በኖቭል ኮሮናቫይረስ የሚከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በቻይና ዉሃን ከተማ ውስጥ በህዳር 2012 ዓ.ም መባቻ አከባቢ ነበር። ከወረርሽኙ ከተከሰተ ይህ ጽሁፍ እስከተሰራበት ጊዜ ድረስ በዓለም ዙሪያ 120 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን ከ2.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞት ተመዝግቧል። በኢትዮጵያም የመጀመሪያው ታማሚ የተገኘው 4 መጋቢት 2012 ዓ.ም ሲሆን ቫይረሱ የተገኘበት ግለሰብ የጉዞ ታሪክ ያለው የ48 ዓመት ጃፓናዊ ነበር።
ከታሀሳስ 2012 ዓ.ም ጀምሮ የኮቪድ 19 በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ክትባብን ለማግኘት የተለያዩ ጥናቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ክትባቱን የማግኘቱ ሂደት በተለያዩ ዓለም አቀፍ የመድኃኒት አምራቾች፣ የሀገር መንግስታት እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ውስጥ በተለየ ትብብር እና ፍጥነት ሲካሄድ ቆይቷል።
ክትባት ሰውነታችን በተፈጥሮ ያለውን በሽታ የመቋቋም ሀይል በመጠቀም በበሽታ የመያዝ እድልን ለመቀነስ የሚያስችል ዘዴ ነው። ፀረ እንግዳ አካላትን (antibodies) በመፍጠር የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርዓትን ያሠለጥናል። ክትባት በውስጡ፤ አንድ ሰው ወደፊት በበሽታ ቢጠቃ በሽታውን ለመለየት እና ለመዋጋት የሚያስችለውን አንቲጂን (የተገደለ ወይም የተዳከመ የቫይረስ ወይም የባክቴሪያ ዓይነት) አለው። ሰውነት በመጀመሪያ ወራሪውን ጀርም ያስታውሳል፣ ፀረ እንግዳ አካላትን (ኢንፌክሽኑን ለመዋጋት የሚያስችል በሽታ የመከላከል ብቃት) ያመነጫል፣ ከዚያ የበሽታውን አይነት እና እንዴት መቋቋም እንደሚችል በማስታወስ እራሱን ይከላከላል።
የክትባት ሙከራ በመጀመሪያ የሚደረገው በእንስሳት ላይ ሲሆን ለአደጋ የማያጋልጥ መሆኑ ከታወቀ በኋላ በሶስት የህክምና ምዘና ደረጃዎች በሰዎች ላይ ይሞከራል፤
የመጀመሪያው ምዕራፍ ክትባቱን ለትንሽ ፈቃደኛ ሠዎች ክትባቱን በመስጠት ደህንነቱን ይገመግማል። በክፍል ሁለት ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠዎች በመስጠት ክትባቱ ያለውን የጎንዮሽ ጉዳቶች ለማየት ጥብቅ ክትትል ይደረጋል። በሶስተኛው ምዕራፍ ክትባቱ በሽታን የመከላከል አቅሙን እና ደህንነቱን ለማረጋገጥ በሺዎች ለሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠዎች ይሰጣል። የህክምና ሙከራዎች ሂደቱን ካለፈ በኋላ ሌሎች አስፈላጊ ደረጃዎችን አልፎ ክትባቱ ለህዝብ ይተዋወቃል።
የ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ከ12 ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በርካታ ክትባቶች መሰራት ጀምረዋል። እንደ የኮቪድ 19 የክትባት መከታተያ (COVID 19 Vaccine tracker) መረጃ ከ200 የሚበልጡ የክትባት እጩዎች በመሰራት ላይ ሲሆኑ እስካሁን ድረስ ቢያንስ በአንድ ሀገር ውስጥ የተፈቀዱ 13 ክትባቶች አሉ። የመጀመሪያው የጅምላ ክትባት መርሃ ግብር የተጀመረው በህዳር 2013 ዓ.ም መባቻ አከባቢ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አምስት ክትባቶች ማለትም ሞደርና ፣ አስትራዜኔካ ፣ ፋይዘር / ባዮንቴክ ፣ ሲኖቫክ እና ቤጂንግ የባዮሎጂካል ምርት ክትባቶች ፀድቀው በስፋት ለህዝብ እየተሰጡ እና ክትትል እየተደረገባቸው ይገኛል። ከሁሉም ፍቃድ ካገኙ ክትባቶች ውስጥ አስትራዜኔካ በ13 ሀገሮች ውስጥ 22 ሙከራዎችን ያደረገ ሲሆን በ74 ሀገሮች ውስጥ ተቀባይነት በማግኘት እንዲሁም በወጪ ቆጣቢነት እና በቀላሉ ለማከማቸት ምቹ በመሆኑ የመሪነቱን ደረጃ ይይዛል። ነገርግን ከየካቲት 2013 መባቻ አንስቶ ክትባቱ በአንዳንድ ተቀባዮች ላይ የደም መርጋት ችግር እየፈጠረ ነው የሚሉ የተለያዩ ስጋቶች እና ወሬ አስነስቷል።
የደም መርጋት ማለት የደም ቅንጣቶች ከፈሳሽነት ወደ ጄል መሰል ከፊል ጠጣራማነት የሚለወጡበት ሁኔታ ነው። የደም መርጋት ሰውነታችን አደጋ በደረሰበት ወይም በተጎዳ ጊዜ ብዙ ደም እንዳይፈስ የሚጠቅም አንዱ የሰውነት ተፈጥሯዊ የመከላከያ መንገድ ነው። ሆኖም የደም መርጋት በማይፈለግበት ጊዜ ሲፈጠር ለሕይወት አስጊ ሲሆን አርተሪ (የደም ቧንቧ) ውስጥ ወይም ቬን (የደም ሥር) ውስጥ ሊከሰት ይችላል። በጣም የተለመደው የደም መርጋት የደም ሥር ውስጥ፤ ብዙውን ጊዜ በእግር አከባቢ በሚገኝ የደም ሥር ውስጥ ይከሰታል። ከዚያም በተጨማሪ ግን በሳንባ ውስጥ ፣ በአንጎል ውስጥ (ስትሮክ) ፣ በሆድ ውስጥ እና በልብ ውስጥ (የልብ ድካም) የመሆን እድል አለው። የደም መርጋት ችግር በኮቪድ 19 ህመምተኞች ላይ ከሚታዩ ተያያዥ ችግሮች አንዱ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ሰውነት በሽታን በመከላከል ስርዓቱ ውስጥ ለጎጂ ኢንፌክሽኖች የሚሰጠው ምላሽ አንዱ የሰውነት መቆጣት (ኢንፍላሜሽን) በመሆኑ ነው። ተመራማሪዎች እንደሚግልፁት ኮቪድ 19 ባለባቸው ታካሚዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰውነት መቆጣት ስለሚታይ፣ ሰውነት ደምን በማርጋት ምላሽ ይሰጣል።
ምንም እንኳን ከኮቪድ 19 በፊት በደም መርጋት ምክንያት የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እና አኃዛዊ መረጃዎች በትክክል ባይታወቁም፣ በደም መርጋት እና የደም ዝውውር መቀነስ ላይ በተደረገ አንድ ጥናት መሠረት በአለማችን በየዓመቱ ከ1,000,000 ሰዎች መካከል ከ750 እስከ 2,690 የሚሆኑት የደም መርጋት ያጋጥማቸዋል። እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ከሚሞቱ 4ሰዎች ውስጥ 1ዱ በደም መርጋት በሚከሰቱ ወይም ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች ይሞታሉ።
እንደ አሜሪካ በሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማእከል (ሲዲሲ) መረጃ ከሆነ ፣ በየዓመቱ 900,000 አሜሪካውያን በደም መርጋት እንደሚጠቁ ይገመታል፤ በዚህም ከ 60,000 - 100,000 ገደማ ሞትን ያስከትላል። እንደ አሜሪካ ብሔራዊ የደም መርጋት ጥምረት (National Blood Clot Alliance) በዓመት ከ1000 ሰወች ውስጥ ከ1 እስክ 3 የሚሆን ሰው በደም መርጋት የመያዝ እድል ያለው ሲሆን በአማካኝ 274 ሰዎች በየቀኑ ይሞታሉ። በየ 37 ሴኮንድ አንድ ሰው በምዕራቡ ዓለም ውስጥ በደም መርጋት ይሞታል። በ2011/12 ዓ.ም በተሰራ ዘገባ መሰረት በአውሮፓ ውስጥ በየዓመቱ ወደ 40,000 የሚጠጉ ሰዎችም በዚህ በሽታ ይሞታሉ።
በ28 የካቲት 2013 ዓ.ም ኦስትሪያ አስትራዜኔካ የተባለው ክትባት በደም መርጋት ምክንያት በተከሰተው ሞት ለአፍታ ማቆሟን አስታውቃለች። ያንን ተከትሎም ዴንማርክ፣ ኖርዌይ እና ሌሎችም በአብዛኛው በአውሮፓ ውስጥ ያሉ ሃገራት የአስትራዜኔካ ከትባትን እንዳገዱ ተሰምቷል። እስከ 5 መጋቢት 2013 ዓ.ም ድረስ አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ፣ ታይላንድ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክን ኮንጎን ጨምሮ 21 አገራት ክትባቱን ያገዱ ሲሆን አንዳንዶቹም ክትባቱን ለጊዜው አቁመዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በ11. መጋቢት 2013 ዓ.ም በኮቫክስ ፋሲሊቲ በኩል 2.184 ሚሊዮን የአስትራዛኔካ ክትባቶችን ማግኘቷ ይታወሳል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶር.) በሰጡት መግለጫም ተጨማሪ ምርመራዎች ተደርጎ ክትባቱ የደም መርጋት የጎንዮሽ ችግር እንዳለው እስካልተረጋገጠ ድረስ ኢትዮጵያ ክትባቱን መስጠት እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳል፤ የዓለም ጤና ድርጅት 8 መጋቢት 2013 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ ላይ ማንኛውም የኮቪድ 19 ክትባት በሌሎች ምክንያቶች የሚከሰቱ ህመሞችን ወይም ሞቶችን አይቀንሰውም ሲል አስረድቷል። የአስትራዜኔካ ክትባት የደህንነት ምልክቶችን አስመልክቶ በመግለጫው “የደም መርጋት ችግር በተደጋጋሚ ይከሰታል፤ በዓለም ዙሪያም በጣም ከተለመደ የልብና የደም ዝውውር ቱቦ በሽታ ውስጥ ሶስተኛ ደረጃውን ይይዛል። በአሁኑ ወቅት የአስትራዜኔካ ክትባት ከሚያስከትለው ጉዳት ይልቅ ጥቅሙ ስለሚያመዝን የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቱ እንዲቀጥል ይመክራል” ሲል አስረድቷል።
የአውሮፓ መድሀኒት ኤጅንሲ የደህንነት ኮሚቴ 9 መጋቢት 2013 ዓ.ም ባደረግው ድንገተኛ ስብሰባው ላይ፤ ኮቪድ 19 ራሱ ለደም መርጋት ችግር እና ሞት ሊዳርግ ይችላል ፣ ክትባቱ በራሱ የደም መርጋት አደጋ ከመጨመር ጋር ግንኙነት ያለው አይደለም ፣ በተወሰኑ የክትባቱ ስብስቦች ወይም ከተለዩ የማምረቻ ጣቢያዎች ጋር የተዛመደ ችግር የሚያሳይ ማስረጃ የለም ፣ እና ክትባቱ ቫይረሱን ለመዋጋት እና ለመግታት ያለው ፋይዳ ከጎንዮሽ ጉዳቱ የበለጠ መሆኑን ወስነዋል። በተጨማሪም ኮሚቴው ክትባቱ በጥቂቱም ቢሆን በደም ውስጥ ያሉ የደም ክፍሎች ዝቅተኛ እንዲሆኑ ከሚያደርጉ ክስተቶች ጋር ሊያያዝ ይችላል ብሏል።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የኮቫክስ አስትራዜኔካ ክትባትን ካገኙ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም፤ በ4 መጋቢት 2013 ክትባቱን መስጠት ብትጀምርም፤ የጤናው ሚኒስትር ዶክተር ሊያ እንደተናገሩት መላው ህዝብን ለመከተብ በጣም ረጅም ጊዜ ይወስዳል። አሁን በታቀደው መሰረትም እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ 20% ህዝብን ብቻ ነው መከተብ የሚቻለው። አሁንም የተለያዩ አካላት ኮቪድ 19ን ለመከላከል የሚደረጉ እያንዳንዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መጨመር እንዳለበት ያስጠነቅቃሉ። ክትባቱን አገኛለው በሚል ተስፋ ማንም መዘናጋት ውስጥ እንደይገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።