ነሐሴ 21 ፣ 2014

መተከል ትናንት፣ ዛሬና ነገ

City: Addis Ababaፖለቲካማህበራዊ ጉዳዮች

የዛሬዋ መተከል 11 የሚሆኑ ብሄሮች መኖሪያ ብትሆንም ጥቁርና ነጭ በሚመስሉ በሁለት ጎራዎች ግን የተከፈለች ናት፤ “ነባርና መጤ”

Avatar: Kassaye Dametie
ካሳዬ ዳምጤ

ካሳዬ ዳምጤ በወቅታዊ ጉዳዮችና ስርዓት ጾታ ላይ የምታተኩር በተለያዩ የብዙኃን መገናኛ አውታሮች የመስራት ልምድ ያላት የአዲስ ዘይቤ ጽሁፍ አቅራቢ ነች።

መተከል ትናንት፣ ዛሬና ነገ
Camera Icon

ፎቶ: መተከል ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ (የማንገማ እርቅ ስነ-ስርዓት)

መተከል ለመድረስ ከአዲስ አበባ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ተነስቼ ወደ አገው ምድሯ ቻግኒ አቅንቼ፤ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ገደማ ደረስኩ። ይሁን እንጂ የመናኸሪያ ሠራተኞች “ከ10 ሰዓት በኋላ መኪና አይወጣም” ስላሉ ጉዞዬን ወደ ግልገል በለስ መቀጠል አልቻልኩም። 10 ሰዓት ላይ “የካርበር ኬላ” (የአማራ፡ቤንሻንጉል ወሰን) ስለሚዘጋና ከጸጥታ ኃይሎችም ጥበቃ የማይገኝ በመሆኑ በስጋት ተሽከርካሪዎች አያልፉም።  

በማግስቱ ከ15 በላይ ሰዎች ባሳፈረች ሚኒ ባስ በ30 ብር ከጠዋቱ 12 ሰዓት ተኩል ገደማ ከቻግኒ-ግልገል ጉዞዬን ጀመርኩ። ይሁን እንጂ “ኬላ እስኪከፈት” በሚል ለአንድ ሰዓት ያክል አማራ ክልል ወሰን ላይ ለመቆየት ግድ ብሎ ነበር። የ32 ኪ.ሜ. መንገድ በብዙ ትዕይንቶች የተሞላች ናት። ኬላ በየቦታው ያለ በመሆኑ መታወቂያ ከእጅ መለየት ይከብዳል። አገር ምድሩ አረንጓዴ ነው። በጢሻና በደን የተሞላውን የመንገዱን ግራና ቀኝ በየአምስት ሰከንዱ አንገቱን እየቆለመመ የሚመለከተው መንገደኛ ብዙ ነው። ከመተከል ጥቃቶች ገሚሶቹ ጉዞና ተጓዠች ላይ መከሰታቸው መንገደኛው አይኑ እንዲያማትርና እንዲጠነቀቅ አስገድዶታል። ወሬውም ስለ እርዳታ ፣ ሠላም፣ ስጋት፣ የኑሮ ውጣ ውረድና የጸጥታ ኃይሎች ያን ሰሞን ስለወሰዱት እርምጃ ነው።

ግልገል በለስ ደረስን። ከተማዋ በእድሜ ትንሽ ናት። የአንድ ወጣት እድሜ ነው ያላት። በ1991 ዓ.ም. እንደተቆረቆረች የሚነገርላትና “ግልገል” እየተባለች በነዋሪዎቿ የምትቆላመጠው ከተማ ከዚህ ቀደም በርካታ እልቂት ማስተናገዷን በሞቅታዋ የረሳች መስላለች። የክረምቱንም አየር አሻፈረኝ ብላለች። እንደ ማንኛውም የዞን ከተማ በመብራትና ውሃ እጦት የምትሰቃይ ከተማም ናት ግልገል። በከተማዋ የተለያየ የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ ሠዎች ከነዋሪዎች (ከሚንቀሳቀሰው) የሚተናነሱ አይመስሉም። ለነዋሪዎቹ ግን ይህ እንግዳ አይደለም። አብረው ወዲያ ወዲህ ከማለታቸው ባሻገር ሲያወሩ ይታያሉ። ነዋሪዎቹና የጸጥታ ኃይሎች ተላምደዋልም ለማለት ያስደፍራል።

የመተከል ነዋሪዎች ያለፉት ሦስት ዓመታትን በስግ ተይዘው “ኑሮ ካሉት…” በሚል ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ዛሬም ብትሆን ግን ብሩህ አልሆነችም። የቀውሱ ትርምስ ሕይወትን አይቀመሴ አለፍ ሲልም መራራ አድርጎታል።

አቶ ደሳለኝ በሽር ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በመተከል ኖረዋል። በድባጤ ወረዳ አማን አምባ በምትባል ጎጥ (ሙስሊም ማሕበረሰብ የሚኖርባት) ነዋሪ ናቸው። በዚች ጎጥ በ1972 ዓ.ም. ኑሮ ከመመስረታቸው በፊት ከትውልድ ቀያቸው ጎንደር፣ ስማዳ አካባቢ በ1955 ዓ.ም. ነበር በልጅነታቸው ከአጎቶቻቸው ጋር ነበር ወደ መተከል የመጡት። በአካባቢያቸው ከህዳር ስድስት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የተነሳ ጥቃት እሳቸውና ቤተሰባቸው ባልመሩት አቅጣጫ ሕይወታቸው እንዲቀየር ሆኗል። ይህ ከሆነ ሁለት ዓመት ሊሞላ ነው። ነገር ግን አቶ ደሳለኝና ቤተሳባቸው ዛሬም ዋጋ እየከፈሉ ናቸው።

“ሁሉም ሠው ተፈናቅሎ ነበር። ለአንድ ሳምንትም፣ ለ15 ቀንም፣ ለአንድ ወርም የተፈናቀለ አለ። እስካሁንም የተፈናቀለ አለ። የሰሞኑ እርቅ እውነት ይሆን እያለ እየመጣም ነው። እዚህ አገር ብዙ እንግልት አለ። በ1983ም ፣84ም ችግር አሳልፈናል። የአሁኑ ግን በጣም ብሷል። በሁሉም አካባቢ ነው። በጣም ችግር አለ። አሁንም ሰቀቀን ነው። እንደልባችን ከብት ጥበቃ አንሄድ፤ እንደልባችን እርሻ አናርስ። ያው ጠበንጃ ያለው ሠው ተሸክሞ ይጠባበቃል። ስንበላም ዘብ እንቆማለን። እኔ ሽማግሌ ነኝ ትንሽ ልጅ አለኝ። እሱ ዛሬ ሌሊት [ሰኔ 21] ተገትሮ ነው ያደረው። ቀን ደግሞ እርሻ ዋለ። ሮንድ የቀንም አለ፤ የማታም አለ። በየሳምንቱ ሀሙስ ሀሙስ ይደርስብኛል። ይኸ ቀን ምናልባት ያልፍ ይሆን?” ብለው ጠይቀው “እንጃ እንግዲህ” ብለው ጥያቄያቸውን በጥርጣሬ ራሳቸው ይመልሳሉ።

የአቶ ደሳለኝ ታሪክ የብዙዎች ታሪክ ነው። እንደ እርሳቸው በቀውሱ ገፈት የቀመሱና ዋጋውን ዛሬም ከዓመታት በኋላ እየከፈሉ ያሉ የመተከል ነዋሪዎች ቁጥር ስፍር የላቸውም።

የመተከል ውልደትና ውድቀት

“ነባርና መጤ”

መተከል በአንድ ጀንበር ወደ “ገሀነም” አልተለወጠችም። ይልቁንም ችግሯ ዘመናትን የተሻገረና የተወሳሰበ ነው። ከወርሃ ሚያዚያ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ብሄር ተኮር ጥቃቶች አካባቢውን የግጭት ቀጠና አድርገውታል። በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ተገድለዋል፤ መቶ ሺህዎች ተፈናቅለዋል፤ ጥሪታቸው ዶግ አመድ ሆኗል።

ለመተከል ቀውስ “ታሪካዊ ምክንያቶች” ስረ-መሰረት ሆነው ይታያሉ። የዛሬዋ መተከል 11 የሚሆኑ ብሄሮች መኖሪያ ብትሆንም ጥቁርና ነጭ በሚመስሉ በሁለት ጎራዎች ግን የተከፈለች ናት፤ “ነባርና መጤ”። በተለያዩ ምክንያቶች በዋናነት ግን ግዛትን ለማስፋፋት የተደረጉ እርምጃዎች ለመተከል አሁናዊ ስዕል ከተለያየ ቦታ የመጡ ሠዎች ቀለም ሆነዋል ይላሉ የታሪክ ተመራማሪዎች።

“ነባር” የሚባሉት የጉሙዝ ማሕበረሰቦች፤ ከመካከለኛው የኢትዮጵያ ዘመን ጀምሮ የጥቃት ኢላማ መሆናቸውን ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ከፍተኛ “የባሪያ ፍንገላ” እና የወርቅ ክምችት ፍለጋ ዛሬ መተከል እያልን በምንጠራው አካባቢ መገፋፋት እንዲኖር አድርጓል። ይህም በአራቱም አቅጣጫ የጉሙዝ ማሕበረሰብ ከመኖሪያው እየተገፋ፤ እንዲያፈገፍግ አስገድዷል።

ከ18ተኛው ክ/ዘመን ጀምሮ መተከል ላይ የተደረጉ ወረራዎችና ሰፈራዎች የጉሙዝ ማሕበረሰብን በማግለልና በማፈናቀል የተደረጉ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ዳኛቸው አየነው በሠላምና ልማት ጥናት ዘርፍ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ናቸው። ኦቶ ዳኛቸው የፒኤችዲ ጥናታቸውን በመተከል የወሰን ግጭቶች ዙሪያ እየሰሩ ሲሆን፤ በአካባቢው የተካሄዱ እርምጃዎች በጉሙዝ ማሕበረሰብ አዕምሮ የማይጠፋ ትዝታ ፈጥሯል ይላሉ። በዚህም ጉሙዞች በባህላቸው “የደጋ ተወላጆችን” መግደል የክብር እና የልዩነት ምንጭ አድርገዋል። በማሕበረሰባቸው “ደገኛ የገደለ” የተለየ የአክብሮት ስፍራ የሚሰጠው ሲሆን፤ ገዳዩ “ጉንዛ” የሚል ስያሜም ይሰጠዋል።

መተከል በ20ኛው ክ/ዘመን የተለያዩ ሰፈራዎችን አስተናግዳለች። ሰፈራዎቹ በራስ-ፍላጎት ላይ የተመሰረቱና በመንግስት እርምጃ የተወሰዱ ናቸው። በዋናነት 1970ዎቹ ደርግ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ለተነሳው ድርቅና ረሀብ ምላሽ ለመስጠት በወሰደው ብሄራዊ የሰፈራ መርሃ-ግብር 82 ሺህ ዜጎች መተከል ሰፍረዋል። ይህም ጉሙዞች ወደ ቆላማ አካባቢዎች እንዲያፈገፍጉ ስለማድረጉ ይነገራል።

ተመራማሪው በአጠቃላይ የጉሙዝና የጎረቤቶቻቸውን ደገኞች ግንኙነት ያበላሸው አድሏዊ የፖለቲካ ውርስ እና መጥፎ አመለካከቶች ናቸው ሲሉ ይገልፃሉ።

በ1983 ዓ.ም. የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ስልጣን ሲጨብጥ በመተከል ቁልፍ የተባሉ ሁለት ውሳኔዎችን አሳልፏል። የግንባሩ ውሳኔ የመተከል ወሰንን እንደገና ማካለል ብቻ አልነበረም። ፌደራላዊ አወቃቀርን ሲያስተዋውቅ መተከል “ባለቤትና ሌሎች ሕዝቦች” (“ነባርና መጤ”) በሚል ለሁለት ተከፍላ ክልል ስድስት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ ተከለለች። በክልሉ ህገ-መንግስት መሰረት ለመተከል የባለቤትነት መብት ያላቸው ነባር የተባሉት ጉሙዝና ሽናሻ ብሄሮች ብቻ ናቸው። ይህም “ሌሎች ሕዝቦች” ወይም “መጤዎቹ” (አገው፣ አማራ፣ ኦሮሞ…) ከፖለቲካዊና ምጣኔ-ሀብታዊ መብቶችና ጥቅሞች እንዲገለሉ አድርጓል።

ተመራማሪው አቶ ዳኛቸው እንደሚሉት ይህ ያያኔው ገዢ ፓርቲ ውሳኔ ዛሬ “ነባርና መጤ” ለሚለው ትርክት ሕጋዊ ከለላ የሰጠ ነው። የባለቤትነትን ጉዳይ ነባር ለሚባሉ ብሄረሰቦች አጎናጽፎ፤ መጤ ለተባሉት ደግሞ ነፍጓል። “መጤዎች” ወይም ከጉምዝና ሽናሻ ብሄር ውጭ ያሉ ማሕበረሰቦች የመምረጥ እንጅ የመመረጥ መብት የላቸውም። የበይ ተመልካች መሆናቸውንም ይናገራሉ። ስልጣን ከሁለቱ ብሄሮች ውጭ የማይቀመስ ነው። ሹመት፣ ቅጥርና የስራ እድገት የትምህርት ደረጃን፣ ልምድንና አቅምን ሳይሆን ብሄርን ብቻ መሰረት ያደረገ ነው።

ሙሉቀን [ስሙ የተቀየረ] የኦሮሞ ተወላጅና የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪ ነው።  በስራ ቦታው ያለውን የብሄረሰብ አድልዎ እንዲህ ይገልጻል።

“አንቺ በስራ ልምድ 20 ዓመት ቢኖርሽ፣ ሙያተኛም ብትሆኝ ቅድሚያ ለእነሱ (ጉሙዝና ሽናሻ) ነው የሚሰጠው። አንቺ ብሄረሰብ ስላልሆንሽ አታገኝም። በመምሪያ፣ የስራ ሂደት ቡድን መሪ የሚሆነው ብሄረሰብ ነው። ኃላፊነት በክልል ደረጃ የሚሰጥ ስለሆነ ያው የመንግስትም ስትራቴጂ ስለሆነ የክልሉ ባለቤት ክልሉን ያስተዳደር በሚል ነው። በዛ አግባብ ሹመት ይሰጣል። የስራ ሂደትንም ማንም አይነካውም የብሄረሰብ ነው። ክፍቱን ወይም በውክልና ይቀመጣል እንጂ። የሚፈልጉት ሠው እስኪመጣ አይቀጠርም።” በማለት በብሄሩ ምክንያት በስልታዊ መንገድ ተጠቃሚ እንዳይሆን መደረጉን ይናገራል።

አበራ [ስሙ የተቀየረ] በዞኑ የመንግስት ሠራተኛ ሆኖ ያገለግላል። ቅድመ አያቶቹ ከክ/ዘመን በላይ በኖሩበት አካባቢ ተጠቃሚ እንዳይሆን መገለሉ አግባብ አይደለም ይላል። አበራ እንደ “ነባር ሕዝቦች” መቆጠር አለብን ብሎም ይከራከራል። ለዚህም የሚያነሳው መከራከሪያ ለዘመናት አንድ አካባቢ ስንኖር “እኛ” የተለየ ተጠቃሚ አልነበርንም የሚል ነው።

“ቅጥርና የትምህርት እድል ላይ ብትሄጂ አፈርማቲቭ አክሽን (ተጎድተዋል የተባሉ የማሕበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ በመንግስት የሚወሰድ እርምጃ) ተብሎ እስከ ሰባት ነጥብ የሚሰጣቸው አሉ። ግን እዚህ ስንኖር እኩል ነው የኖርነው። መንገድ ሳይኖር እኩል ተቸግረን፤ ህክምና ሲያጡ አብረሽ ነን። ስለዚህ ከእነሱ መነጠል አልነበረብንም፤ እኩል ኖረናልና።” ይላል።

በመተከል በፖለቲካው መገለል ብቻም ሳይሆን እንደ መሬት ያሉ ሀብቶችን ለማግኘት ችግር እንደሆነ የሚያነሱት ተመራማሪው አቶ ዳኛቸው፤ በአጠቃላይ በሁለቱም ወገኖች ኩርፊያ አለ ይላሉ። ፖለቲካን የያዙት “ነባሮቹ” ተገፍተው ወደ ቆላማ አካባቢዎች መኖራቸውና ከዚህም ጋር ተያይዞ እንደ ትምህርት ያሉ ማሕበራዊ መሰረተ ልማቶችን በማጣታቸው በምጣኔ-ሀብት አቅም ደካማ መሆናቸውንም ያነሳሉ። ይህም በሁለቱ ወገኖች መካከል ውጥረትን ፈጥሯል።

ልዩነቶች እየሰፉ ሄደው፤ ፍላጎቶችም በርትተው ዛሬ ላይ “የባለቤትነት ነጠቃ” እዚህም እዚያም እንዲነሳ አድርጓል። “መተከል የኛ ነው” የሚሉ ኃይሎች ተበራክተው በአካባቢው ውጥረት እንዲነግስና ቀድሞውኑም ተገፍተናል ላሉ ታጣቂዎች ደግሞ እንደ ማበረታቻ መሳሪያ መደረጉን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ይናገራል።

በ2010 ዓ.ም. የመጣው አዲሱ አስተዳደር ያላስደሰታቸውና ያኮረፉ (ከሕወሓት ጋር ጥብቅ ግንኘነት ያላቸው) የጉሙዝ ፖለቲከኞች የታሪክ ትርክትን በመጠቀም “መጤ” ወይም “ቀዮ” (ሽናሻን ጨምሮ) የሚባለው ማሕበረሰብ ላይ ስለማነጣጠራቸው በብዙሃኑ ይነሳል። ከዚህም ባሻገርም ውስጣዊና ውጫዊ እጆች ታክለው መተከል የእልቂት ምድር እንድትሆን አድርጓልም የሚሉት ጥቂቶች አይደሉም።

መተከል ከ2011 ዓ.ም. ወዲህ ስትታመስ ታዲያ ምን እርምጃ ተወሰደ? ለሠላም ምን ያህል ድረስ ተጓዘች የሚለውም የአያሌዎች ጥያቄ ነው።

አባጣ ጎርባጣው የሠላም መንገድ

ተኸድሶና የታደሰው ተኸድሶ

ለመተከል አላባራ ላለ ቀውስ መፍትሄ ፍለጋ በጠረጴዛ ዙሪያ አያሌዎች ተቀምጠዋል። ከጠቅላይ ሚስትሩ እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሠላም ሚኒስትር እስከ ክልሉ ርዕሰ መስተዳደር፤ ከፖሊስ እስከ መከላከያ ድረስ መተከል ተመላልሰው፤ መክረው ዘክረዋል። ነዋሪዎችን መሳሪያ ከማስታጠቅ ጀምሮ ከታጣቂዎች ጋር ስልጣን እስከመጋራት፤ ከተሃድሶ ስልጠና እስከ ትራክተር እደላ፤ ከወታደራዊ ዘመቻ እስከ እርቀ-ሠላም፤ መተከል ምን ያላየችው አለ? ጥያቄው ግን እርምጃዎቹ ምን ያህል ፍቱን ሆኑ የሚለው ነው።

ከሦስት ጊዜ በላይ የተቋቋመውና አሁን የመተከል የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት በሚል እንደገና የተደራጀው ኃይል “እጅ የሠጡ” የጉሙዝ ታጣቂችን ተሃድሶ ማስገባት ቁልፍ ሆኖ ያገኘው ባለፈው ዓመት ነበር። ኮማንድ ፖስቱ በ2013 ዓ.ም. በሁለት ዙር ለ2300 ታጣቂዎች ስልጠናውን ሰጥቷል። ነገር ግን ውጤቱ እንደ ጉም የተነነ ነበር።

የመተከል ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በተሃድሶ ስልጠናው ታጣቂዎች የፖለቲካና የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን ያስታውሳሉ።

“ስልጣን የምትፈልጉ ከሆነ ስልጣን እንሰጣችኋለን። ትጥቅ ግን መፍታት አለባችሁ። ግድያ ማቆም አለባችሁ። ተኩስ መቆም አለበት። ወደ ልማት መመለስ አለብን በሚል በዚህ ዞን አራት ወንበር፤ በየወረዳው ደግሞ አራት አራት በአጠቃላይ 25 ወንበር ሰጠናቸው። ይህንን አልተጠቀሙም። ቤት ሰርተው እንዲኖሩ የከተማ መሬትም ሰጥተናቸዋል” ሲሉ የመንግስታቸውን ጥረት ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ታጣቂዎቹ ተመልሰው ጫካ ገቡ። የመንግስት ጥረት ለምን መና ሆነ? ለምን አልተሳካም? ለሚለው ጥያቄ ታጣቂዎች መንጠባጠባቸውን አስተዳዳሪው እንደምክንያት ያነሳሉ። “ሁሉም ወረዳ ታጣቂዎቹ አልገቡም” ይላሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች ግን እስከ ትጥቁ የገባ ታጣቂ እንዴት ወደ ሠላም ይመለሳል ሲሉ የመንግስትን እርምጃ ይተቻሉ።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሠላምና ደህንነት ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ ታጣቂዎቹን በወቅቱ ትጥቅ መንጠቅ ባለመቻሉ እስከ መሳሪያቸው ወደ ስልጠናው እንዲገቡ መደረጉን ይናገራሉ።

“መሳሪያቸውን ቀስ ተብሎ ማራገፍ ይቻላል በሚል እሳቤ ነበር የተተወው። ወደ ዘላቂ ልማት እንዲገቡ መንግስት በገባው ቃል መሰረት ምቹ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነበር። በእነርሱ በኩል ዋነኛውና ትልቁ ግዴታ አንደኛ ከዚህ በኋላ ወደ ግጭት አለመግባት ነው። ሁለተኛ ደግሞ የታጠቁትን መሳሪያ መፍታት ነው። ነገር ግን በእነሱ በኩል ያለውን ግዴታ ሊፈጽሙ አልቻሉም። እንዲፈጽሙ ጥያቄ በሚቀርብበት ወቅት ተመልሰው ወደ ጫካ ገቡ።” ይላሉ።

የዞኑ ኮማንድ ፖስት ወታደራዊ ዘመቻ ማድረግን እንደ “ሁለተኛ አማራጭ” ይመለከታል። አሁናዊ ትኩረቱም በተልዕኮ እጅ የማይሰጡ ታጣቂዎችን በእነሱ አጠራር “መደምሰስ” ፤ እጅ በመስጠት ሠላማዊ ኑሮ የመረጡ ታጣቂዎችን ደግሞ ወደ ታደሰው ተሃድሶ ማስገባት ነው። ቆፍጠን ያሉ ሁለት አማራጨች ብቻ አሉ።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ አዲሱን ተሃድሶ “ተስፋ ሰጪ” ሲሉት አቶ አብዮት አልቦሮ ደግሞ “ውጤታማ” ይሉታል። ለዚህም ማሳያ ብለው የሚጠቅሱት ሠላማዊ ኑሮ ጀምረዋል ላሏቸው ታጣቂዎች ትራክተር በመስጠት ወደ እርሻ እንዲገቡ ማድረግ እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ ማደራጀት የመሳሰሉትን ነው።

የሠላምና ልማት ባለሞያው አቶ ዳኛቸው አየነው መንግስት ከቀውሱ አንገብጋቢነት አንጻር እርምጃ ለመውሰድ መዳዳት አሳይቷል ይላሉ።

“ይህ ሁሉ ግፍ መድረስ አልነበረበትም እኮ። [ጉዳቱ] በሁለቱም ወገኖች ነው። በዚያ ወገን ስትሄጅ በጣም የሚዘገንን ታሪክ አለ። በዚህም ስትሄጅ ብዙ ነገር ተበላሽቷል። ግን አሁንም አልረፈደም። አሁንም ከተሰራ ብዙ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።” ሲሉ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።

አቶ መልካሙ ጃራ ሕዝባዊ መሰረቱን በመተከል የጣለው የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ም/ሊቀ-መንበር ናቸው። ተሃድሶውን ፓርቲያቸው አስቀድሞ ሲወተውተው የነበረ እርምጃ እንደሆነ ጠቅሰው፤ እንቅስቃሴውን በመልካም ያነሳሉ። ታጣቂዎች ለበደሉት በደል ይቅርታ ጠይቀው ወደ ማሕበረሰቡ መመለሳቸው ለነገ የጋራ አብሮ መኖር ድልድይ እንደሚሆንም እምነታቸውን ይገልጻሉ። ነገር ግን የሠላምን ጥሪ በቅንነት ተቀብለው እጅ የሰጡ ታጣቂዎች እንዳሉ ሁሉ፤ “ሌላ ፍላጎት ያላቸው እንዳሉም በክትትል ማወቅ ችለናል” ይላሉ።

“ግልጽ የሆነ አቋም የያዙ [ታጣቂዎች] አሉ። አቋማቸው ግልጽ ያልሆነ ደግሞ አሉ። ያለ ትጥቅ የገቡ፤ ትጥቃቸውን የሰወሩ እንዳሉ አውቀናል። በዚህም ምክንያት አመኔታ ሙሉ ለሙሉ እንዳንጥል ያደርገናል። ነገር ግን ማሕበረሰቡ ተደራጅቶ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል የሚል እምነት አለን። የእኛም አስተዋጽኦ እዚህ ውስጥ የሰፋ ነው። ይህን በአይነ ቁራኛ እየተከታተልን ነው” ብለዋል።

ይህ እርምጃ መከራ ለበዛባቸው የመተከል ምንዱባን ግርታን የፈጠረም ነው። የመጀመሪያው ተኸድሶ ያለ ስኬት ማብቃቱ ተጠራጣሪ አድርጓቸዋል።

ዝናቡ [ስሙ የተቀየረ] የመተከል ነዋሪና በመንግስት ስራ ላይ የተሰማራ ወጣት ነው። በአካባቢው የተሰነዘረ ጥቃት በእሱና በቤተሰቡ እንዲሁም በማሕበረሱ ላይ ያሳረፈው ጫና ከባድ እንደሆነ ይናገራል። ባለፈው ዓመት ለስራ በተሰማራበት ወረዳ ጥቃት ሲነሳ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ቤት ውስጥ ተደብቀው ለቀናት መቆየት ግድ ብሏቸው እንደነበር ያስታውሳል። ወደ ቤተሰቦቹ አካባቢ ለመጓዝ የ20 ብር ትራንስፖርትን በ300 ብር ወረፋ ጠብቆ ሲጓዝ “ሽፍቶች” ያላቸው ታጣቂዎች መኪናውን በማስቆማቸው ዘሎ ሲያመልጥ እግሩ መሰበሩን ይናገራል።

ዝናቡ ምንም እንኳ ከእኔ የተሻለ አመራሮቹ ያውቃሉ ቢልም፤ ይህን ሁሉ ግፍ የፈፀሙ ታጣቂዎች “እንክብካቤ” ሳይሆን በሕግ መጠየቅ አለባቸው ብሎ ያምናል።

በማሕበረሰቡ ዘንድ እንደዚህ አይነት ቅሬታ እንዳለ አቶ መልካሙም ይስማማሉ። በተለይም የትኩረቱ አይን የተጣለው ታጣቂዎች ላይ ብቻ እንደሆነና በጥቃቶቹ ሕይወታቸው የተስተጓጎለባቸውን የማሕበረሰብ ክፍሎች ቸል ተብለዋል የሚሉ ወገኖችም አሉ።

በአካባቢው መንግስት ሌላም የመፍትሄ አማራጭ እየተሞከረ ነው። ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን፤ የመተከልን ጥቁር አሻራ ለማራገፍ እርቅ መፈፀም አለበት በሚል ከዞን እስከ ቀበሌ የወረደ የተለያዩ መርሃ-ግብሮች ተካሄደዋል።

ማንገማ፤ ባህላዊ እርቅ

እንደ የትኛውም ግጭት እንደሚከሰትበት ማሕበረሰብ መተከልም ባህላዊ የግጭት መፍቻ እሴቶች አሏት። ብዝኃነት ያላቸው ነዋሪቿ፤ በብሄረሰብ መሀልና እርስ በእርስ የሚከሰትን ግጭት ማረቂያ ዘዴዎች ዛሬም ቀጥለዋል። ከእነዚህም የእርቅ እሴቶች አንዱ በጎሳ ወይም በብሄር መካከል የሚነሱ ግጭቶች መፍቻ ዘዴው ማንገማ ነው። በጎሳ መካከል ያሉ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ሠላምን ለማስፋፋትና ግጭትን ለመከላከል የሚመሰረቱ ስለመሆናቸው አጥኚዎች ይናገራሉ። በመተከልም የተለያዩ ብሄረሰቦች አብረው ሲኖሩ በጊዜ ሂደት ቆለኛ የሚባሉትን የጉሙዞችን የሠላም እሴት ማንገማን ደገኞቹ ተለማምደው ተቀብለዋል።

አቶ ቦጋለ አሊጋዝ ማንገማ በ20ኛው ክ/ዘመን የነበረውን የግጭት ፍቺ አበርክቶን በዳሰሱበት ጥናታዊ ጽሁፋቸው፤ ማንገማ የጎሳ ግጭቶችን ለመፍታት በጣም አስፈላጊ የሆነ ባህላዊ ተቋም መሆኑን ያሰምራሉ። ይህ ዘዴ በእያንዳንዱ የመተከል አካባቢ ውስጥ ግጭቶችን በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና እንደነበረው ጠቅሰው፤ ይህም የሚያሳየው “ማንገማ እንደ ባህላዊ የግጭት መፍትሄነት ንቁ፣ ጉልህ እና በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ነው” ይላሉ።

ማንገማ በጉምዘኛ ጉባኤ ወይም ስብሰባ ማለት ነው። በተለያዩ የአካባቢው ቋንቋዎች ተመሳሳይ አልያም ተቀራራቢ ስያሜ ያለውና ዓላማውም ሠላም ማምጣት ነው። ለምሳሌ በኦሮሞኛ ሚቹ፣ በአገውኛና አማርኛ ወዳጅ፣ በሽናሸኛ ሀርማ ሆዳ ይባላል።

የማንገማ ስነ-ስርዓት

የማንገማ ስነ-ስርዓት ትርጓሜ ባላቸው ቁሳቁሶች ተመስሎ ግጭት ዳግም እንዳይከሰት መሀላ በመፈፀም ይከወናል። ስነ-ስርዓቱ ወንዝ ላይ የሚፈጸም ሲሆን፤ “እርግማን” ላይ የሚያተኩርም ነው። የስነ-ስርዓቱ ታዳሚዎች “እንዲህ አድርጌ ብገኝ እንዲህ ሆኜ ልቅር” እያሉ መሀላ ይፈጽማሉ። ወግና ባህሉን በሚያውቁ ትላልቅ የአገር ሽማግሌዎችም ይከወናል።

የአገር ሽማግሌዎች በመነጋገር ችግሩ (ግጭቱ) ላይ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ጥቁር በግ ይገዛል። በጉ ለችግሩ ክብደትና ላስከተለው ጉዳት ተምሳሌት ነው። ወደ ወንዝ ተሂዶም ጎጂና ተጎጂ ወንዙ ማዶ ለማዶ ሆነው ይቆማሉ። እንዳይተያዩም ነጭ ጨርቅ ተወጥሮ ይሰቀላል።

ጥይት፣ መብረቅ የመታው እንጨት፣ ቀርቀሀ፣ ጦር፣ የውሻ አይነ ምድር፣ ከሰል (የተቃጠለ እንጨት) ቆሮቆንዳ እንዲሁም ክብሪት ይዘጋጃል። ከዚያም ስነ-ስርዓቱ በጉን በማረድ ይጀመራል። በዳይና ተበዳል ደሙን በእጃቸው እየነኩ መሀላ ይፈጽማሉ።

ጥይቱን በመንከስ “መልሼ ወደ ግጭት ብገባ፤ ቃሌን ባጥፍ ይሄ ጥይት ይምታኝ፤ ወደ ግጭት ብመለስ ይሄ እሾህ ይውጋኝ፤ የእባብ ጭንቅላትን ረግጦ በማለፍም ዳግም ከበደልኩ እባብ ይንደፈኝ፤ ክፉ ከሰራሁ እንደ ድንጋዩ ያድርቀኝ፤ ዘሬ ይጥፋ…” እየተባለ መሀላው ይፈፀማል።

በደም በተነከረ እጃቸው እየተጨባበጡ፤ ግጭቱ (በደሉ) ዳግም እንዳይፈጸም ቃለ-መሀላ እንደሚደረግ የጉሙዝ ብሄረሰብ አፈ-ጉባኤ የሆኑት አቶ ጆንሴ ኢብሳ ይናገራሉ። በዳይ “ዳግም ይህን ባደርግ አጥንቴ ይሰበር፤ እርግማን እንደ እሾህ ይውጋኝ፤ አይለፍልኝ” እያለ ይምላል። የስነ-ስርዓቱ ታዳሚዎች መሬት ላይ እንደ ገመድ የተዘረጉ ቁሳቁሶችን ተራምደው እንዲሻገሩም ይደረጋል። ይህም ማሕበረሰቡ ያለፈን በደል ስለመተዉ፤ ይቅር ስለማለቱ ተምሳሌት ነው።

የማንገማ ስነ-ስርዓት ይቅር ባይነት የሚታይበትና ዳግም በደልን ላለመፈጸም ቃል የሚገባበት ነው። የስነ-ስርዓቱ ክዋኔ የሚያጠነጥነው ግጭት “ሁለተኛ እንዳይደገም” ነው። ከተደገመም በተገባው መሀላ መሰረት ቅጣቱ (እርግማኑ) እንደሚደርስ ይታመናል። የአገር ሽማግሌዎች “መሀላው ይይዛል፤ አይለቅም። በተለይ የመብረቅ እንጨት ክፉ ነው። ከተራመዱት አይለቅም” ይላሉ።

አቶ ለሚ ወንበራ የአገር ሽማግሌ ናቸው። ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በማሕበረሰቡ መሀል ግጭት ሲነሳ የማስታረቅ ኃላፊነትን እየተወጡ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ለመተከል ቁስል እንደ ሁነኛ መድኃኒት በተወሰደውና ማሕበረሰቡን እያንቀሳቀሰ ባለው እርቀ-ሠላም የአገር ሽማግሌም ናቸው። የእርቅ ስነ-ስርዓቱን ዓላማ ሲገልጹ፡

“ሠው ወደ ቤቱ ተመልሶ እሸት እንኳ ተክሎ እንዲበላ ነው ፍላጎታችን። በዚህም በዚያም ሠው ተጎድቷል። እና ይቅር ብላችሁ ታረቁ ነው። የጉሙዝ ማሕበረሰብም፤ ቀዩ [ከጉሙዝ ውጭ] ማሕበረሰብም ተጎድቷል። ይቅር ብላችሁ እንደበፊቱ አንድ ሆናችሁ ኑሩ ነው የምንለው፤ መንግስትም የሚለው።” ይላሉ።

አቶ ለሚ፤ “ማረጋጊያ” ሲሉ እየተካሄደ ያለውን እርቅ ይገልጻሉ።

ማንገማ ምንም እንኳ የጉሙዝ ባህላዊ የግጭት መፍቻ እሴት ቢሆንም በመተከል ዞን በሚኖሩ የተለያዩ ብሄረሰቦችም ተቀባይነት አለው። አቶ ጆንሴ ማሕበረሰቡ ለዘመናት አብሮ በመኖሩ በጋብቻና በሌሎች ማሕበራዊ መስተጋብሮች እንደተዋኸደው ሁሉ ባህሉን በእኔነት ተቀብሏል ይላሉ።

በአካባቢያቸው ይህን ጨምሮ እንደ ማንገማ ያሉ ቅቡልነት ያላቸው ግጭት መፍቻ መንገዶች ሞልተው ተርፈዋል። ጥያቄው ግን ግጭቶች ተመንድገው ከቁርሾም አልፈው፤ የተነጣጠሩ ጥቃቶች ሲበራከቱ፤ ማሕበረሰቡ ሲለያይ እነዚህ ዘዴዎች የት ነበሩ የሚለው ነው። አቶ ለሚ የመተከል ጥቃቶች ስረ-መሰረትና ምክንያት እንዲሁም ከጀርባ ያሉ ፍላጎቶች ለዘመናት የማሕበረሰባቸው መገለጫ አድርገው ከከወኗቸው የግጭት መፍቻ ዘዴዎች አቅም በላይ መሆኑን ይናገራሉ።

“የዘንድሮውማ አልተቻለም። ባሰ፤ ተባባሰ። እንደሚሉት ሌላ ነገር ነው። እኛ ግን ውስጡን አናውቀውም። ጉሙዞችን ስናናግር መተከልን ወደ አዊ ዞን ለመውሰድ ተፈልጓል ተብለን ነው የተነሳነው ይላሉ። እራሳችንን ለማዳን፤ መብታችንን ለማስከበር ነው የተነሳነው ነው የሚሉት።” በማለት ጉዳዩ ለሰሚ ቀላል እንደሆነው አይደለም ባይ ናቸው።

የጉሙዝ ብሄረሰብ አፈ-ጉባኤ አቶ ጆንሴ ኢብሳ ጥቃቶቹ ከመከሰታቸው አስቀድሞ እርቅ ማድረግ እንዳልተቻለ ያነሳሉ።

“ታጣቂዎች መብታችንን እስክናገኝ ድረስ ሠላም አንፈልግም፤ አንታረቅም ብለው አሻፈረኝ ስላሉ እንጂ፤ እርቀ-ሠላም ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት አልቦዘኑም” ይላሉ።

አቶ ጆንሴና አቶ ለሚ በእርቅ ስነ-ስርዓቱ ተስፈኞች የሆኑትን ያህል ነዋሪዎች ግን ቁጥብ ሆነዋል። ወ/ሮ መልኪቱ ወርቁ እርቁ እውነት ላይሆን ይችላል ብለው ከሚጠራጠሩት ወገኖች መሀል ናቸው። ለዚህም የሚያነሱት ምክንያት ለእርቅ የተቀመጡት ታራቂዎቹ (በዳዮቹ) ትክክለኞቹ ታጣቂዎች አይደሉም የሚል ነው።

“ዛሬ እዚህ እርቅ ቢሆን እዚያ [ሌላ ቦታ] እየገደሉ ነው። በእርቅ እነሱን ማን ያምናል? እርቅ ሲባል ደግሞ ሽማግሌ ሽማግሌው ነው የሚመጣው እንጂ ሽፍታ አይመጣም። አይመጣም ተደብቆ። በእርቁ ቀን ሌላ ቦታ ያጠቃሉ። ይኸ እርቅ ነው? እርቅ አይደለም።” ይላሉ።

በሌላ እይታ ደግሞ እንደ መተከል አይነት እልቂቶች በዳይ የበደሉን ያህል ቅጣቱን እንዲከፍል መደረግ አለበት የሚል አቋም የሚያንጸባርቁ ወገኖች ጉዳዩ በፍ/ቤት እንዲታይ ፍላጎት አላቸው። ከማሕበረሰቡ “በዳይ እየተካሰ ነው” የሚሉ ቅሬታዎች አሉ። የአካባቢው መንግስት ይህ ቅሬታ እንዳለ ቢናገርም፤ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ቁርሾን ማራገፍ ይገባል፤ ሌላ አመራጭ የለም በሚል አቋም እርቅ ላይ አተኩሯል። “ትላልቅ አሳዎች” ግን ለፍርድ እንደሚቀርቡና እየቀረቡ ሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ይናገራሉ።

ከግማሽ የሚልቀው የሕዝብ ቁጥሯ የተፈናቀለባት መተከል፤ አባጣ ጎርባጣውን የሠላም መንገድ የሙጥኝ ብላ ተያይዛዋለች። በሠላም ሠርተው ማደርን የሚመኙ እንደነ አቶ ደሳለኝ በሽር ያሉ ነዋሪዎቿ እፎይ ብለው እስኪተነፍሱ የቤት ስራ አለባት።

የአትኩሮት መንገዶች

የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ም/ሊቀ-መንበር አቶ መልካሙ ጃራ የመንግስት አሁናዊ ትኩረት መልሶ መቋቋም ላይ መሆን አለበት ይላሉ።

“ሕዝቡ በሠላም ወጥቶ በሠላም መግባትና ወደ መደበኛ ስራው መመለስ አለበት። ለታጣቂዎች የተሰጠው ትኩረት ለሌላው ማሕበረሰብም መሰጠት አለበት። ሕዝቡ የሚያርስበት በሬ አልቋል፤ ወድሞበታል። እና ሕዝቡ በእንጨትና በትናንሽ ብረት ለማረስ ተገዷል። ስለዚህ ሠላማዊው ማሕበረሰብም መረዳት አለበት። ሁለተኛው በርካታ ተማሪዎች የጉሙዝም፣ አገውም፣ አማራም፣ ቦሮ ሽናሻውም ወላጅ አልባ ሆነዋል። ቤተሰቦቻቸውን አጥተዋል፤ ንብረታቸው ወድሟል። የሚለብሱት የሚበሉት የላቸውም። ለእነሱ ምቹ የሆነ አዳሪ ትምህርት ቤት አይነት ገብተው መማርና ከስነ-ልቦና በደሉ ነጻ መሆን የሚችሉበት መንገድ መመቻቸት አለበት። ይህ ካልሆነ የሠላማዊው የማሕበረሰብ ችግር አይፈታም።”

ለመተከል ቀውስ መወሳሰብ የአካባቢው መንግስት ሰርጎ-ገቦች የሚላቸው መሪዎች ከምክንያቶች ውስጥ ናቸው። አቶ መልካሙ አሁንም አስተዳደሩ አልጠራም ይላሉ። አካባቢው የልማት ኮሪደር በመሆኑ ኮንትሮባንድን ጨምሮ ለህገ-ወጥ ስራዎች የተጋለጠ ነው ሲሉ መንግስት ለዘለቄታዊ ሠላም ሲል ቤቱን እንዲያጸዳ ምክረ-ሃሳብ ያቀርባሉ። 

የሠላምና ልማት ባለሞያው አቶ ዳኛቸው ትልቁ ስራ” ነባርና መጤ” የተባሉት ሁለቱ ወገኖች ጎደለን የሚሏቸውንና የሚፈልጓቸውን ታሪካዊ ውርሶች ማጎናጸፍ ያስፈልጋል ሲሉ፤ ለመተከል የአትኩሮት መንገድ ይጠቁማሉ። ለጉሙዝ ማሕበረሰብ አኗኗሩን ያማከለና እሽታውን ያስገኘ የምጣኔ-ሀብት አማራጭን፤ ከጉሙዝ ውጭ ለሆኑትና “መጤ” ተብለው ከስልጣን ለተገለሉት ነገር ግን ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከግማሽ ለሚበልጡት ደግሞ የፖለቲካው በር ሊከፈትላቸው ይገባል። ይህ ሲሆን ነው ዘላቂ ሠላም ሊመጣ የሚችለው ይላሉ።

መተከል ትናንት፣ ዛሬና ነገ፤ ታሪክ፣ ውርስና የሁለት ወገን በደል፤ በአባጣ ጎርባጣው መንገድ ወደ ፊት ምን ይገጠማት ይሆን? ችግሯስ ይቀረፍ ይሆን? ጊዜ ብቻ የሚመልሰው ሆኗል።

አስተያየት