መጋቢት 17 ፣ 2013

“በትግራይ ከ516 በላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ለክሊኒኮች ሪፖርት ተደርጓል” - የተባበሩት መንግስታት

ወቅታዊ ጉዳዮች

በትግራይ ክልል የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ ከ516 በላይ በሆኑ ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ድርጊት እንደተፈፀመ በክልሉ በሚገኙ 5 ክሊኒኮች ሪፖርት ተደርጓል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።

“በትግራይ ከ516 በላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ለክሊኒኮች ሪፖርት ተደርጓል” - የተባበሩት መንግስታት

በትግራይ ክልል በብሔራዊው የመከላከያ ሠራዊት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይሎች መካከል የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ ከ516 በላይ በሆኑ ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ድርጊት እንደተፈፀመ በክልሉ በሚገኙ 5 ክሊኒኮች ሪፖርት ተደርጓል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
 

በአሜሪካ፤ ኒውዮርክ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት ማብራሪያ የሰጡት የድርጅቱ የኢትዮጵያ ምክትል አስተባባሪ “በታጠቁ የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች እና በብዙ ሰዎች በቤተሰቦቻቸው ፊት የተደፈሩ እና የቤተሰባቸውን አባል እንዲደፍሩ ጭምር የተገደዱ ሰለባዎች ስለመኖራቸው” ተናግረዋል።
 

ከ516 በላይ ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደተፈፀመባቸው ያስታወቁት ምክትል አስተባባሪዋ “ድርጊቱ ሪፖርት የተደረገው በመቀሌ፣ አዲግራት፣ ውቅሮ፣ ሽሬ እና አክሱም ከተሞች ለሚገኙ የሕክምና ተቋማት ነው” ብለዋል።
 

“አብዛኛው የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት በሚችሉበት ደረጃ ላይ ባለመሆናቸውና ከአስገድዶ መድፈር ድርጊቱ ጋር በተያያዘ መገለል ይደርስብናል በሚል ስሜት የተፈፀመባቸውን ነገር ያልተናገሩ ሴቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል” ያሉት ምክትል አስተባባሪዋ “ይህንን ተከትሎ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ቁጥር ከዚህም ሊያሻቅብ እንደሚችል” ተናግረዋል።
 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በትግራይ የአስገድዶ መድፈር እና የንብረት ዘረፋ ድርጊት እንደተፈፀመ ለመጀመሪያ ግዜ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
 

“ሴቶች እኮ አሁን በወንድ ነው የተደፈሩት፤ የእኛ ወታደሮች ግን በሳንጃ ተደፍረዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጁንታ ሲሉ የጠሩት ኃይል “በትግራይ ክልል ከ30 ሺህ በላይ እስረኛ፤ በመቀሌ ከተማ ደግሞ ከ10 ሺህ በላይ እስረኛ ፈትቶ ሄዷል” ካሉ በኋላ “የተፈታው እስረኛ ይዘርፋል፣ የእነርሱ ርዝራዦች ይዘርፋሉ፣ መከላከያም የሚያበላሸው ነገር አለ፤ ሌሎች ኃይሎችም ተጨማምሮ ህዝባችን ጉዳት ላይ ነው ያለው” ማለታቸው አይዘነጋም።
 

“በትግራይ ክልል የአስገድዶ መድፈርና የዘረፋ ጥፋቶች እንደደረሱ መረጃዎች ያመላክታሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆኖ በትግራይ እህቶቻችን ላይ የመድፈር እና ዘረፋ ድርጊት የፈፀመ ማንኛውም ወታደር በሕግ ይጠየቃል፤ እኛ ጁንታን ምታ እንጂ ሕዝባችንን አጎሳቁል አላልንም” ብለዋል።
 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው በእርግጥም የአስገድዶ መድፈር ድርጊት በትግራይ እንደተፈፀመ ማስረጃዎች ያሳያሉ ከማለታቸው በፊት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ ተቋማት እንዲሁም የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ በይፋዊ የትዊተር ገፃቸው ላይ በትግራይ ክልል የአስገድዶ መድፈር ድርጊት እንደተፈፀመ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
 

መንግስት “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ሲል በሰየመው የትግራይ ጦርነት የኤርትራ ወታደሮች ድንበር አልፈው የኢትዮጵያ ግዛት ላይ ሰፍረው እንደነበር ያመኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተናገሩ ሁለት ቀናት በኋላ መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ወደ ኤርትራ፤ አስመራ አቅንተዋል።
 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በእዚያ በነበራቸው ቆይታ ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መነጋገራቸውን የጠቀሰው የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ኤርትራ ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ ግዛት ለማስወጣት ከስምምነት ላይ መድረሷንና ወታደሮቹ ከኢትዮጵያ ግዛት ለቀው ሲወጡ ወዲያውኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቦታውን እንደሚረከብ አስታውቋል። 

አስተያየት