መጋቢት 16 ፣ 2013

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ንግግር ልታደርግ ትችላለች ተባለ

ፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሚቀጥለው ሳምንት ሳውዲ አረቢያ፤ አቡዳቢ ውስጥ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ንግግር ሊያደርጉ እንደሚችሉ አሽራቅ የተሰኘ የሳውዲ መገናኛ ብዙኃን ጠቅሶ የግብፁ አል-አህራም ዘግቧል።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ንግግር ልታደርግ ትችላለች ተባለ

የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሚቀጥለው ሳምንት ሳውዲ አረቢያ፤ አቡዳቢ ውስጥ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ንግግር ሊያደርጉ እንደሚችሉ አሽራቅ የተሰኘ የሳውዲ መገናኛ ብዙኃን ጠቅሶ የግብፁ አል-አህራም ዘግቧል።

 

እ.ኤ.አ 2023 ላይ ሙሉ ለሙሉ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የሕዳሴ ግድብ የሚሰጠኝ ጥቅም ጉልህ ነው የምትለው ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በማደርገው ትግል ውስጥ ግድቡ የሚጫወተው ሚና አይተኬ ነው ትላለች።

 

ሱዳን እና ግብፅ በበኩላቸው በግድቡ ዙሪያ ስምምነት ሳንደርስ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መካሄድ የለበትም ሲሉ ይሞግታሉ።

 

ሁለቱ አገራት ይህንን ሃሳባቸውን ከግብ ለማድረስ ሲሉ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ እና የአፍሪካ ኅብረት ያደራድሩን በሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት የተያዘው የድርድር ሂደት ላይ ፅኑ አቋም እንዳላት በመግለፅ የአገራቱን ጥያቄ ሳትቀበለው መቅረቷ ይታወሳል።

 

አሁን ላይ በተለያዩ የግብፅ የመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰማው ዜና ግን ሶስቱ አገራት በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በቀጣይ ሳምንት በሳውዲ አረቢያ አደራዳሪነት አቡዳቢ ውስጥ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው አማካኝነት ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ነው።

 

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃሳብ ምን እንደሆነ ለማወቅ ለሚኒስቴሩ በርግጥ ኢትዮጵያ በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በሳውዲ አረቢያ አሸማጋይነት አቡዳቢ ውስጥ ከሁለቱ አገራት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ለንግግር ትቀመጣለች ወይ ስንል ጥያቄ አቅርበናል።

 

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲስ ዘይቤ በሰጠው ምላሽ “በጉዳዩ ዙሪያ የተጣራ ነገር ስለሌለ ይሄ ነው ማለት አይቻልም፤ ይሄ ነው ብለን የምናረጋግጠው ነገር የለም” ብሏል።
 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ ወቅት የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሲናገሩ “ሕዳሴ ግድብ በገንዘብ እና ዲፕሎማሲ ዘርፈ-ብዙ የሆነ ጣጣ/ችግር ያለበት ነው፤ ይህ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል በገባነው መሰረት እናሳካዋለን፤ ይህ የሚታጠፍ ሃሳብ አይደለም” ሲሉ መግለፃቸው የሚታወስ ነው።
 

“ኢትዮጵያ፤ ግብፅ እና ሱዳንን የመጉዳት ፈፅሞ ፍላጎት የላትም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሚዘንበውን ዝናብ በሚቀጥለው ክረምት እንያዝ አልን እንጂ የአባይን ወንዝ ፍሰት እንያዝ/እንገድብ አላልንም” ካሉ በኋላ “የግብፅ እና ሱዳን መንግስታት ዝግጁ ከሆኑ ውሃ አሞላልን በተመለከተ ኢትዮጵያ ነገ ጧት ለመፈረም ዝግጁ ናት” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
 

በተያያዘ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የገባችውን የግዛት ይገባኛል ውዝግብ ለመፍታት የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ሁለቱን አገራት እንዲነጋገሩ ለማድረግ ያቀረበችውን ጥያቄ ሱዳን እንደምትቀበለው አስታውቃለች።
 

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ከካቢኒያቸው ጋር በነበራቸው ስብሰባ ጉዳዩን በተመለከተ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ቀረበ የተባለውን ሃሳብ የሚያጠና ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዳቋቋሙ ተናግረዋል።
 

በኤሜሬቶች በኩል የቀረበውን የእናደራድራችሁ ኃሳብ ይመረምራል የተባለው የሱዳን የቴክኒክ ኮሚቴ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ከሚባሉ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጣ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ሪፖርቱን ለካቢኔ አባላት አቅርቧል።
 

በቴክኒክ ኮሚቴው የቀረበውን ሃሳብ መርምሮ ያፀደቀው ካቢኔ በኤሜሬቶች በኩል የቀረበውን ሃሳብ በመርህ ደረጃ እንደተቀበለውና ድርድሩ ግን የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ እንዲሆን ከውሳኔ ላይ እንደደረሰ ተነግሯል።
 

በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት የአቡዳቢው ንጉስ ሞሐመድ ቢን ዛይድ የደህንነት አማካሪ ሞሐመድ ዳህላን የሱዳን ጦር አካባቢውን ከለቀቀ በኋላ ሁለቱ አገራት በሚወዛገቡበት ስፍራ ዓለምአቀፍ ኃይሎች እንዲሰፍሩ ማድረግ እንደሚቻል ሃሳብ እንዳላቸው ዘገባዎች አመልክተዋል ሲል ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።
 

ኢትዮጵያ ሉዓላዊ የግዛቴ አካል በሱዳን የጦር ኃይል ተወሯል እያለች ብትሆንም ሱዳን ግን ገና አስር በመቶ የሚሆነው ግዛት በቁጥጥሬ ስር አልገባም የሚል ሃሳብ ታነሳለች።

አስተያየት