በአፍሪካ መዲናዋ አዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር መስማት እና መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ግምታዊ መረጃዎች ከስድስት ሚልዮን በላይ ህዝብ እንደሚኖርባት ቢያሳይም፤ የተሽርካሪዎቿ ብዛት ከተጠቃሚዎቿ ጋር የተመጣጠነ አይደለም፡፡ የትራንስፖት እጥረት እና የፍሰት መጨናነቁ በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ላይ ይበልጥ ይባባሳል፡፡
ፒያሳ አከባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ስመኝ ሺመልስ የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት ከተፈተኑት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አንዷ ናቸው። ወይዘሮ ስመኝ በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት በትራንስፖርት ጥበቃ ከአንድ ሰዓት በላይ እንደሚያሳልፉ ነገረውናል። ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው የሚወስዳቸውን መጓጓዣ በመጠበቅ ከሚያጠፉት ጊዜ በተጨማሪ በመንገድ መጨናነቁ ምክንያት ረዘም ያለውን ከሥራ ውጭ ያለውን ጊዜ መንገድ ላይ ያሳልፋሉ። በዚህ ሂደት የሚያጠፉት ጊዜ የትራፊክ መጨናነቅ ከሌለበት ጊዜ ጋር ሲወዳደር በእጥፍ ብልጫ እንዳለው ነው የሚናገሩት።
በሹፍርና ህይወቱን የሚገፋው አቶ ባህሩ ይልቃል የወይዘሮ ስመኝን ሃሳብ ይጋራል።
''15 ደቂቃ የሚፈጅ መንገድ በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ከ2 ሰዓት በላይ ሊወስድ ይችላል፤ ይህ ለእኛም ለተሳፋሪውም በጣም አድካሚ እና አሰልቺ ነው'' የሚለው ባህሩ ይህን ችግር ለማቃለል አንዳንዴ በሕገ-ወጥ መንገድ ማለትም (ደርቦ በማለፍ፣ ባልተፈቀደ ተመላሽ ተሽርካሪዎች መንገድ በመሄድ፣ በመንደር ውስጥ ለውስጥ መንገዶች በመሄድ፣ በእግረኛ መንገድ ላይ በመንዳት) ጊዜውን ለመጠቀም እንደሚሞክር ገልጾ ይህም በትራፊክ ፖሊስ ቅጣት አስከትሎበት እንደሚያውቅ ይናገራል።
በተሽከርካሪ እጥረት ምክንያት ከተሳፋሪ በሚመጡ ጥያቄዎችና ፍላጎት መሰረት የሰውን ችግር ለማቃለል ከተፈቀደው የሰው ቁጥር በላይ አገልግሎት እንደሚሰጥ ይልቃል ይገልጻል።
የነዋሪው እና የመኪኖች ቁጥር አለመጣጠን፣ አብዛኛው መኪና የግለሰብ መሆን፣ ውስን የመንገድ አገልግሎት መኖር እና የመንገዱ አሰራር ቦታ ቆጣቢ በሆነ መንገድ አለመሰራቱ በከተማዋ ውስጥ ላለው ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግሮች አሁን ያለውን እጥረት እና መጨናነቅ የፈጠሩ ዋና ዋና ሰበቦች መሆናቸውን አቶ ይልቃል ያስቀምጣል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት 630ሺህ 440 ተሽከርካሪዎች መካከል130ሺህ የሚሆኑት ከስድስት ሚልዮን በላይ ለሚገመተው የከተማዋ ነዋሪ የትራንስፖርት አግልግሎት ይሰጣሉ። ከአንድ የከተማዋ ጥግ ወደ ሌላው ወስደው ይመልሳሉ፡፡
"የመኪና መብዛት እና አማራጭ መንገድ ባለመኖሩ የከተማዋ የመኪና እንቅስቃሴ የተጨናነቀ ነው" የሚለው ሰለሞን አወቀ በረጲ ሳሙና ፋብሪካ ውስጥ በሹፍርና ሙያ የሚያገለግል ሲሆን በትራፊክ መጨናነቁ ምክንያት የሚባክነው ጊዜ ድርጅቱን እንዳከሰረ ይናገራል።
"ችግሩን ለመቀነስ ከዋና መንገዶች ይልቅ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ለመጠቀም እሞክራለው" በማለት እንደ መፍትሄ የተጠቀመውን አማራጭ አስቀምጧል። እንዲሁም መጨናነቁን ለመቀነስ መኪኖች የሚንቀሳቀሱበት ሰዓት በ'ኮድ' ቢከፈል የተሻለ ነው ብሎ እንደሚያምን ሀሳቡንም አጋርቷል።
አቶ አረጋዊ ማሩ የአ.አ ትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የችግሩን ግዝፈት በመዘርዘር የሰለሞንን የመፍትሔ ሃሳብ በተወሰነ መልኩ ይጋሩታል።
በኮቪድ ስርጭት ሳቢያ ኮድ ሁለት ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱበት ሰዓት ትከፋፍሎ የነበረው መመሪያ መነሳቱን እና የትራፊክ ፍሰቱ ሁኔታ ታይቶ ዳግም ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል አቶ አረጋዊ ይናገራሉ። በተጨማሪም የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ከቀኑ 10 እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት እንዳይንቀሳቀሱ የወጣ መመሪያ መኖሩንም አክለዋል።
በአዲስ አበባ ከሚገኙት 630ሺህ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 208ሺህ ያህሉ ኮድ 2 ማለትም የግል መሆናቸውን የሚናገሩት ኃላፊው ኅብረተሰቡ ወደ ብዙኃን ትራንስፖርት ትኩረት እንዲያደርግ እና የመንገድ መጨናነቁ እንዲቀንስ ምቾት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው ይላሉ። እንደ ምቾት የጠቀሷቸውም በመንግሥት የሚተዳደረው የብዙኃን አገልግሎት ሰጪ አውቶብስ ከሌሎች የትራንስፖርት ሰጪዎች ጋር ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ማድረግን ነው፡፡ 'የሸገር ባስ ድጋፍ ሰጪ' የሚባሉት ለዚህ ዋነኛ ማሳያ እንደሆኑም ይናገራሉ። በተጨማሪም ለብዙኃን ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የሚሆን መንገድ ይዘጋጃልም ብለዋል።
ለብዙኃን ትራንስፖርት የሚውል 14ሺህ ተሽከርካሪ መኖሩን የሚናገሩት ኃላፊው ከዚህም ውስጥ በተለያየ ምክንያት አገልግሎት በመስጠት ላይ የማይገኙትን በመቀነስ ከ10ሺህ እስከ 10ሺህ 500 የሚገመቱ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ያብራራሉ። ከነዚህም ውስጥ ወደ 815 የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች የከተማ አውቶብስ፣ ሸገር ባስ እና የሸገር ባስ ድጋፍ ሰጪዎች ናቸው።
በአጠቃላይ እነዚህ መኪናዎች ለ2.7 ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ኃላፊው ተናግረዋል። እንዲሁም ከኮቪድ19 ስርጭት ጋር በተያያዘ አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉ ሰዎች ቁጥር ውስን መሆኑን የገለጹ ሲሆን ይህም የትራንስፖርት እጥረት እንዲጨምር ሊያደርግ እንደሚችል ስጋታቸውን አጋርተዋል። ነገር ግን ከትራንስፖርት እጥረት እና ከበሽታው አስጊነት አንጻር 'ከሁለቱ አንዱን መምረጥ' ግዴታ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰሎሞን በከተማዋ ውስጥ ከ100 በላይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን፤ የተጎዱ መንገዶች ጥገና በብዛት እየተከናወነ መሆኑ ችግሮችን ሊያቃልል ይችላል ብለው ያምናሉ። ነገር ግን ሁሉንም ተደራሽ ለማድረግ የአቅም ውስንነት መኖሩንም አክለዋል።