የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) አዲስ በሚቋቋመው የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ውስጥ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሊሰየሙ እንደሚችሉ የአዲስ ዘይቤ ምንጭ ተናግረዋል።
የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ለሁለት ዓመት ገደማ ያህል በዋና ዳይሬክተርነት የመሩትን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣንን ለመልቀቅ እፈልጋለሁ ብለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ተከትሎ መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፉት ደብዳቤ “ከመጋቢት 27 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ላበረከቱት አስተዋፅኦ እያመሰገንኩ ከስራዎ እንዲሰናበቱ በጠየቁት መሰረት ከመጋቢት 01 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ስንብቱ የተፈቀደልዎ መሆኑን አስታውቃለሁ” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ለምን እንዳሰቡ ከእርሳቸው በይፋ የተገለፀ ነገር ባይኖርም ማንነቴን ባትገልፁብኝ ያለ ምንጫችን ለአዲስ ዘይቤ ሲናገር “ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ያሰቡት ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀውን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሰረት በማድረግ ሳይሆን አይቀርም።”
እንደ ምንጫችን ገለፃ “በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ላይ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሚባል ራሱን የቻለ ተጠሪነቱም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ መስሪያ ቤት እንደሚቋቋም ተገልጿል።”
አዲሱ ባለሥልጣን ሁለት ከሲቪል ማኅበረሰብ፣ ሁለት ከመገናኛ ብዙኃን፣ ሁለት ለመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ጠቀሜታ እና አግባብነት ካላቸው የተለያዩ ተቋማትና የማኅብረሰብ ክፍሎች እንዲሁም ሶስት አግባብነት ካላቸው የመንግስት አካላት፤ በአጠቃላይ ዘጠኝ የቦርድ አባላት እንደሚኖሩት አዋጁ ይደነግጋል።
ለአራት ዓመት በስልጣን ላይ የሚቆዩትና ከሁለት ግዜ በላይ ሊመረጡ የማይችሉት የቦርድ አባላት የባለሥልጣኑን ዋና ዳይሬክተር ከመለመሉ በኋላ በመንግስት አቅራቢነት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሰየም ያደርጋል።
የሚሾመው ዋና ዳይሬክተር የስራ ዘመን አራት ዓመት ሆኖ ከሁለት የሥራ ዘመን በላይ በሥልጣን ላይ ሊቆይ እንደማይችል የሚደነግገውን አዲሱን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የሚያነሳው ምንጫችን አሁን ያለው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አዲስ በሚቋቋመው የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን መተካቱ አይቀሬ ስለሆነ ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ይህ ከመሆኑ በፊት በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ይዘውት የነበረውን የዋና ዳይሬክተርነት ሹመት በመልቀቅ አዲስ የሚቋቋመውን መስሪያ ቤት ለመምራት እየተዘጋጁ ነው ይላል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ምላሻቸው ምን እንደሆነ የጠየቅናቸው የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር “አሁን የፅሞና ግዜ ላይ ስለሆንኩኝ በጉዳዩ ላይ እንዲህም እንዲያም ነው ለማለት አልፈልግም” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
የእርሳቸው ምክትል የነበሩት አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም ከቀናት በፊት ከተሾሙበት ሥልጣን እንደተነሱ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል እንደተመደቡ ዋዜማ ሬድዮ መዘገቡ ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት መምህሩ ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ ማስተማር እንደሚወዱ ይናገሩ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ጠቅልለው ወደ ማስተማር ስራ ይመለሳሉ አልያም ከዚህ በፊት ይቆጣጠርና ይከታተል የነበረውን የብሮድካስት መገናኛዎችን ጨምሮ የህትመት መገናኛዎችንም ይመራል የተባለውን አዲስ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ይመራሉ ወይንስ ሌላ ውሳኔ ያደርጋሉ የሚለው ጉዳይ ግን በግዜ ሂደት የሚታይ ይሆናል።
በመገናኛ ብዙኃን ስራ ላይ የተሰማሩ አካላትና ጋዜጠኞች የቀድሞውን ዋና ዳይሬክተር ስራ በተመለከተ በጎ ምልከታ እንዳላቸው አዲስ ዘይቤ ከተለያዩ ምንጮቹ ለመረዳት ችሏል።
አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የውጭ ዜጎች እስከ 25 በመቶ ድርሻ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ሲሆን፤ ስም ማጥፋት በሚል በመገናኛ ብዙኃንና በጋዜጠኞች ላይ ይቀርብ የነበረውን የወንጀል ተጠያቂነት በማስቀረት በፍትሃብሔር ብቻ እንዲታይ አድርጎ ደንግጓል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚጣለው የቅጣት ጣሪያ ግን ከ100 ሺህ ወደ 300 ሺህ ብር ከፍ ብሏል።