በሁለት የጎንደር ከተማ የገጠር ቀበሌዎች ለቀናት የዘለቀው የተኩስ ልውውጥ “ጎንደርን ለማወክ የፈለጉ ኃይሎች” በተፈጸመ ጥቃት የተነሳ መሆኑን የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ ገልጸዋል። የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት አካባቢውን ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ እንደሆነም ከንቲባው አክለዋል። ካሳለፍነው ሳምንት የመጀመርያ ቀናት አንስቶ በጎንደር ከተማ ዙርያ በሚገኙ ሁለት የገጠር ቀበሌዎች በተኩስ ድምጽ እየተናጡ መሆናቸውን የአካባቢውነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ አስረድተዋል። እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ገለፃ የተኩስ ልውውጡ ለቀናት ያህል ቀን እና ምሽት ሳይቋረጥ መሰማቱ ነዋሪዎችን አስግቷል፡፡ ሁነቱን ተከትሎ ከተገቢው የመንግሥት አካል ማብራሪያ በወቅቱ አለመሰጠቱ ነገሩን ከማባባሱም በተጨማሪ ያልተረጋገጠ መረጃ እንዲሰራጭ ምክንያት መሆኑን ነዋሪዎቹ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ተኩስ ከተጀመረ ከኣራት ቀናት በኋላ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ ለከተማዋ ራዲዮ በሰጡት ማብራሪያ ጎንደርን ለማወክ የፈለጉ ኃይሎች “ቁስቋም” እና “ዳብርቃ” በተባሉ አካባቢዎች ላይ በፈጸሙት የድንገቴ ጥቃት መኖርያ ቤቶችን አቃጥለዋል ብለዋል።
እንደ ከንቲባው ማብራሪያ “ጽንፈኛ የቅማንት ታጣቂ ሽፍቶች” እና “የህወሓት ርዝራዥ” ብለው በገለጹዋቸው አካላት እየተፈፀሙ ያሉትን ጥቃቶች ለመመከት በአሁኑ ሰዓት የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሕግ የማስከበር እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት የከተማውም ሆነ የዙሪያው አስተዳዳር የፀጥታ ችግሮችን ቀድሞ መከላከል ላይ የክልሉና ያካባቢው መስተዳድሮች ድክመት እንዳለባቸው ይገልፃሉ። ከተማ መሀል ሰዎች እየተገደሉና እየታፈኑ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት የሕግ ባለሙያው አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ እንዲሁ “የበዛ” ብለው በገለጹትን የከተማ አስተዳደሩን ቸልተኝነት ለሚፈጠሩት የጸጥታ ችግሮች ቀዳሚ ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡
ይህ የፀጥታ ችግር በዋነኝነት የከተማ አስተዳደሩ ግዙፍ ቸልተኝነት የወለደው ነው፡፡ ሰዎች ወጥተው መግባት ጭንቅ እንዲሆንባቸው ያደረገው የጸጥታ መዋቅሩ ተቀናጅቶ አለመሥራቱና መዳከሙ ነው” የሚሉት የሕግ ባለሙያው ይህንን ክፍተት ተጠቅሞ የራሱን ዐላማ የሚያራምደው “የቅማንት ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ” ሲል ራሱን የሚጠራው ቡድን ተጠያቂ እንደሆነ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
በየትኛውም በጎንደር ዙሪያ ባሉ ቀበሌዎች የሚኖር የቅማንት ብሄረሰብ ተወላጅ እንደማንኛው አርሶ አደር ከክላሽ ያለፈ ትጥቅ እንደሌለው የሚጠቅሱት የሕግ ባለሙያው ይህ ኃይል ግን በአገር መከላከያ ሠራዊት የሚያዙ ከባድና የቡድን የጦር መሳሪያዎችን ታጥቋል ባይ ናቸው፡፡ የሚተኩሷቸውን ከባድ መሳሪያዎችንም ድምጽ በማስረጃነት ያነሳሉ። ይህንን አቅርቦትና ድጋፍ በመጠቀምም ከባለፈው ወር ጀምሮ በነባሩና በአዲሱ የጭልጋ ወረዳ አንዳንድ ቀበሌዎች፣ አይከል ከተማ፣ ሮቢት ንዑስ ወረዳ ላይ የፀጥታ ችግር ፈጥሮ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን እንዳይረጋጋና የሽብር ቀጠና ለማድረግ አብዝቶ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ቴዎድሮስ መረጃ እንዳላቸው ይገልጻሉ።
ይህንን ኃይል ወደ ሕግ ለማቅረብ አቸጋሪ የሆነበትን ምክንያትም የሕግ ባለሙያው ያነሳሉ። ወቅትና ጊዜ እየጠበቀ የደፈጣ ጥቃት ሰንዝሮ ስለሚሸሽ፣ ይህን ጥቃት ከፈፀመ በኋላ ሄዶ የሚመሽገው ከሰላም ፈላጊው የቅማንት ህዝብ ውስጥ መሆኑ፤ ከመሸገበት የቅማንትና የአማራ ህዝብ መኖርያ ቀዬዎች እርምጃ እንዳይወሰድበት በንፁኃን ላይ የጎንዮሽ ጥቃት ስለሚደርስ እና ይህን እርምጃ መንግሥት ቢወስድ ይህ ጽንፈኛ ኃይል ጉዳዮን ለፓለቲካ ፕሮፓጋንዳ ከመጠቀም ባሻገር የቅማንት ህዝብ ላይ ጥቃት በመሰንዘር መንግሥት እንደፈፀመው አድርጎ በማሳየት በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ስለሚያደርስ ነው ይላሉ።
መንግሥት ኃላፊነት የሚሰማው፣ በሕግ የሚተዳደርና በማኅበራዊ ስምምነት የመሰረተ የአስተዳደር ስርዓት ስለሆነ ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን የሚወጣው በንፁሃን ላይ የጎንዮሽ ጉዳት (collateral damage) በማይደርስበት ሁኔታ በመሆኑ ይህ የጎንዮሽ ጎዳት መድረስ ስለሌለበት ጽንፈኛ ኃይሉ ከህዝብ ውስጥ ስለመሸገ ረዘም ላለ ጊዜ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን አቶ ቴዎድሮስ አስምረውበታል፡፡