ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የምትገኘው አዳማ በብዙዎች ዘንድ ለስብሰባና ኮንፈረንስ ተመራጭ ናት፡፡ ከልዩ ልዩ የሐገሪቱ ክፍሎች ተገኝተው የሳምንቱን የመጨረሻ ቀናት በተዝናኖት የሚያሳልፉባት ጎብኚዎች ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በየጊዜው ከሚሰሙ አነስተኛ የዝርፊያ ወንጀሎች በቀር የከፋ የእንቅስቃሴ ስጋት እንዳልነበረባትም ነዋሪዎቿ ይመሰክራሉ፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሐገር አቀፍ ስጋት መሆኑን ተከትሎ የተጣለው ገደብ እንደ ሌሎች የሐገሪቱ ከተሞች ሁሉ አዳማንም ጎድቷት አልፏል፡፡ የምሽት መዝናኛዎች አገልግሎት ማቋረጣቸው፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የጭነት ልካቸውን በግማሽ መቀነሳቸው፣ የምሽት እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ መቋረጡ የከተማዋ ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽእኖውን አሳርፏል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት በከፊል ዝግ ሆኖ የነበረው ሀገር አቀፍ አዋጅ ተነስቷል፡፡ በቻልነው ሁሉ በቤታችን እንድንሆን የሚጠይቀው ሕግ አስፈላጊ የሚባሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሁሉ እየወሰድን በኑሮ እንቅስቃሴ ውስጥ እንድንሳተፍ ተፈቅዷል፡፡ ሀገር አቀፍ ምርጫን እስከማራዘም የደረሰው አዋጅ ተሽሮ ህይወት ቀጥላለች፡፡ አዳማ ከተማ ግን ዛሬም በኮማንድ ፖስት ሕግ ውስጥ ያለች ይመስላል፡፡ በከተማዋ ከምሽት 3ሰዓት በኋላ የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን በግል ተሽርካሪም ሆነ በእግር መዘዋወር አለመፈቀዱ ጥያቄ ያጭራል፡፡ ለመሆኑ በአዳማ የሰዓት ገደብ ተጥሏል? ወይስ ከተማዋ በኮማንድ ፖስት ትእዛዝ ስር ትገኛለች?
የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሻምበል ተገኔ የምሽት እንቅስቃሴ ገደብን አስመልክቶ ለአዲስ ዘይቤ በሰጡት ቃል ‹‹ከምሽት 3፡00 በኋላ ምንም ዐይነት ትራንስፖርት አይገኝም፡፡ ድንገት ሰው ቢታመምብን እንኳን ሃኪም ቤት ማድረስ የምንችልበት እድል የለም›› ብለዋል፡፡
ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች የምሽት ታርጋ ተሰጥቷቸው አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር የነገረን አቶ ወንደሰን ጌታቸው የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የተሰማራ ወጣት ነው፡፡
‹‹ሦስት ሰዓት ሳይሞላ ወደ ቤት ለመግባት ሩጫ ነው፡፡ ህዝቡ ወደ ቤት ሳይገባ እኛ ቤታችን ነን፡፡ ምክንያታችን ደግሞ ቅጣት ሽሽት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሕብረተሰቡ ለችግር ተዳርጓል፡፡ በምሽት በእግር ሲንቀሳቀስ ለዝርፊያ እና ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጠ ነው፡፡ እኛም ገቢያችን ቀንሷል፡፡ በኮሮና ምክንያት የተጣለው እግድ ቢነሳም እኛ አሁንም እገዳ ላይ ነን›› የሚለው ወጣቱ ለችግሩ መፍትሔ የሚለውን ሐሳብም ሰንዝሯል፡፡
‹‹ከተማ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱት ‹‹ባጃጆች›› ተገቢው ስልጠና ተሰጥቶ ወደ ሥራ መሰማራት አለባቸው፡፡ እንደቀድሞው የማታ ታርጋ እየተሰጠ በቁጥጥር ስራቸውን እንዲሰሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ የታርጋቸው መጨረሻ ሙሉ ቁጥር የሆነውን አንድ ቀን፣ ጎዶሎ ቁጥር የሆነውን በሌላኛው ቀን እያደረጉ በፈረቃ ቢያሰሩንም ይችላሉ፡፡ ከሥራ አምሽተው የሚወጡ ወይም በልዩ ልዩ ምክንያት ከምሽት 3 ሰዓት በኋላ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ላይ ናቸው››
በጉዳዩ ዙሪያ ሐሳብ ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ብዙወርቅ ሽፈራው አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ብዙወርቅ በእግር እና በትራንስፖርት ብቻ ሳይሆን በግል ተሸከርካሪያቸው በምሽት ለመንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ይናገራሉ፡፡
‹‹አሁን አሁን አዳማ ላይ በምሽት መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነው፡፡ በቀበሌ ታጣቂዎች የሚያስደበድብ ሆኗል፡፡ ለማን አቤት እንደምንል ግራ ገብቶናል፡፡ ሁኔታው የመንቀሳቀስ መብትን የሚገድብ ነው››
የነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን የምሽት መዝናኛዎች፣ የሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ቅሬታ የሆነውን የምሽት እንቅስቃሴ ገደብ አስመልክቶ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ወደ አዳማ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አምርቻለሁ፡፡ የከተማዋ ትራንስፖርት ስምሪት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ገዙ ታደሰ ቅሬታው አልደረሰንም ይላሉ፡፡
‹‹የኦሮምያ መንገድ ትራንስፖርት በመመሪያ ቁጥር 17/45 መሰረት የባለ ሦስት እግር ተሽርካሪዎች የሰዓት ገደቡን ጥሰው ከተገኙ 5መቶ ብር፣ ከተፈቀደላቸው የረዥም ርቀት ተሽርካሪ ውጭ ያሉ 5ሺህ ብር፣ ሚኒባሶች 1ሺህ 5መቶ ብር እንደሚቀጡ ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሰረት የጸጥታ አካላት ሕጉን በማስፈጸም ላይ ይገኛሉ››
ያሉን ሲሆን በመተግበር ላይ የሚገኘውን ሕግ ሕብረተሰቡ እንዲያውቀው ተደርጓል ወይ የሚለውን ጥያቄ ሲመልሱ
‹‹ኮማንድ ፖስቱ ከተነሳ በኋላ የሕብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ፣ በተለይ ምሽትን ተገን ተደርገው የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ሲባል አዋጁ ጸድቋል፡፡ በሕብረተሰብ ደረጃ የተነሳውን ቅሬታ ይዞ ቢሯችን የመጣ ግለሰብም፣ አካላም የለም›› ብለዋል።