ሰኔ 30 ፣ 2014

በውሃ እጥረት ምክንያት ለዳግም በርሃማነት አደጋ የተጋለጠው የአርጎባ ወረዳው 'ደለመኔ' ተራራ

City: Dessieኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች

በክልል ደረጃ በሞዴልነት ተሸላሚ የነበረው ይህ የተፋሰስ ልማት በውሃ እጥረት ምክንያት የለሙት የፍራፍሬ ዛፎች ጠውልገው፣ ከፊሎቹም ደርቀዋል

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በውሃ እጥረት ምክንያት ለዳግም በርሃማነት አደጋ የተጋለጠው የአርጎባ ወረዳው 'ደለመኔ' ተራራ
Camera Icon

Credit: Social Media

የደለመኔ ተራራ የወረዳው ታታሪ ወጣቶች በጀመሩት የተፋሰስ ልማት ከዚህ በፊት አካባቢው ከነበረበት በርሃማነት ወደ አረንጓዴ ስፍራነት ተቀይሮ ነበር። የአካባቢውን የአየር ንብረት ለኑሩ ምቹ ማድረግ ቢቻልም በአሁኑ ጊዜ ባጋጠመው የውሃ ችግር ምክንያት ለዳግም በርሃማነት እየተጋለጠ ይገኛል። በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተው ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የገቢ ምንጭ መፍጠር የቻሉት ወጣቶችም ምርታማነቱ በመቀነሱ ምክንያት ስራ አጥ ሆነው ለችግር ተዳርገዋል።

የአካባቢው በረሃ ንዳድ ሳይበግራቸው፣ የቦታው ዝናብ አጠር መሆን ተስፋ ሳያስቆርጣቸው ፣ ጉልበታቸው ለተራቆተው ተራራ ልማት ሳይሰንፍ አረንጓዴ ነገር ይበቅልበታል ተብሎ የማይታሰብበትን ደረቅ ስፍራ በተፋሰስ አልምተው በአማራ ክልል በተፋሰስ ልማት ሞዴል በመባል እንደምሳሌ ሲጠቀሱ ቆይተዋል የአርጎባ ልዩ ወረዳ ወጣቶች።

ወጣቶቹ በወረዳው የሚገኘውን በተለምዶ 'ደለመኔ' በመባል የሚታወቀውን ተራራ በተፋሰስ ስራ በማልማት የተራቆተውን መሬት ወደ ፍራፍሬ ልማት ቦታነት ቀይረውም ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠሪያ አድርገውታል።

አርጎባ ወረዳ በደቡብ ወሎ ዞን ምስራቃዊ አቅጣጫ የሚገኝ ሲሆን ከአፋርና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋርም ድንበርተኛ ነው። ደለመኔ ተራራ ቀድሞ ምን ይመስል እንደነበር አዲስ ዘይቤ በስራው ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶችን አነጋግራለች።  

ሀቢብ ጀማል የአርጎባ ልዩ ወረዳ ነዋሪ ሲሆን ለስራ ፍለጋ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ቢሄድም ያሰበው ሳይሳካለት ወደ ሃገሩ ተመልሷል። እንደሱ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ከገጠማቸው ወጣቶች ጋር አንድ ላይ በመሆንና በሃገራቸው ላይ ሰርተው ለመጠቀም በመወሰናቸው በማህበር ተደራጅተው ስራ መጀመራቸውን ሲያስታውስ፤

"ከሳኡዲ አረቢያ በግዳጅ ተባረን ወደ ሃገራችን ተመልሰን ስራ አጥ ሆነን ነበር። ወረዳው በማህበር አደራጅቶን ተራራውን በተፋሰስ ስራ በማልማት ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ስራ ገብተን ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ አምርተን እየሸጥን በኑሯችንም ጥሩ ለውጥ አይተን ነበር" ብሏል ሃቢብ።

"አካባቢው በርሃማ ከመሆኑ የተነሳ ተራራው በጣም የተራቆተ ነበር። ቀን ከሌት ጠንክረን በመስራታችን ወደ አረንጓዴ ስፍራነት መቀየር ችለን ነበር" የሚለው ደግሞ ወጣት ሰይድ አሰፋ ነው። ሰይድ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ በ2012 ዓ.ም. ከቤተሰቦቹ ጋር ተፈናቅሎ የመጣ ወጣት ነው። 

ሌላዋ የልማት ስራው ተሳታፊ ራቢያ በሽር ከ 10ኛ ክፍል ትምህርቷን በማቋረጥ እንደ እኩዮቿ የራሷንና ቤተሰቧን ኑሮ የተሻለ ለማድረግ በማሰብ በህገ-ወጥ ደላሎች አማካኝነት በየመን በኩል ወደ ሳኡዲ አረቢያ ተጉዛ የነበረች ወጣት ነች። የሳኡዲ ኑሮዋ ሃገር ቤት ሆና ስታስበውና ስትመኘው ከነበረው ተቃራኒ ሆኖ ከባድ የስቃይ ጊዜ አሳልፋለች። ለሁለት ዓመታት ያህል በቤት ሰራተኝነት ብትቆይም አሰሪዎቿ የሰራችበትን ገንዘብ ሳይከፍሏት ህገወጥ ናት ብለው ለፖሊስ ካስረከቧት በኋላ ለሶስት ወር ያህል በእስር ቤት አሳልፋ በ2009 ዓ.ም. ወደ ሃገሯ ተመልሳለች።   

"ወደ ሃገር ቤት ከመጣሁ በኋላ ለቤተሰቦቼ ምንም ነገር ማድረግ ባለመቻሌ ብስጭት ውስጥ ገብቼ የነበረ ቢሆንም ከተሰራ በሃገር ውስጥም ቢሆን መለወጥ እንደሚቻል በዚህ ስራ ልምድ ወስጃለሁ” ትላለች ራቢያ ደለመኔ ተራራን አልምተው ፍራፍሬ በመሸጥ የሚተዳደሩ የአካባቢዋን ወጣቶች በማየት፣ እነርሱ ማህበር ውስጥ አባል በመሆንና ወደስራ በመሰማራት ከራሷ አልፋ ቤተሰቦቿንም መርዳት እንደቻለች በመግለጽ። 

የደለመኔ ተፋሰስ ልማት ህብረት ስራ ማህበር በ2008 ዓ.ም. ስራ የጀመረ ቢሆንም በየአመቱ የአባላቶቹ ብዛት እየጨመረና በስነ ህይወታዊ ዘዴ ተራራው እየተሸፈነ ተጠቃሚ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም እየተበራከቱ መጥተው ነበር። የማህበሩ አባላት በአብዛኛው ከአረብ ሃገር ተመላሽ ወጣቶች ሲሆኑ የወረዳው ወጣቶችም ተሳታፊ ነበሩ።

ለጥናትና ምርምር የሚመረጥና በሃገር ደረጃ ሞዴል የሚሆን ተፋሰስ ለማድረግ አሁንም እየተሰራ መሆኑን የሚገልጹት የአርጎባ ልዩ ወረዳ የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አደም እንድሪስ ናቸው። 

"ቦታውን አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ለአትክልትና ፍራፍሬ መትከያ ስፍራዎች መከለያ የሚሆኑ የተለያዩ ሼዶችን በመገንባት ላይ እንገኛለን” ያሉ ሲሆን በርካታ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘሮችን በማልማት አካባቢውን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተግባር ትምህርት ማሳያ፣ ለጥናትና ምርምር ተመራጭ ቦታ እንዲሆን ጠንክረው እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል። 

በተፋሰስ ስራው ላይ የተሰማሩት ወጣቶች በስፍራው የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶችን በማከናወን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባለፈ የአካባቢው ስነ ምህዳርም እንዲሻሻል የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል። 

አቶ አደም እንደሚሉት ወጣቶቹ በረዥም ጊዜ የሚደርሱ የአትክልት ዘሮችን ተክለው እስኪያፈራና ለሽያጭ እስኪደርስ በሚወስደው የጊዜ ቆይታ ተስፋ ቆርጠው ሊበተኑ ይችሉ ነበር። ነገር ግን ይህ እንዳይሆን ጎን ለጎን የግብርና ባለሙያዎች እገዛ እያደረጉላቸው በአጭር ጊዜ ለገበያ የሚደርሱ እንደ ቲማቲም፣ ድንች፣ ጎመን፣ ቃሪያ ያሉ አትክልቶችን አምርተው ይጠቀማሉ ብለዋል። የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ለነዋሪው ህዝብ ከሚያቀርበው የቧንቧ ውሃ በመቀነስ ወደ ተራራው እንዲደርስላቸው በማድረግ የውሃ ችግር ሳይኖርባቸው እንዲሰሩ እገዛ ማድረጉንም የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።

ዛሬ ላይ ግን ይህ በክልል ደረጃ በሞዴልነት ተሸላሚ የነበረው የተፋሰስ ልማት አደጋ ተጋርጦበታል። የአትክልት ስፍራው ባጋጠመው የውሃ እጥረት ምክንያት የለሙት የፍራፍሬ ዛፎች ጠውልገው፣ ከፊሎቹም ደርቀው ለሚመለከታቸው አመታት የተለፋበት ልማት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ስጋትን ያጭራል። 

የአካባቢው ህዝብ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ፣ የቧንቧ ውሃ ተጠቃሚው እየበዛ ስለመጣ ወረዳው እንደበፊቱ ለተጨማሪ የልማት ስራዎች የሚተርፍ ውሃ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖበታል። በዚህም የተነሳ የወረዳው ውሃ ልማት ጽ/ቤት ወደ ተራራው የሚሄደውን ውሃ ሊያቋርጠው ችሏል። 

የተፋሰስ ልማት ማህበሩ አባልና ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ምርቱን እየሸጠ ተጠቃሚ የነበረው ወጣት አህመድ አልዩ ስለሁኔታው ሲገልጽ "በፊት ለልማት ይውላል ተብሎ የማይታሰበውን ቦታ እናለማዋለን ብለን ጠንክረን አሳክተነዋል፤ ነገር ግን ይህ ሊሳካ የቻለው ተደራጅተን ወደ ስራ ስንገባ በወረዳው በኩል ድጋፍ ስለተደረገልን ነው” ይላል። 

ድጋፉ በዋናነት የውሃ አቅርቦት ነበር፤ ከቦታው በርሃማነት አኳያ ከፍተኛ የውሃ ችግር ያለበት ስፍራ በመሆኑ ወረዳው ህብረተሰቡ ከሚጠቀመው ውሃ በመቀነስ ተራራው ድረስ ቧንቧ ዘርግቶ ሲያለሙበት ቆይተዋል። ተራራው ላይ ውሃ በመግባቱ ምክንያትም በርካታ ወጣቶች ወደ ተፋሰስ ስራው እንዲሳቡ ማድረግ ችሎም ነበር። ነገር ግን ይህ ዘላቂ ሊሆን አልቻለም።  

የተፋሰስ ልማቱ ውጤታማ ሆኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰፊ ሄክታር መሬትን እንደመሸፈኑ በወቅቱ የራሱ የሆነ የውሃ አማራጭ እንዲኖረው ተደርጎ ባለመሰራቱ የብዙዎች ህይወት የተቀየረበት ስራ አደጋ ላይ ወድቋል። ከዚህ በፊት ተራራውን ለማልማት ሲጠቀሙበት የነበረው የውሃ መስመር ነዋሪው ህብረተሰብ ላይ የውሃ እጥረት በመፍጠሩ ምክንያት ሊቋረጥ ችሏል፤ ይህም ወጣቶቹ ተስፋ እየቆረጡ ስራውን እንዲያቆሙ እያስገደዳቸው እንደሆነ ይገልጻሉ። 

"አልምተነው የነበረው አትክልትና ፍራፍሬ በውሃ ችግር ምክንያት በመድረቁ ልፋታችን ከንቱ ሆኖ በመቅረቱ አዝነናል" ብሏል አህመድ።   

አቶ መሃመድ ሙሳ የ01 ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊና የደለመኔ ተፋሰስ ልማትን በቅርበት የሚከታተሉ ግለሰብ ናቸው። የአካባቢውን ልማት መጠበቅ እንዲያስችል ተራራው ለብቻው የሆነ የውሃ አማራጭ ያስፈልገዋል ይላሉ። 

"በተፋሰስ ስራው ላይ የተሰማሩት ከ700 በላይ ወጣቶች 21.2 ሄክታር መሬት በማልማት በርሃማነትን መከላከል እንደሚቻል ያስመሰከሩ ናቸው” ያሉት አቶ መሃመድ በውሃ እጥረት ምክንያት ስፍራው ተመልሶ ለበርሃማነት እንዳይጋለጥ የሚመለከተው የመንግስት አካል ለተፋሰሱ ልማት ብቻ የሚያገለግል የውሃ አማራጭ ሊፈጥር ይገባዋል ብለዋል።  

የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም እንድሪስ በተፈጠረው የውሃ እጥረት ምክንያት በአትክልትና ፍራፍሬው ላይ ያንዣበበውን አደጋ በዘላቂነት ለመቅረፍ ከክልል አመራሮች ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ገልጸውልናል። 

"ወረዳችን ቆላማ እንደመሆኑ የውሃ ችግር ስላለብን ለተፋሰስ ልማቱ የሚያገለግል አንድ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድና ስድስት ሪዘርቫየር እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ውሃውን በቁጠባ በጠብታ መስኖ /Drop irrigation/ መጠቀም እንዲቻል የሚያደርግ ጥናት አስጠንተን ለክልል ልከን ስለታመነበት ለተግባራዊነቱ እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል። 

በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ያጋጠመንን የውሃ ችግር ለመቅረፍ እንሰራለን ያሉት ኃላፊው "ከዚህ በፊት የውሃ ጉድጓድ ለመቆፈር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት ሊቋረጥ ችሏል። ክልሉም በአካባቢው ላይ የነበረውን የተፋሰስ ልማት ሞዴል አድርጎ እንደመምረጡ ያጋጠመውን ችግርም ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባዋል" ሲሉ አጥብቀው አሳስበዋል። 

አስተያየት