ከፍተኛ ዋጋ ያስረዳሉ።

ድሬዳዋ ከተማ በኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ከ 30 አመት በላይ አገልግለው ጡረታ የወጡት አቶ ንጉሴ ውቃው በበኩላቸው ምድር ባቡር ድርጅት እያገለገሉ በነበሩበት ወቅት ከደሞዝ እየተቀነሰ እንዲከፍሉ እየተደረገ ፔዦ ብስክሌት ገዝተዋል። አሁን እድሜያቸው ከ70 አመት በላይ ቢሆንም የሚንቀሳቀሱት በፔዦ ብስክሌታቸው ነው። በወቅቱ ስራ እንዳይረፍድባቸው የገዟት ቢሆንም “የእድሜ ልክ ቅርስ ሆናለች” ሲሉ ይገልጿታል ብስክሌቷን።

የመጀመሪያዋ ፔዦ 404 አውቶሞቢል ከተመረተች ወደ 62 አመት ብታስቆጥርም አሁንም ድረስ ጥንካሬዋንና ሞገሷን ጠብቃ በድሬዳዋ ጎዳናዎች ትታያለች። ከተማዋን የሚጎበኙ የውጭ ዜጎች መኪናዋን አገልግሎት ላይ በሚመለከቷት ጊዜም ከፍተኛ አግራሞት ሲፈጥርባቸው ይታያል። ይህች ፔዦ 404 ሞዴል የጊዜና ቴክኖሎጂን ለውጥ ተቋቁማ በድሬዳዋ እስካሁን ብትቆይም በተለያዩ የአለም ሃገራት አገልግሎት አቁማ እንደ ውድ ቅርስ ለጨረታ ትቀርባለች። ለቤተሰብና ሽርሽር እስከ አነስተኛ ጭነት በሚሆን ቅርፅ የተመረቱ የተለያዩ የፔዦ 404 መኪኖች በአውሮፓ ከ10000 እስከ 50,000 ዩሮ (550,000- 2,600,00 ብር) ለጨረታ ቀርበው በመሸጥ ላይ ይገኛሉ። 

አስተያየት