ግንቦት 23 ፣ 2013

የመገናኛ ብዙኃን ባለልጣን የሐይማኖት ጣቢያዎችን ምዝገባ ማራዘሙን ገለፀ

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚጀመር ሲጠበቅ የነበረው ምዝገባ የአንድ ወር የጊዜ ገደብ ተይዞለት ነበር፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ባለልጣን የሐይማኖት ጣቢያዎችን ምዝገባ ማራዘሙን ገለፀ

በ10 ቀን ውስጥ ይጀመራል የነበረው የሐይማኖት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ምዝገባ በበይነ መረብ ሚዲያዎች ምዝገባ ሂደት መዘግየት ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስሥልጣን  ለአዲስ ዘይቤ አሳውቋል። ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚጀመር ሲጠበቅ የነበረው ምዝገባ የአንድ ወር የጊዜ ገደብ ተይዞለት ነበር፡፡

ባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዮናታን ተስፋዬ የሐይማኖት ተቋማት ቴሌቭዥኖች የምዝገባ ሂደት ላይ ጣቢያዎቹ በቅድሚያ ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶችን ለመራዘሙ እንደተጨማሪ ምክንያት ገላጸዋል። 

እንደ አቶ ዮናታን ገለፃ ከመስፈርቶቹ መካከል የቴሌቪዥን ጣቢያው አስተምህሮቱን የሚያስተላልፍለት የሐይማኖት ተቋም በሰላም ሚኒስቴር የተመዘገበ መሆኑ፤ የሐይማኖት ተቋሙ ለጣቢያው የሚሰጠው የድጋፍ ደብዳቤ እና እንደማንኛውም የንግድ ድርጅት ከሚመለከተው የመንግሥት አካል የሚሰጥ ዕውቅና ማቅረብ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

“እነዚህን መስፈርቶች ለማሟላት ጊዜ ስለሚያስፈልግ በዚህ ቀን ምዝገባው ያበቃል ማለት አይቻልም” ሲሉ አቶ ዮናታን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በመጋቢት 2013 ዓ.ም. በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ሥራ ላይ የዋለው አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፤ የሐይማኖት ተቋማት የብሮድካስት አገልግሎት ፍቃድ እንዲያገኙ የደነገገውን ተግባራዊ ለማድረግ በቅርቡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የሐይማኖት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።  አዋጁ በተጨማሪም የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን በባለስልጣኑ እንዲመዘገቡና ፍቃድ እንዲወስዱ ይደነግጋል።

“በአዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የተሰጣቸውን መብት ተጠቅመው የሚመዘገቡ የቴሌቪዝን ጣቢያዎች ተገቢውን ሽፋን እና እገዛ የሚያገኙ ሲሆን የማይመዘገቡ ጣቢያዎችን ግን እንደ ሕገ-ወጥ ይታያሉ” የሚለውን የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን መመርያን አስመልክቶ አዲስ ዘይቤ አንዳንድ የሐይማኖት ቴሌቭዥን ተቋማትን አነጋግራለች።

የ“ሚንበር ቲቪ መልቲሚዲያ ፕሮዳክሽን” ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዩ አደም ምዝገባው ለቴሌቭዥን ተቋማቱም ሆነ ለህዝቡ እንዲሁም ለመንግሥት አዎንታዊ ተጽዕኖ ያለው እንደሆነ ያምናሉ፡፡

‹‹የሀይማኖት ቴሌቭዥን ተቋማቱ ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው መንቀሳቀሳቸው በየትም ቦታ ህዝቡን ያንፃሉ ሚሏቸውን ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ሥራዎች በነፃነት መሠራት ይችላሉ፡፡ ህዝቡም በሀይማኖት ሽፋን የሚያጋጭ መልዕክት የያዙ ፕሮግራሞች እንዳይደርሳቸው ያደርጋል'' በማለት ያብራራሉ፡፡

“ይሁን እንጂ ይህ ሕግ መቀመጫቸውን በውጪ ሀገር ያደረጉ እና ባለቤትነታቸው የዚያው ሀገር የሆኑ ነገር ግን ፕሮግራማቸውን በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚያስተላልፉ ጣቢያዎችን እንዴት እንደሚመለከት ግልፅ ቢያደርግ ጥሩ ነው' ብለዋል።

የማኅበረ ቅዱሳን ተወካይም በበኩላቸው ሕጉ መደንገጉ  ለቴሌቪዝን ጣቢያው ጥሩ ሚባል አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ያብራራሉ። “ለአንድ ተቋምም ለሚሰራው ስራ በሕግ የሚከታተለው እና ተገቢውን ድጋፍ የሚያደርግለት አካል መኖሩ ይህ ነው የማይባል ጠቀሜታ እንዳለው ግልፅ ነው'' ሲሉ አክለዋል።

በሌላ መልኩ “ይህ ሕግ መልካምነቱ እኛ የቴሌቭዥን ተቋማቶች ያሉብንን ውስጣዊ ጉዳዮች ከማስተካከል ባለፈ የሚተላለፉትም መልዕክቶች በአግባቡ እና በተጠያቂነት መድረስ እንዲችሉ ከማድረግ አኳያ ግዙፍ ነው። በሕግ ስር መተዳደሩም መስመሩን እንዳይስት ከማድረግ አንፃር ልክ ነው” ያሉት ደግሞ የJPS ቴሌቭዥን ሚዲያ ኦፊሰር አቶ ሰለሞን ግርማ ናቸው።

ሐይማኖታዊ ይዘቶችን ብቻ የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃን በብሮድካስት አገልግሎት ላይ እንዲሳተፉ በአዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቢፈቀድም፤ አሁንም ቢሆን ግን እነዚህን መሰል ተቋማት የራድዮ የስርጭት ሞገድ ማግኘት ላይ ገደብ ተጥሎባቸዋል። በአዋጁ አንቀጽ 40 ላይ የሐይማኖት ተቋማት “ውስን በሆነ የሬዲዮ ሞገድ በመጠቀም የብሮድካስት አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ አይሰጣቸውም” የሚል ድንጋጌ ሰፍሯል። 

ይህን በሚመለከት ያነጋገርናቸው የመገናኛ ብዙኃን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዮናታን በምላሻቸው “ለኢትዮጵያ በዓለም የቴሌኮሙኒኬሽን ማኅበር ለብሮድካስት አገልግሎት የተመደበው የራዲዮ ሞገድ ውስን በመሆኑ ይህን ውስን ሃብት ላለማባከን ነው፡፡ ወደፊት በቴክኖሎክጂው ሀብት ስንዳብር ይህንን ጥያቄ ለማሟላት እንስራለን” ሲሉ አስረድተዋል።

ይህንና መሰል የተሻሻሉ ሕጎችን የያዘው አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው በጥር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ሲሆን የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎ፤ ቀደም ሲል የመገናኛ ብዙኃንን ምዝገባ እና ፍቃድ ሲያስፈጽም የነበረው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ስያሜውን ወደ ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቀይሯል። 

አስተያየት