ግንቦት 10 ፣ 2014

እየተባባሰ የመጣው የእሳት አደጋ አሳሳቢነት

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

በመዲናዋ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የእሳት አደጋ ጭማሬ ማሳየቱ ተገልጿል

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

እየተባባሰ የመጣው የእሳት አደጋ አሳሳቢነት

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእሳት አደጋ ተከስቶ ያደረሳቸውን ጉዳቶች በዜና መስማት እየተበራከተ መጥቷል። ሰዎች እድሜ ልካቸውን ለፍተው ያካበቱትን ሀብት ንብረት በአንድ ቅፅበታዊ ክስተት ወደ ዶግ አመድነት የሚቀይረው ይህ አስከፊ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስጊነቱ ሲጨምር ይስተዋላል።

በአዲስ አበባ ከተማም ይህ አደጋ በተደጋጋሚ የሚከሰት ሲሆን፣ ባሳለፍናቸው ዘጠኝ ወራቶች በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ 377 የእሳት አደጋዎች መድረሳቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በዚህ ሳቢያ ከ450 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም፣ የ13  ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ እና ክ100 ሰዎች በላይ ድግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጉ ተገልጿል። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሬ ማሳየቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የእሳት አደጋ ጉዳይ አሁን እየተሰጠው ካለው የተሻለ ትኩረት እንደሚያሻው ይጠቁማል።

“የነዚህ እሳት አደጋዎች መደጋገም መንስዔ ምንድነው?” ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ “ሁሉም እሳት አደጋዎች ለማለት በሚያስደፍር መልኩ መንስዔያቸው የጥንቃቄ ጉድለት እና ቸልተኝነት የሚያስከፍላቸው ዋጋዎች ናቸው” ሲሉ መልሰዋል።

እንደ ባለሙያው ገለፃ ከሚከሰቱት የእሳት አደጋዎች መካከል ከ85% በላይ የሚሆኑት በማህበረሰቡ መዘናጋት ሲሆን፣ የቀሩት 15% ደግሞ በተፈጥሮአዊ ሁነቶች ይፈጠራሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ማዕከሉን ጨምሮ አስር የእሳት አደጋ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ቅርንጫፎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ንጋቱ፣ ሁሉም ቅርንጫፎች  የ 24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት ክፍት እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ለእሳት አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን ሲጠቁሙ አዲስ አበባ ስትመሰረት ጀምሮ የነበሩ ቀዳሚ የሚባሉ ሰፈሮችን ይጠቅሳሉ። “እንደ ቂርቆስ፣ አዲስ ከተማ፣ ፒያሳ እና መሰል ነባር መንደሮች ከፕላን ጋር ተያይዞ መሰረታዊ ችግር ስላለባቸው ለአደጋ የተጋለጡ ያደርጋቸዋል” በማለት በነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ የገበያ ቦታዎች፣ የመኖርያ ቤቶች እና የንግድ ሱቆች ከፍ ያለ ጥንቃቄ ካልተደረገባቸው ተጎጂ እንደሚሆኑ ይናገራሉ።

ከነዚህ በተጨማሪም ፋብሪካዎች የተተከሉባቸው አካባቢዎችም ሌላ ተጋላጭ ተብለው የተለዩ ቦታዎች መሆናቸውን ይጠቁማሉ። “በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ ፋብሪካዎች ላይ ሁሉ የድንገተኛ እሳት አደጋ መኪናዎች ማቆም ስለማይቻል፣ ሰራተኞች እና በውስጡ የሚንቀሳቀሱ ግለሶች ሁሉ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንመክራለን” ይላሉ ባለሙያው። አያይዘውም እነዚህ ተጋላጭ ቦታዎች ተብለው ተለዩ ማለት ያልተጠቀሱ ቦታዎች ከአደጋ ነፃ ናቸው ማለት ስላልሆነ ሁሉም ሰው ጥንቃቄ ሊለየው እንደማይገባ ያሳስባሉ።

እሳት በፍጥነት ለማጥፋት ተብለው በየቦታው ተሰቅለው የሚታዩት የእሳት ማጥፊያ መሳሪያዎች የንግድ ተቋማት እና ልዩ ልዩ ቦታዎች ላይ አለ ለማለት ያህል ከመስቀል ባለፈ አጠቃቀሙ ላይ ብዙኃኑ እምብዛም እውቀት ያለው እንደማይመስልም የእሳት አደጋ መከላከያ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህን ሲያስረዱም በአዲስ አበባ በሚገኙ አንዳንድ የንግድ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ሳይቀሩ በግድግዳ ላይ የሰቀሉትን የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ አጠቃቀም እንደማያውቁት ትዝብታቸውን ተናግረዋል።

የእሳት ማጥፊያ መሳሪያዎች በቀለም ቀይ መሆናቸው ያመሳስላቸው እንደሆን እንጂ ለአንዱ የምንጠቀመው ለሌላ እንደማያገለግል የአጠቃቀም መመሪያዎች ያሳያሉ። በዚህም ለእንጨት ቃጠሎዎች፣ ለወረቀቶች፣ ለተቀጣጣይ ፈሳሾች፣ እንዲሁም ለኤሌክትሪክ ቦታዎች እንደየአይነታችው የሚስማማቸው የማጥፊያ መሳሪያዎች እንዳላቸው ይታወቃል።

የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል በንግድ ሱቆች፣ በሆቴሎች እና በነዳጅ ማደያዎች የሚቀመጡ የእሳት ማጥፊያ መሳሪያዎችን መቆጣጠር እና በተገቢው መንገድ አገልግሎት ላይ እየዋሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ አንዱ ነው። ነገር ግን በየቦታው የሚታዩት የግንዛቤ እጥረቶች ስራው ምን ያህል እየተሰራ እንደሚገኝ ጥያቄ ያስነሳሉ።

ይህን አስመልክቶ ማብራሪያቸውን የሰጡን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው “ኮሚሽን መስርያ ቤቱ አደጋ ቅነሳ የሚባል ስራ ይሰራል፣ በዚህም አደጋ ከመድረሱ በፊት እንዴት እንዳይከሰት ማድረግ እንደሚቻል እና ከደረሰ እንዴት መከላከል ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ ትምህርት እና ስልጠና ይሰጣል” ብለዋል። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ከተካተቱ ተግባራት በየቦታው ተሰቅለው የምንመለከታቸውን የእሳት ማጥፊያ መሳሪያዎች ማንኛውም ሰው እንዴት መጠቀም እንደሚችል ግንዛቤ መፍጠር አንዱ ነው።

ስልጠናዎቹ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎቹ በተለያዩ መድረኮች እንደሚደረጉ የሚናገሩት አቶ ንጋቱ “የግንዛቤ ክፍተቱ የተፈጠረው እኛ የምናሰለጥናቸው የተለያዩ ግለስቦች ለስራ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም በቅርባቸው ለሚገኙ ሰዎች ያወቁትን መልሶ ለማሳወቅ የሚያደርጉት ጥረት አናሳ በመሆኑ ተደራሽነቱ ስለሚቀንስና ከዚያም ባለፈ ስልጠናውን ያገኙት ሰዎችም ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ቸልተኛነት ስለሚታይባቸው ነው” ብለዋል።

የህዝብ ግንኙነቱ እንደገለጹት አንድ ጊዜ የተገዛ የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ በአመት ሁለቴ፣ ማለትም በስድስት ወር አንዴ በኮሚሽኑ ፍተሻ ሊደረግበት እንደሚገባም አሳውቀዋል። በተጨማሪም የእሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ፍተሻ ያደረገባቸው መሳሪያዎች ላይ የማረጋገጫ ስቲከር እንደሚለጥፍ በመጠቆም ወደ ኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ቢሮዎች መከላከያዎቹን ወስዶ የማያስፈትሽ አካል ለአደጋ ተጋላጭነቱ የሰፋ እንደሆነ ያሳስባሉ።

በሌላ በኩል “በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ የሚደርሱትን የእሳት አደጋዎች አስቀድሞ መቆጣጠር እንዳይቻል የእሳት አደጋ ባለሙያዎች ዘግይተው ነው የሚደርሱት” የሚሉ ስሞታዎችን ከማህበረሰቡ መስማትም የተለመደ ነው።

የህዝብ ግንኙነቱም እነዚህን ቅሬታዎች እንደሚሰሙ በማመን “መዘግየት አይፈጠርም ማለት አይቻልም፣ ነገር ግን መዘግየቱን የሚያስከትሉት ገፊ ምክንያቶች ናቸው” ይላሉ።

ምክንያት ያሏቸውን ሁኔታዎች ሲያብራሩም በአንደኛነት የሚያስቀምጡት ማህበረሰቡ በተገቢው ሰዓት ወደ ኮሚሽኑ አለመደወሉን ነው። ይህንንም ሲያስረዱ “ተደውሎ የእሳት አደጋ መድረሱ ካልተነገረን የምናውቅበት ምንም መንገድ የለም፣ ባደጉት ሀገራት የእሳት አደጋ መከሰቱን እና ቦታውን ለመከላከያ ቢሮዎቹ የሚያመላክቱ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች አሉ፣ በሀገራችን ግን ይሄ ስለሌለ በፍጥነት አደጋ ሲከሰት ወደኛ መደወል ያስፈልጋል” ብለዋል።

እንደ አቶ ንጋቱ ገለጻ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል የእሳት አደጋ ቢሮን ስልክ ቁጥር በትክክል የማያውቀው ሲሆን፣ አደጋ ሲከሰት ስልኩን የሚያውቅ ሰው ራሱ የሚደውለው ዘግይቶ መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም የእሳት አደጋ ሰራተኞችን መድረሻ ሰዓት የሚያየው ሰው ጊዜውን የሚያሰላው አደጋው ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን እንጂ ደውሎ ጥቆማውን ካቀረበበት ሰዓት ጀምሮ ያለውን ባለመሆኑ ነው እንደተዘገየ የሚያስበው ይላሉ።

እንደ ሌላኛ ምክንያት ደግሞ የሀገሪቱ የመንገድ አጠቃቀምን ያነሳሉ። በዚህም ረገድ ያደጉት ሀገራት ለአደጋ መከላከያ መኪናዎች የተለዩ መንገዶች እንዳላቸው በማንሳት በሀገራችን ግን ከሌሎች መኪናዎች ጋር እየተጋፉ መሄዳቸው እንደሚያዘገያቸው አስረድተዋል።

ይህን የህዝብ ግንኙነቱን ሃሳብ የሚያጠናክሩት አቶ ሻሼ ተክሉ የተባሉ የእሳት አደጋ መከላከል ሰራተኛ ናቸው። “መንገድ ላይ ሳይረን እያሰማን ስናልፍ ትራፊኮች መንገድ ለማስከፈት ቢሞክሩም አንዳንድ ሹፌሮች ግን ተባባሪዎች አይደሉም፣ አውቀን የሚመስላቸው ሁሉ አሉ” በማለት የህብረተሰቡ የትብብር ማነስ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ያስቀምጣሉ።

ሌላው የሻሼ አስተያየት “እሳቱ ትንሽ ነው እኛው እንቆጣጠረዋለን” በማለት ወደ እሳት አደጋ በጊዜ የማይደውሉ ግለሰቦችን ይመለከታል። ከዚህ አንፃር እሳት ሲፈጠር ምንም ሳያወላውሉ ሰዎች በቅድሚያ ወደ እሳት አደጋ ቢሮ መደወል እንዳለባቸው ያሳስባሉ። 

“ወደ እሳት አደጋ የመስመር ስልክ እየደወሉ የሚቀልዱም አሉ” የሚሉት ደግሞ አቶ ምትኩ ፋንታሁን የተባሉ የኮሚሽኑ ስልክ ተቀባይ ሰራተኛ ናቸው። እንዲህ አይነት ግለሰቦች ምን ጥቅም ለማግኘት እንደሚቀልዱ ባይታወቅም፣ በእነርሱ ሳቢያ ለትክክለኛ አደጋ ክፍት መሆን ያለበትን የስልክ መስመር እንደሚያጨናንቁ በመረዳት ከእኩይ ተግባራቸው ሊታረሙ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው በበኩላቸው ኮሚሽን መስርያ ቤቱ ሁሉም ማህበረሰብ አጭር እና ረዣዥም የእሳት አደጋ ቢሮ ስልክ ቁጥሮችን እንዲይዙ ከመምከር ባለፈ፣ አደጋ ከመድረሱ በፊት ስለሚደረጉ መከላከያ ዘዴዎች ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ጋር በመተባበር እና የአየር ሰዓት ጭምር በመግዛት የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችንም እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ታዲያ ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም ድረስ የእሳት አደጋ እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረ መምጣቱ አልቀረም፣ ይህን ለመቀነስም ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

 

አስተያየት