የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት፤ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ያካሄደው 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ “እውነታችንን መንጠቅ አይቻልም” ባሉ የሕዝብ ተወካይ እና “የትኛውን እውነት” ሲሉ በተከራከሩ ሌላ የሕዝብ ተወካይ መካከል የቃላት ፍልሚያ አስተዳናግዷል።
የፓርላማ አባል አቶ መሐመድ ሃሰን ከሰሞኑ በሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተውን ጥቃት አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄያቸውን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ከሆነ “ግጭቱ የሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ሳይሆን በግልፅ ቋንቋ የኦሮሞ አርሶ አደር እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ነው” ብለዋል።
በቦታው የተካሄደውን ግድያ በተመለከተ የተናገሩት አቶ መሐመድ “በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እና በአጎራባች የሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳዎች ኦነግ ሸኔ በሚባል የዳቦ ስም በወሎ ኦሮሞ አርሶ አደሮች ላይ በቤታቸው፣ በመንደራቸው በክልሉ ልዩ ኃይል በአርሶ አደሩ፣ በወጣቱ፣ በአገር ሽማግሌ እና በተወዳጅ የመስጊድ ኢማም ላይ በተለይ በሸዋ ሮቢት ሆስፒታል በማንነታቸው ምክንያት ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ የተጨፈጨፉ ሰዎች መኖራቸውንና ቁስለኞች፣ ታማሚዎች አስታማሚዎች እንዲሁንም እናቶች ሕክምና ተከልክለው በቤታቸው እና በጤና ጣቢያ እየሞቱ እና ሞታቸውን እየተጠባበቁ ነው” ሲሉ አማረዋል።
“ከነቤታቸው የተቃጠሉ አዛውንቶች፣ ሃብት ንብረታቸው የወደመባቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ላይ የተፈፀመው ጥቃት የተካሄደው በልዩ ኃይል ነው” የሚሉት የፓርላማ አባሉ “ኦነግ ሸኔ በሚል የዳቦ ስም በአማራ አርሶ አደሮች ላይ እየተፈፀመ ያለው የዘር ማፅዳት የጦር ወንጀል በሶስት ምክንያቶች የተካሄደ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” በማለት ተናግረዋል።
“አንድም ኦሮሞ በመሆናቸው፣ ሁለትም ሙስሊም በመሆናቸው፣ ሶስትም የአማራ ክልል ፅንፈኛ ኃይሎች በኦሮሚያ ክልል ባላቸው ፍላጎት የተነሳ የዞኑን ሕዝብ እንደ ቅድመ ክፍያ ቀብድ አስይዘው ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም በወሎ ሕዝብ አንገት ላይ ገመድ አስገብተው እያጠበቁ ፍላጎታቸውን የማሳካት የአጋች ታጋች ድራማ/ሴራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊገነዘብልን ይገባል” ሲሉ አቶ መሐመድ ገልፀዋል።
“የመግለጫ ጋጋታ፣ በሚዲያ ዘመቻ፣ አክቲቪስቶች እንዲሁም ባለሥልጣናት የሉንም ያሉት የፓርላማ አባሉ እውነታችንን መንጠቅ ግን አይቻልም” ካሉ በኋላ “አሁን እየሆነ ያለው ሳታማሃኝ ብላኝ ስለሆነ የፌደራሉ መንግስት ለዚህ ሕዝብ ሊደርስ ይገባል” ሲሉ ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል።
ሌላኛው የፓርላማ አባል አቶ ሰጠኝ አዲሱ ስም ሳይጠቅሱ ነገር ግን “አንዳንድ የፓርላማ አባላት” በሚል ባደረጉት ንግግር “የኢትዮጵያ ሕዝብን ወክለን እዚህ የተገኘነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተላለፍ የሚገባን እውነተኛ እና ትክክለኛ የሆነ መረጃ ለማስተላለፍ ነው ካሉ በኋላ እኛ የምንነጋገረው የበለፀገች ኢትዮጵያን ወደፊት ለማምጣት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“አሁን በአንዳንድ የተከበሩ የምክር ቤት አባላት የሚነገረው ግን” አሉ አቶ ሰጠኝ “በተለያዩ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች የሚገለፅን አስተሳሰብ ባልተረጋገጠና ባልተጨበጠ ሁኔታ የክልል ሆነ የፌደራል መንግስት በትክክል ባልተረዳው አግባብ የሚገለፀው (እዚህ መግለፅ) ተገቢነት ያለው አይመስለኝም” ሲሉ የአቶ መሐመድን ሃሳብ ወርፈዋል።
“እኔ ለረጅም ዓመት በአማራ ክልል በአመራርነት ሰርቻለሁ ያሉት አቶ ሰጠኝ የአማራ ክልል ምክር ቤትም ሆነ የክልሉ መንግስት ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ አቅፎ ያለምንም ልዩነት ከሚተዳደሩበት ክልልሎች አንዱ ነው” ሲሉ ከገለፁ በኋላ “እኔ አሁን ይሄ ነገር እንዴት እንደመጣ አይገባኝም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በበኩላቸው ትልቁ የኢትዮጵያ ካንሰር ከሰፈራችን የዘለለ ነገር አለማሰባችን ነው፤ የሰፈር ሃሳብ ኢትዮጵያን ያሳንሳል፤ እባካችሁ የፓርላማ አባላት ከዚህ አስተሳሰብ ውጡ፤ ይህ አገር የኦሮሞ እና አማራ ብቻ አይደለም በማለት ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኦሮሞ እና አማራን ለማባለት የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉ እያወቃችሁ በከፈቱላችሁ ቦይ መፍሰስ የለባችሁም ሲሉ የፓርላማ አባላቱን ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙገሳ የቸሩት የፓርላማ አባል ወ/ሮ ገበያነሽ ነጋሽ “በብዙ ተግዳሮቶች የተተበተበች አገርን ተረክበው ቋጠሮዋን ለመፍታትና ወደ ብልፅግና ለማድረስ በሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት ዛሬም እንደ ትላንቱ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎንዎ ነው” ብለዋቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወ/ሮ ገበያነሽ ስለቀረበላቸው የሙገሳና ማበረታቻ ቃል ያሉት ነገር የለም።