አንድ በግ ለመግዛት ነበር አራት ሆነን ገበያ የወጣነው። ቦታው ደሞ መሃል ቦሌ መስቀል ፍላወር አደባባይ ከሚገኘው በግ ተራ። ምነው ታድያ አንድ በግ ለመግዛት አራት ሰው? የሚል ጠያቂ አይጠፋም፤ እንደውም እኛ አምስት ነበርን ከመካከላችን አንዱ የሽያጭ ሰራተኛ በመሆኑ ለስራ ተደውሎለት ሄዶ ነው። እንጂ እኛማ የአንድ ግቢ ተከራይ አባወራዎች ነን በጋራ አንድ በግ ገዝተን እንደ አውደ ዓመት ቅርጫ የምንቃመሰው።
ከገበያው ደርሰን ሙክት ስንመርጥ ቆየን። ሻጩ የበጎቹን ጥርስ እያሳየን “የሸረፈ ያልሸረፈ” በማለት እያማረጠን ጫን ያለ ዋጋ ይጠራል። እኛ ግን የያዝነው የመዋጮ ብር ከእለቱ የዋጋ ተመን ጋር አልገናኝ አለን። “አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው፣ ታላቅ ችሎታ ነው” እንዳለው ዜመኛው በአቅማችን ጠቦት ለመግዛት አጭር ስብሰባ ማድረግ ግድ ሆነብን።
በዚህ ቅፅበት ላይ ነበር አምስተኛው ጓደኛችን የተቀላቀለን “እስካሁን አልገዛችሁም ?! እኔ እኮ ሁለት መኪና ሸጬ መጣሁ” አለን በኩራት። “እንዴ! መኪና እንዲህ በቀላሉ የሚሸጥ እና የሚገዛ ሸቀጥ ሆነ ማለት ነው?” እያልኩ ዙሪያዬን ሳስተውል፤ ጎዳናው በአዳዲስ የቤት መኪኖች እንደተሞላ ልብ አልኩ። አብዛኞቹ ደግሞ “ሱዙኪ ዲዛየር” የሚል ስያሜ ያላቸው አውቶሞቢሎች ናቸው። ከዚህ አጋጣሚ በኋላ ነበር፤ ነገሩ እንዴት ነው? በማለት ወደ መኪና መሸጫዎች ጎራ ያልኩት።
“ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም በአሁን ሰዓት በአነስተኛ ዋጋ ሊገኝ የሚችል ዜሮ ዜሮ (የትም ያልተነዳ) መኪና ሱዙኪ ዲዛየር ነው” የሚሉት አቶ አበበ የኬቢ መኪና አስመጭ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ናቸው።
በመኪና ሽያጭ ስራ ላይ ለረዥም ዓመታት እንደሰሩ የሚናገሩት አቶ አበበ ቀደም ሲል የተለያዩ ዓይነት አዳዲስና ያገለገሉ መኪኖችን ከውጪ በማስገባት ለሽያጭ ያቀርቡ እንደነበር ይገልጻሉ። “ከሁለት ዓመት ወዲህ መንግሥት ያገለገሉ መኪኖች ላይ ከፍተኛ ታክስ በመጣሉ ምክንያት ዜሮ ዜሮ (አዳዲሶቹን) ብቻ ከውጭ እያስመጣን እንገኛለን። በገበያ ላይ ካለው ምርት በላይ የመኪና ፈላጊው ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። በኑሮም፣ ለስራም፣ በግል ለመንቀሳቀስም መኪና በጣም አስፈላጊ ሆኗል” ይላሉ አቶ አበበ።
ይህንኑ የሱዙኪ ዲዛየር መኪና ሲገዛ ያገኘሁት ወጣት እንደነገረኝ ከሆነ ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ስራ ባለማግኘቱ ከቤተሰብ ጋር በመነጋገር ባገኘው ገንዘብ በግል የታክሲ አገልግሎት (ራይድ) ለመስራት በመጠኑ ያገለገለ መኪና ለመግዛት ሲሞክር ስለተወደደበት አዲስ መኪና ለመግዛት ወስኗል። “አሮጌ ቪትዝ ከሰው ላይ ልገዛ ብዬ ሲወደድብኝ ትንሽ ብር ጨምሬ ዲዛየር ገዝቼ ልሰራበት ነው” በማለት ይስረዳል።
መጋቢት 2012 ዓ.ም በወጣው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ላይ በተለይ ከውጭ ለሚገቡ ያገለገሉ አውቶሞቢሎች (የቤት መኪኖች) እስከ 2 ዓመት ላገለገሉ 30 በመቶ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ ወደ 110 በመቶ ተመንድጓል። እስከ 7 ዓመት ላገለገሉ መኪኖች ደግሞ እስከ 260 በመቶ የታክስ ጭማሪ በመደረጉ አስመጪዎች ይበልጥ ፊታቸውን አዲስ መኪኖችን ወደ ማስመጣት አዞረዋል።
የሱዙኪ ዲዛየር መኪናን ተመራጭ ያደረጉትን ዋና ዋና ምክንያቶች የዘረዘሩልን የአውቶሞቲቭ ባለሙያው አቶ ሞገስ እንደሚሉት “ከዋጋቸው በተጨማሪ የሱዙኪ ዲዛየር መኪኖች ነዳጅ ቆጣቢ በመሆናቸው በሊትር እስከ 18 ኪ.ሜ መጓዝ ይችላሉ፣ ሙሉ በሙሉ አውቶማቲክ አለመሆናቸው ወይም በከፊል አውቶማቲክ መሆናቸው እና ለሀገራችን አየር ጠባይ ተሰማሚ ሆነው መመረታቸው ተመራጭ አድርጓቸዋል” ሲሉ ያስረዳሉ።
ቦሌ መስቀል ፍላወር “የአዲስ አበባ የመኪና ገበያ ማዕከል” ነው ማለት ይቻላል፤ ቄራ እና ቦሌ ብራስን መሰል ሌሎች ሰፈሮች ቢኖሩም። በተለይም ከደንበል ህንጻ በመስቀል ፍላወር እስከ ጎተራ ማሳለጫ ድረስ ባለው ሶስት ኪ.ሜ በማይሞላ መንገድ ግራና ቀኝ ላይ 23 የመኪና መሸጫዎችን ቆጥሬአለሁ። በዚሁ መስመር በሰፋፊ ግቢዎች ውስጥ ብዙ አይነት የቤት መኪኖች የገዢ እና የተመልካችን ዐይን በሚስብ መልኩ ተደርድረው ይታያሉ። ከእነዚህ ውስጥ የበዙት የሱዙኪ ዲዛየር መኪኖች ናቸው።
አቶ ሞገስ ነጋሽ የአውቶሞቲቭ ባለሙያ ሲሆኑ “ሀሌል” በተባለ የመኪና አስመጪ ድርጅት የስራ ሃላፊ ናቸዉ። “ሱዙኪ የጃፓን መኪና አምራች ድርጅት ነው። ነገር ግን የሱዙኪ ዲዛየር መኪኖች በአሁን ወቅት የሚመረቱት ማሩቲ ዲዛየር /Maruti Dzire/ በሚል ስያሜ በህንድ ነው። ከዚያም በዱባይ በኩል የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን ገበያ ተቆጣጥሮ ወደ እኛ ደርሷል። በገፍ መመረቱና በአንጻራዊነት አንስተኛ በሚባል ዋጋ መቅረቡ ተመራጭ አድርጎታል” ይላሉ።
ተዘዋውሬ ከተመለከትኳቸው የመኪና መሸጫዎች ውስጥ 1 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር እየተሸጠ ካለው ከሱዙኪ ዲዛየር እስከ 20 ሚሊዮን ብር ድረስ የሚሸጡ የተለያዩ ዓይነት የቤት መኪኖች በገበያው ላይ ይገኛሉ።
በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተወነጨፈ ካለው የኑሮ ውድነት እና የሸቀጦች የዋጋ ንረት ጣራ በደረሰበት በዚህ ወቅት የመኪና ገበያው ተሟሙቆ ይታያል። የመኪና አስመጪዎች ከመብዛታቸውም በላይ የያዙት የመሸጫ ግቢ አልበቃ ብሏቸው በደጃቸው ባለው አውራ ጎዳና ግራና ቀኝ ላይ ጥግ አስይዘው ለገዢ ያሳያሉ።
በድለላ ስራ ላይ የተሰማራ አንድ ግለሰብ እንዳጫወተኝ አንዳንድ ባለሀብቶች እንዲህ ተፈላጊ የሆኑ መኪኖችን ገዝተው በማስቀመጥ ከወራት በኋላ መልሶ በመሸጥ ከአንድ መኪና ላይ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደሚያተርፉ ይገልጻል “የገንዘብ የመግዛት አቅሙ በመዳከሙ በባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ መኪና እና መሰል ንብረቶችን ገዝቶ ማስቀመጥ ተመራጭ ሆኗል” ሲል የታዘበውን ተናግሯል።
ለመኪና አስመጪዎች እንዲህ መብዛት የቤት መኪና ፈላጊው ገበያ እየጨመረ ከመምጣቱ ባለፈ ከመንግሥት የሚሰጥ ማበረታቻ ይኖር ይሆን? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ለዚህ መልስ የሰጡን መኪና አስመጪ ድርጅቶች የስራ ሀላፊዎች እንደሚሉት ከሆነ በተቃራኒው በስራው ላይ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ተደራራቢ የቀረጥ ስርዐት መኖሩ ትልቅ ችግር እንደሆነባቸው ይገልፃሉ።
በሌላ በኩል የአስመጪነት ፍቃድ ያለው የትኛውም ድርጅት በቀላሉ ወደዚህ የስራ ዘርፍ መግባት መቻሉ፣ የመኪና ፈላጊው መብዛት እንዲሁም ባንኮችና መሰል ተቋማት ለሰራተኞቻቸው በብድር መልክ የመኪና ግዢ አማራጭ ማቅረባቸው ለመኪና ገበያው መሟሟቅ ምክንያት መሆናቸውን የሚገልጹም አሉ።
“በአዲስ አበባ ከተማ ካለው የትራንስፖርት ችግር አኳያ እኔን ጨምሮ ብዙ የስራ ባልደረቦቼ ከቤት ይልቅ ለመኪና ብድር ወስደን ገዝተናል። ቤት መግዛት በጣም ውድ ስለሆነ መኪና መግዛት ተመራጭ ነው” የሚሉት የባንክ ባለሙያው አቶ ሲሳይ አሰፋ ናቸው።
በተጨማሪም በከተማው ባለው የትራንስፖርት ችግር አገልግሎት በመስጠት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የግል ታክሲ አገልግሎት (ራይድ) ስራ ላይ ለመሰማራት ብዙዎች መኪና እንደሚገዙ ገልጸው፤ በእዚህም “የመኪና ፈላጊው ቁጥር እየጨመረ መጥቷል” ሲሉ አቶ ሲሳይ ኃሳባቸውን ገልጸዋል።
ለረዥም ጊዜ በባንክ ቤት ቆጥቦ ባገኘው ብድር ሱዙኪ ዲዛየር መኪና ገዝቶ ፒያሳ አካባቢ የራይድ አገልግሎት እየሰጠ ያገኘሁት (ስሜ እንዳይገለጽ ያለኝ) ወጣት፤ እንዳጫወተኝ “መኪናዋን ከስድስት ወር በፊት ገዝቼ እስካሁን እየሰራሁባት እዳውን እየከፈልኩ ነው። የሚገርመው እኔ ከገዛሁበት ዋጋ ላይ አሁን 300 ሺህ ብር ጨምሯል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
ከዚህ ቀደም ሱዙኪ ኩባንያ ከሞተር ሳይክል ጀምሮ እስከ ትላልቅ ተሽከርካሪዎች ድረስ በማምረት ይታወቃል። “የሱዙኪ ምርት ቀደም ሲል በ'ቪታራ' ሞዴል በደንብ ወደ ገበያው ገብቶ ነበር። አሁን ላይ SWIFT(ስዊፍት)፣ S-PRESSO(ኤስ-ፕሬሶ) የሚባሉ ዓይነቶች ቢኖሩም DZIRE(ዲዛየር) ሞዴል ግን በብዛት ተቀባይነት አግኝቷል" ሲል የሽያጭ አማካሪው አቶ ዮሐንስ ይገልፃል።
የዲዛየር መኪናን አጠቃላይ አቅም ስንመለከት ባለአራት ስሊንደር ሲሆን በዚህም 61 ኪሎ ዋት ሐይል ወይም 82 የፈረስ ጉልበት ያመነጫል። መኪናው ቤንዚን የሚጠቀምና ከፍተኛ የፍጥነት አቅሙ 170 ኪ.ሜ በሰዓት የሆነ እንዲሁም የነዳጅ ፍጆታው በአማካኝ 16.7 ኪ.ሜ በሊትር እንደሆነ የመኪናው መረጃ (ማኑዋል) ያሳያል።
ወ/ት ትግስት በአፍሮሊንክ ድርጅት ውስጥ የመኪና ሽያጭ ባለሙያ ናት። እንደትግስት ገለፃ ገዢዎች ከመኪናው ሞዴል በላይ የከለር (የቀለም) ዓይነት ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚገዙ ትናገራለች “በአብዛኛው የሚፈለጉት ሲልቨርና አይጥማ ከለር (ብርማና ግራጫ ቀለሞች) ናቸው። በዚህም ምክንያት ብቻ ከ 50 እስከ 100ሺህ ብር የዋጋ ልዩነት አላቸው” በማለት ትናገራለች።
በጎዳና ላይ ለአፍታ ብንመለከት በተለይም የቤት መኪኖቹ ቀለማቸው ተመሳሳይ ነው። ለሽያጭ የቆሙት መኪኖችም እንደዛው ብርማ (ሲልቨር) እና በተለምዶ አይጥማ የሚባለው ግራጫ (ግሬይ) ቀለም የተቀቡ ናቸው። “ይህ ለምን ሆነ?” የሚለውን ጥያቄ ለማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች እንተወውና የመኪና ሽያጭ አማካሪ የሆነትን የአቶ ዮሐንስን ኃሳብ ስናይ፤ የመኪናው የውጪ አካል (ቦዲ) አደጋ ቢደርስበት በቀላሉ ቀለሙን ለመስራት ስለሚያስችል እንደሆነ ያስረዳል።
በሀገራችን የመኪና ታሪክ ለረዥም ዘመን የቶዮታ ምርቶች ሰፊ ተቀባይነት አግኝተው እስካሁን ዘልቀዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቤት አውቶሞቢል በሆኑት ኮሮላ፣ ቪትዝ እና ያሪስ የመኪና አይነቶች ተይዞ የነበረውን ጎዳና አሁን ላይ በሱዙኪ ዲዛየር እየተሞላ ያለ ይመስላል።
አቶ ሞገስ ይህን የመኪና ገበያ ሁኔታ ሲያስረዱ “የቪትዝ መኪና ምርት ስለተቋረጠ በድጋሚ ወደ ገበያ የሚመጣ አይመስለኝም። የቶዮታ ኮሮላ አይነት እና ሌሎች መኪኖች ግን በዓለም ገበያ ካላቸው ተቀባይነት አንፃር ይቀጥላሉ። በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙትም ፈላጊ አላቸው ግን ምርቱ አነስተኛ ስለሆነ ቶሎ ያልቃል” ይላሉ።
ከጅቡቲ ወደብ በረዣዥም የጭነት ተሽከርካሪዎች ተጭነው በየቀኑ የሚገቡት የቤት መኪኖች ብዛታቸው እየጨመረ መጥቷል። በተያያዘም የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ድርጅት ከነሀሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም ከጅቡቲ ወደቦች ተሽከርካሪዎችን ጭኖ ማጓጓዝ መጀመሩን አዲስ ዘይቤ መዘገቧ ይታወሳል።
በሌላ በኩል በመኪና ሽያጭ እና በአስመጪነት ስራ ላይ ለረዥም ዓመታት ከታዘቡት እና ከአጋጠማቸው ሁኔታ በመነሳት አቶ አበበ እንደሚሉት “አሁን ከመኪና ፈላጊ መብዛት የተነሳ አንዳንዶቹ 'መኪና እናስመጣለን' እያሉ ቀብድ ተቀብለው በመጥፋት እያጭበረበሩ ነው” ሲሉ የተሟሟቀውን የመኪና ገበያ በመጠቀም ዝርፊያ እየተካሄደ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
የጃፓን ሱዙኪ ካምፓኒ እ.ኤ.አ በ1909 የተመሰረተ ቀዳሚ ተሸከርካሪ አምራች ሲሆን በዓመት 3 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎች በማምረት ለዓለም ገበያ የሚያቀርብ ተቋም ነው። ኩባንያው ከጃፓን በተጨማሪ በሃንጋሪ፣ በታይላንድ፣ በህንድ እና በማሌዥያ ማምረቻዎች አሉት። እንደ ግሎባል ሱዙኪ ድረገጽ መረጃ መሰረት የካምፓኒው ጠቅላላ ሃብት 3.3 ትሪሊዮን ዶላር ደረሷል።
ከ1970ዎቹ ወዲህ በስፋት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ገብቶ ተቀባይነት ያገኘው የጃፓኑ ቶዮታ ካምፓኒ ደግሞ በዓመት 10 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን በማምረት በዓለም ቀዳሚ ነው። እ.ኤ.አ 1937 ተመስርቶ ተሽከርካሪዎችን እያመረተ በዓለም ገበያ ተቀባይነት ያገኘው ይህ ተቋም አሁን ላይ 562 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ ሃብት እንዳለው ከቶዮታ ኢንዳስትሪ ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።