ሰኔ 30 ፣ 2014

ሰሞነኛው የዶሮ በሽታ እና በዘርፉ ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት

City: Adamaኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች

ለአንድ ወር ከሚጠጋ ሙሉ እገዳ በኋላ ከሰሞኑ በከፊል የተለያዩ ቅድመ ጥንቃቄዎች ተቀምጠው የዶሮ እና የዶሮ ውጤቶች ወደ ገበያ መቅረብ ጀምረዋል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ሰሞነኛው የዶሮ በሽታ እና በዘርፉ ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት
Camera Icon

Credit: Social media

ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ በቢሾፍቱ እና አዲስ አበባ የዶሮ በሽታ መከሰቱን የሚገልጹ መረጃዎች ሲዘዋወሩ ቆይተዋል። የግብርና ሚኒስቴር ሰኔ 3/2014 ዓ/ም ለኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች እና አቀናባሪዎች ማህበር በጻፈው ደብዳቤ በተለያዩ ቦታዎች የዶሮ ሞት ክስተት እያጋጠመ በመሆኑ ችግሩ ተጣርቶ መፍትሔ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ የዶሮና የዶሮ ውጤቶችን (የአንድ ቀን ጫጩት እና የለማ እንቁላል) ገቢ እና ወጪ ላልተወሰነ ጊዜ ማገዱ ይታወሳል። 

ለአንድ ወር ከሚጠጋ ሙሉ እገዳ በኋላ ከሰሞኑ በከፊል የተለያዩ ቅድመ ጥንቃቄዎች ተቀምጠው የዶሮ እና የዶሮ ውጤቶች ወደ ገበያ መቅረብ ጀምረዋል። በጉዳዩ ላይ በግብርና ሚኒስቴርም ሆነ በሌላ መንግስታዊ የአስተዳደር አካል ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች እና አቀናባሪዎች ማህበር ለአባላቱ ከአርብ ሰኔ 24/2014 ዓ/ም ጀምሮ ግብርና ሚኒስቴር ባስቀመጠው መመሪያ መሠረት ምርቶቻቸውን ለገበያ ማቅረብ እንደሚችሉ የሚገልጽ ባለአምስት ነጥብ መልዕክት ለአባላቱ አስተላልፏል። ሆኖም ነጋዴዎች እና የዘርፉ ተዋንያን የመመሪያው ግልጽ አለመሆን አተገባበሩን አክብዶታል ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።

በሽታው ከተከሰተበት እና ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ በበሽታውና በወጣው እገዳ ምክንያት ዶሮ አርቢዎችም ሆኑ አጠቃላይ ዘርፉ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው ይነገራል። በበሽታው ምክንያት የዶሮ ሀብት ማጣት፣ ለሰራተኞች ያለመደበኛ ገቢ ደሞዝ መክፈል ፣ የዶሮ መኖ እና ተያያዥ የህክምና ወጪ ማውጣት የወቅቱ የዶሮ አርቢዎች ራስ ምታት ሆኗል። 

አብዛኞቹ አርቢዎች ከባንክ በተገኘ ብድር የሚሰሩ እንደመሆናቸው በእዳ ጫናና ኪሳራ እንዲሁም በተፈጠረው የገንዘብ እጥረት ምክንያት ዶሮዎችን ተገቢውን የተመጣጠነ ምግብ ባለመመገባቸው ዳግም ዶሮዎቹን ወደ ምርታማነት የመመለስ ስጋት እንደፈጠረባቸው ይገልጻሉ።  

አዲስ ዘይቤ በአዳማ፣ ቢሾፍቱ እና አዲስ አበባ በዘርፉ ላይ ከተሰማሩ ነጋዴዎች፣ ባለሞያዎች እና ማህበራት ጋር ቆይታ አድርጋለች። 

የዶሮ እና የዶሮ ምርቶች ሽያጭ እና እንቅስቃሴ እግድ በከፊል ከመነሳቱ በፊት ያነጋገርነው ዳዊት ተበጀ ዘርፉ የገጠመውን ፈተና አጋርቶን ነበር። ዳዊት በአዳማ ከተማ በአጠቃላይ የእንስሳት ተዋጽኦ አቅርቦት ስራ ላይ የተሰማራ ነጋዴ ነው። የሚሰራበት ዳና የተሰኘው የእንስሳት ተዋጽኦ አቅራቢ ድርጅት ከአዳማ በስተደቡብ 15 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ወንጂ አቅራቢያ ከሚገኘው የዶሮ ማርቢያው እንዲሁም ቢሾፍቱ ከሚገኙ የዶሮ ስጋ አቅራቢዎች የተዘጋጀ የዶሮ ስጋ አስመጥቶ ለደንበኞቹ የሚያቀርብ ነው። 

መንግስት ሰኔ 3 ያስተላለፈውን መመሪያ ተከትሎ ሙሉ ለሙሉ ስራ ማቋረጣቸው በዳናም ሆነ በሌሎች የዶሮ እርባታና ንግድ ስራዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚያዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና ማህበራዊ ጫና አሳድሯል ይላል ።

“ያለፉት ሶስት ሳምንታት ለሰራተኞቼ የምከፍለው ከኪሴ ነው። ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ ሰራተኞችን ለመበተን እንገደዳለን” ያለን ዳዊት ተበጀ በድርጅቱ በአማካኝ እስከ 2500 ብር የሚከፈላቸው 23 ሰራተኞችም እንደሚገኙ ገልጿል።  ከእግዱ በፊት በሳምንት እስከ 1500 ኪሎ ግራም የዶሮ ስጋ በድርጅታቸው በኩል ለሆቴሎች እና ሱፐርማርኬቶች ይቀርብ እንደነበር የገለጸው ዳዊት የዶሮ እርባታ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ኑሮ ላይ እገዳው ከፍተኛ ጫና አሳድሯል ይላል። ይህ ጉዳይ የቅርብ ወዳጁን ህይወት ያሳጣ ኪሳራ እንዳደረሰም ዳዊት በሃዘን አጫውቶናል። 

“ጓደኛዬ፣ ከባንክ 5 መቶ ሺህ ብር ተበድሮና ከራሱም ያለውን ብር ጨምሮ እንዲሁም ስምንት ወራት ወረፋ ጠብቆ የሶስት ወር እድሜ ያላቸው 10 ሺህ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን ይዞ ስራ ጀምሮ ነበረ። ገና በቂ ምርት መሰብሰብ ባልጀመረበት ሁኔታ ይኼ በሽታ ተከሰተ” ያለው ዳዊት የእንቁላል ሽያጭ ከታገደ በኋላ ስሙን ሊገልጽልን ያልፈለገው ጓደኛው እያንዳንዳቸውን በ230 ብር የገዛቸውን ዶሮዎች በ65 ብር ለመሸጥ መገደዱንና በዚህም ምክንያት በደረሰበት ከፍተኛ ኪሳራ ምክንያት ራሱን ማጥፋቱን ገልጾልናል። 

የዶሮ እርባታ ስራ እጅግ አድካሚ እንደሆነና የመኖ ውድነት፣ የካፒታል እጥረት እንዲሁም የተሻሻለ የጫጩት ዝርያ አግኝቶ ወደስራ ለመግባት ወራት አለፍ ሲልም አመት እንደሚያስጠብቅ የሚያብራራው ዳዊት የበሽታው መከሰት ዘርፉን የባሰ እንደሚጎዳው ይናገራል።

ውሂብ ግርማ ሌላው ያነጋገርነው በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ በዶሮ እርባታ ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ ግለሰብ ነው፡፡ ውሂብ በሞያው የእንስሳት ሀኪም ሲሆን ግብርና ሚኒስቴር የዶሮ እና የዶሮ ምርቶችን እገዳ ከጣለ በኋላ አርቢዎች ባቋቋሙት ኮሚቴ ውስጥ በቢሾፍቱ የሚገኙ ዶሮ አርቢዎችን በመወከል እየሰሩ ከሚገኙ  5 ሰዎች መሀከል አንዱ ነው፡፡

የበሽታውን ምንነት ሊገልጽ የሚችለው የግብርና ሚኒስቴር ነው የሚለው ውሂብ ግርማ በዋናነት ግን እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን እያጠቃ እንደሆነ ይናገራል። ከእንቁላል ጣዮቹ ውጪ ሌሎች እንደስጋ ዶሮ ዓይነት ዝርያዎች ላይ እንዲሁም እድሜያቸው አነስተኛ የሆኑ ዶሮዎች ላይ አለመከሰቱን ይገራል።

አቶ ብርሃኑ ሚሊዮን፣ የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች እና አቀናባሪዎች ማህበር ሊቀ መንበር ካለፈው አርብ ጀምሮ በከፊል ከተፈቀደው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ አድርገዋል። "የግብርና ሚኒስቴር ነው የበሽታውን ምንነት እያጠና ያለው፣ ሚንስቴሩ ችግሩን ተረድቶ ሪፖርት ሲያወጣ እኛም በደንብ ልንረዳው እንችላለን" የሚሉት አቶ ብርሃኑ ሚሊዮን እስከዚያ ግን አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።

“የሞቱትን ዶሮዎች በአግባቡ በመቅበር፣ በበሽታው የተነካኩ ቁሶች በማስወገድ እስካሁን የተወሰዱት የጥንቃቄ እርምጃዎች መቀጠል አለባቸው” ያሉት ሊቀመንበሩ የተጠናከረ የአሀዝ መረጃ ባይኖርም በተለያየ ጊዜ በበሽታው ምክንያት የሞቱ ዶሮዎች ሪፖርት እንደተደረጉላቸው ይናገራሉ። ነገር ግን እሳቸው እንዳሉት የግብርና ሚንስቴር በበሽታው የተመዘገበ የሰው ሞት እስካሁን እንደሌለ አረጋግጧል።       

“በሽያጭ ክልከላው ወቅት የተፈለፈሉ ጫጩቶች ወደ እርባታ እየገቡ አልነበረምና አንድ የዶሮ ማርቢያ ቦታ 7 መቶ 50 ሺህ ጫጩቶች ማስወገዱን ገልጿል” የሚሉት አቶ ብርሃኑ ከፍተኛ የሆነ ቁጥር ያለው እንቁላል በእጃቸው ላይ መኖሩንና ከውጭ የሚያስገቡትን ግን ማቆማቸውን አርቢዎቹ እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

ከበሽታው በላይ ክልከላው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል የሚሉት አቶ ብርሃኑ ለአብነትም የግብርና ሚኒስቴር የገለጸውን ቁጥር፣ ማለትም የ50 ሺህ ዶሮዎች ሞት መመዝገብን እንደአብነት አንስተው የአንድ ዶሮ ዋጋ 500 ብር ቢሆን ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንዲሁም የአንድ ጫጩት ዋጋ በአማካኝ 50 ብር ቢሆን የ 7 መቶ 50 ሺህ ጫጩት ዋጋ 40 ሚሊየን ብር በላይ ኪሳራ ያደርሳል ሲሉ በቀላል ስሌት የሚደርሰው የኢኮኖሚ  ተጽዕኖ አስረድተውናል። 

እነዚህን እና መሠል ጫናዎች ለማስቀረት ከግብርና ሚኒስተር ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው በአሁኑም ወቅት በከፊል እግዱ ተነስቶ ምርቶች ወደ ገበያ መግባት መጀመራቸውን ያበረታታሉ። 

“አዲሱ የከፊል ሽያጭ ፍቃድ የዶሮ እንቁላል እና ስጋ ወደ ገበያ እንዲቀርብ ይፈቅዳል፤ ይህም በመኖ እና ሌሎችም ተያያዥ ወጪዎች ጫና ለተጎዱ አርቢዎች አፎይታ ነው” ያሉት አቶ ብርሃኑ የአሰራር መመሪያው ላይ ስለተገለጹት ሁለት አካባቢዎቸ ሲያስረዱ መመሪያው የዶሮ እርባታ እና ስራ የሚከናወንባቸውን አካባቢዎች ከበሽታው አንጻር ነጻ ቀጠና (Free Zone ) እና የቁጥጥር ቀጠና (Controlled Zone) ሲል እንደሚለያቸው ይናገሩሉ።  

በሁለቱ መሀከል ያለውን ልዩነት የጠየቅናቸው አቶ ብርሃኑ በሽታው ከአዲስ አበባ እስከ ሞጆ ድረስ ያሉ ከተሞች ውስጥ ባሉ የዶሮ እርሻዎች ላይ መታየቱን ገልጸው በሽታው ያልታየባቸው አካባቢዎች ነጻ ቀጠና (Free Zone) ሲሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች ያለምንም ክልከላ የዶሮ ስጋ እና እንቁላል ፣ ጫጩቶችን ፣ ቄብ እንዲሁም ትልልቅ ዶሮዎችንም መሸጥ እንደሚቻል ይገልጻሉ። በተቃራኒው የቁጥጥር ቀጠና (Controlled Zone) ተብለው በተለዩ አካባቢዎች ደግሞ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲፈጸም መመሪያው ያሳስባል።

ሌላዋ ያነጋገርናት ዶ/ር ቤተልሔም ተስፋ በሞያዋ የእንስሳት ሀኪም ስትሆን በዶሮ እርባታ ዘርፍም እየሰራች ትገኛለች። ዶ/ር ቤተልሔም እንደምትለው በትክክል ነጻ እና የቁጥጥር ቀጠና ተብለው የተለዩ አካባቢዎች ባለመኖራቸው በነጻ ቀጠና ውስጥ ያሉ አርቢዎችም የቁጥጥር ቀጠናው ክልከላ ሰለባ እየሆኑ እንደሆነ ትናገራለች።

አጠቃላይ ጉዳዩ በይፋ በደንብ መታወቅ አለበት የምትለው ዶ/ር ቤተልሔም “መንግሥት ስለበሽታው ምንነት ለህዝብ ግልጽ ማደረግ አለበት ። በምን እንደሚተላለፍና በሰው ላይ የሚያመጣው አደጋ መታወቅ አለበት። እንቁላል እና ስጋ መብላት በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል ወይ የሚለው በባለሞያ ሚዲያ ላይ መገለጽ አለበት” በማለት አሳስባለች።

ዶ/ር መባገብርኤል  እስጢፋኖስ የመባ ፋርም ባለቤት ናቸው ። እሳቸውም በሞያቸው የእንስሳት ሀኪም ሲሆኑ ድርጅታቸው መባ ፋርም የዶሮ እና የመኖ ስርጭት ላይ እንደሚሰራ አጫውተውናል። 

"ከክልከላው ጋር በተያያዘ አዳዲስ ጫጩቶችን ወደ እርሻው ማስገባት አልቻልንም፤ ለሽያጭ የደረሱና ወደ ደንበኞቻችን መድረስ የነበረባቸው ዶሮዎችንም መሸጥ አልቻልንም" ይላሉ ሃኪሟ።

ለሽያጭ የደረሱ 16 ሺህ ዶሮዎች በእርሻቸው እንደሚገኙ የተናገሩ ሲሆን የግብይት መመሪያው ነጻ እና የቁጥጥር ቀጠናዎችን ቢገልጽም ግልጽ አይደለም ይላሉ የተቀመጡት የቅድመ- ምርመራ መግለጫዎች የሚተገበሩ እንዳልሆኑ በማብራራት። 

የዳና የእንስሳት ውጤቶች አቅራቢው ዳዊት ተበጀ በቅርቡ በተፈቀደው የከፊል እንቅስቀሴ ወደ ስራ እየተመለሰ እንደሆነ ገልጾ ነገር ግን ምርቶችን ከቦታ ወደ ቦታ ሲያንቀሳቅስ በተቆጣጣሪ በተለይም በደንብ አስከበሪዎች እየገጠመው ያለው ተደጋጋሚ ፍተሻ እና የጉርሻ ጥያቄ እንዳሰለቸው ነግሮናል። ይሄ መስተካከል እንዳለበትም አሳስቧል።

አሁን አርቢዎች ያጋጠማቸው ችግር ውስብስብ እንደሆነ የገለጸው ደግሞ ውሂብ ግርማ ነው። እሱ እንደሚለው አሁን ባሉበት ሁኔታ በሙሉ አቅም ወደ ስራ መመለስ አስቸጋሪ ነው። “እግዱ በከፊል የተነሳው የእንቁላል ዶሮዎች እና ብሮይለሮችን ለተባሉት ነው። እንደሳሶ ፣ ኮክለር የተባሉ እና ቄብ ላሉ ዶሮዎች ገና አልተፈቀደም" ሲል ስራቸው እየተደናቀፈ እንደሆነ ገልጿል።

ከላይ የቀረቡትን ቅሬታዎች ያውቋቸው እንደሆነና እንደማህበር የአባላትን መብት ለማስከበር ምን እየሰሩ እንደሆነ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች እና አቀናባሪዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ሚሊዮን እንደሚሉት ችግሩ ለውሳኔ ያስቸግራል። 

“በሽታው ተዛምቶ እንደሀገር ያለንን የዶሮ ሀብት ከምናጣ እንደማህበር ክልከላው መኖሩ ይጠቅማል ነው የምንለው” ያሉ ሲሆን አርቢው በሀገር የመጣውን ችግር ተባብሮና ያሉትን የፋንናንስ አማራጮች ተጠቅሞ ይህንን ጊዜ እንዲያልፍ ምክር እየሰጠን ነው ይላሉ።

"ተቆጣጣሪ አካላቱን ያሰማራው ግብርና ሚኒስቴር ነው ፤ ስለዚህ ያለው ማሻሻያ በአግባቡ እንዲሰራበት እየተነጋገርን ነው” ሲሉ ነግረውናል።

መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የላብራቶሪ ውጤቶች በቶሎ እንዲደርሱና አፋጣኝ መፍትሔዎች እንዲፈለጉ መሠራት አለበት ፣ አብዛኞቹ ዶሮ አርቢዎችም በባንክ ብድር የሚሰሩ ስለሆነ የፋይናንስ ተቋማት ብድር መመለሻ ጊዜያቸውን ማራዘም ቢችሉ በማለት አስተያየታቸውን የደመደሙት አቶ ብርሃኑ ሚዲያዎችም የተዛባ መረጃ ከማውጣት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። 

በጉዳዩ ላይ ምን እየተሰራ ነው የሚለውን ጥያቄ ይዘን ከግብርና ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባለመሳካቱ ማካተት አልቻልንም።

አስተያየት