ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ በቀን መቁጠሪያ “ካሌንደር” ዝግ መሆኑ ተቀምጦ አንደ ህዝብ በዓል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ደምቆ ሲከበር የአንድ ወጣት እድሜን ያስቆጠረው ግንቦት 20 ሠላሳኛ ዓመቱ ሲቃረብ መከበሩ አጠያያቂ ሆኗል፡፡ “ሥራ ዝግ ነው አይደለም?” “ተከብሮ ይውላል ታስቦ?” የሚለውን ጥያቄ በርካቶችን ለባለፉት ሁለት ዓመታት እያነጋገረ ይገኛል፡፡
ለመሆኑ ግንቦት ሃያ ሲከበር የኖረው በልምድ ወይስ በሕግ?
የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀንን በሚመለከት ሥርዓት የሚያስይዙ ሕግጋት የወጡት በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ነው፡፡ የአፄውን በተከተለው የደርግ አገዛዝ ዘመንም አዲስ ሕግ ወጥቷል፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜም እንዲሁ መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው በ1967 ዓ.ም. የወጣው የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀን አዋጅ ቁጥር 16/1967 እና ይህንን ተከትሎ በዚሁ ዓመት የወጣው የሕዝብ በዓላት አከባበር አዋጅ ቁጥር 28/1967 እንዲሁም በ1985 ዓ.ም. የወጣው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የሥራ ቀንና ሰዓት የሚወስነው አዋጅ ቁጥር 43/1985 ናቸው፡፡
አዋጅ ቁጥር 16/1967 ሲወጣ ከያዛቸው ዓላማዎች ውስጥ “የኢትዮጵያውያንን እኩልነትና አንድነት ለማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑ”፣ “ሕዝቡ ጊዜውን በተለያዩ ስርዓት አልባ የዕረፍት ቀናት ሳያሳልፍ የሥራን ጠቃሚነት የበለጠ እንዲረዳና እንዲያምን አስተዋጽኦ ማድረጉ” እና “በታሪክም፣ በሃይማኖትም፣ በልማድም የሚከበሩ በዓላትን ሳይዘነጉ ማሰብና ማክበር አስፈላጊ መሆኑ” ዋነኞቹ እንደሆኑ በአዋጁ ላይ ተደንግጓል።
በአዋጅ ያልተሻሩ ነገር ግን በተግባር የማይከበሩ፣ በአዋጅ ያልተድነገጉ ነገር ግን በይፋ ከሚከበሩ በዓላት መካከል መስከረም 2 እና ግንቦት 20 ይጠቀሳሉ፡፡ አዲስ ዘይቤ እነዚህን በዓላት አስመልክቶ የሕግ ባለሙያ ማብራሪያ ጠይቃለች፡፡ የሕግ ባለሙያው አቶ ልኩ ወርቁ መስከረም ሁለት 'የለውጥ ቀን' ተብሎ ይከበር እንደነበር ከማስታወስ ይጀምራሉ፡፡
“መስከረም ሁለት በሕግ የታወቀ ቢሆንም በአሁን ሰዓት በሕግ ባይሻርም በተግባር መከበሩ ቀርቷል፡፡ ግንቦት ሃያም እንደዚሁ በሕግ ሳይሆን በገቢር በዓል ሆኗል፡፡ እነዚህ በዓላት ላይ ያለው ነገር በሕግ መፅናቱ የማይቀር ሲሆን ለእዚህ አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ እስኪሟላ ጊዜ ስላስፈለገ ብቻ ዘግይቷል።’’ ሲሉ አስረድተዋል።
በባለፉት ሦስት ዓመታት ከመጣው የአስተዳደር ለውጥ ጋር ተያይዞ ግንቦት 20ን ተከብሮ ከመዋል ታስቦ ወደ መዋል እየተንደረደረ ይመስላል፡፡ ካሌንደር ይዘጋዋል ወይስ የሥራ ቀን ነው? የሚል ውዝግብ በሰፊው እየተደመጠ ይገኛል፡፡
ለመሆኑ ይህ ጥያቄ ከሕጉ አንጻር እንዴት ይፈታል? ለሚለው የአዲስ ዘይቤ ጥያቄ አቶ ልኩ ሲመልሱ “በዘመነ ኢሕአዴግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 43/1985 ዐቢይ ትኩረቱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የሥራ ሰዓት መወሰን ነው። እንደ አዋጁ ድንጋጌ በሕግ በዓላት እንዲሆኑና እንዲከበሩ የተወሰኑትን ቀናት ማክበር ግዴታ ነው፡፡ ይህንን መተላለፍ በደንብ መተላለፍ የሚያስቀጣ ያልተፈቀደ ተግባር ነው፡፡ ደንብ ተላላፊነቱ የሚመነጨው በዓሉን ካለማክበር ነው፡፡ የበዓላት አከባበር ሥርዓቱን አለመከተልም እንዲሁ በገንዘብ አሊያም እስከ 8 ቀን የሚደርስ እስራት ያስቀጣል፡፡ ይህ የደንብ መተላለፍ ተጠያቂነት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 817 ላይ ተደንግጓል፡፡ አስጠያቂነቱ በአሁኑ የወንጀል ሕግ ብቻ ሳይሆን በቀድሞውም ሕግ ላይ የነበረ ሲሆን የመንግሥት፣ የግልና የንግድ ተቋማት ሕዝባዊ አገልግሎት እንዳይሰጡ በተባለበት ቀን አገልግሎት ሲሰጡ ከተገኙ የደንብ መተላለፍ እንደሆነ ደንግጓል፡፡
ሕጉ የበዓላት አከባበር ሥርዓት ምን መምሰል እንዳለበት የመወሰን ያለባቸውን አካላትንም አስቀምጧል፡፡ እነዚህ አካላት የሚያወጧቸውን የአከባበር ደንቦች መጣስም እንዲሁ ደንብ ተላላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን በአዋጁ ያልተካተቱ በገቢር ግን የሚከበሩ እንደ ግንቦት 20 ያሉ በዓላት ላይ መስሪያ ቤቶች በስምምነት ካልዘጉ በስተቀር በሕግ አይገደዱም” ሲሉ አብራርተዋል።
ከላይ ያነሳናቸው ሕግጋት በትግበራ ላይ ያላቸው ጉራማይሌ መልክ አንዱ ህጸጻቸው ነው፡፡ በአዋጆቹ ላይ በበዓልነት ዕውቅና ቢሰጣቸውም፣ በሌላ አዋጅ ባይሻሩም በገቢር የቀሩና በሕግ የበዓል ቀን መሆናቸው ሳይደነገግ የሚከበሩ መኖራቸው ለሕግ የተሰጠው ዋጋ እያሽቆለቆለ መሄዱን፣ እንቅስቃሴአችን ሕግጋትን ያልተከተለ መሆኑን ያሳያል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ በማሳያነት የሚያቀርቡት ደግሞ ግንቦት ሃያን እና መስከረም ሁለትን ነው፡፡
በዚህም ከላይ ያነሳነውን ጥያቄ በአጭሩ ስንመልስ ግንቦት 20 አዋጁ ላይ አልተደነገገም፡፡ ስለዚህ የሰራተኛ እና አሰሪ ሕጉ አይመለከተውም፡፡ ነገር ግን በአሰሪውና ሰራተኛው ስምምነት እለቱን የእረፍት ወይም የበዓል ቀን ማድረግ ይችላሉ፡፡ መስከረም ሁለት እስካሁን በአዋጅ አልተሻረም፡፡ አንድ ሰው እለቱን እንደ በዓል ቆጥሮ ስራ አልገባም ብሎ ጉዳዩን ወደ ፍርድቤት ቢወስደው በሕጉ በቂ የመከራከሪያ ነጥብ እለው፡፡