ጥቁር ሰማያዊ የደንብ ልብስ የለበሱና ቆመጥ የያዙ አድፍጠው ሕገ-ወጥ ናቸው ያሏቸውን የጎዳና ላይ ነጋዴዎች የሚያሳድዱ ደንብ አስከባሪዎችና ፖሊሶች፤ በተደጋጋሚ ያሉበትን አካባቢ የሚቃኙና ድምፃቸውን ጎላ አድርገው የያዙትን ለመሸጥ የሚጥሩ እንዲሁም የያዙትን ይዘው ለመሮጥ የተዘጋጁ ሕገ-ወጥ ናቸው የተባሉ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች፤ በአሳዳጅና ተሳዳጅ መካከል ሆነው ሕገ-ወጥ ናቸው ከተባሉት የጎዳና ላይ ነጋዴዎች የቀረበላቸውን ለመሸመት ጥረት የሚያደርጉ ዜጎች፤ ይህ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በየቀኑ የሚያስተናግዱት ትዕይንት ነው።
የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ መዲና ተብላ በምትጠራው አዲስ አበባ በአሳዳጆችና ተሳዳጆች መካከል የሚፈጠረውን ግብግብ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም። በተለይ በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓታት የሚደራው የመንገድ ዳር ግብይት ከህፃናት አልባሳት ጀምሮ እስከ ኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ብሎም ምግብ ድረስ ይገበያይበታል።
በደንብ ማስከበር እና ቁጥጥር ባለሙያዎች እንዲሁም በፖሊስ የሚሳደዱት የመንገድ ዳር ነጋዴዎች ከአሳዳጆቻቸው መዳፍ እራሳቸውንና የያዙትን ቁሳቁስ ለማትረፍ ሲሉ የማያደርጉት ነገር እንደሌለ የነገረን አንድ የመንገድ ዳር ነጋዴ ስራው የሰቀቀን እንደሆነ ያስረዳል።
“ስራችንን ስንሰራ ኅብረተሰቡ በበጎ ዐይን አይመለከተንም፤ ሰርተው መብላት የሚፈልጉ ዜጎችን ስለምን ያሳድዷቸዋል ሲል ይጠይቀናል” የሚለው ደግሞ ሕገ-ወጥ ናቸው የተባሉትን የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በማሳደድ ስራ ላይ የተጠመደና ስሜን ባትገልፁብኝ ያለ አንድ የደንብ ማስከበር እና ቁጥጥር ባለሙያ ነው።
በሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የደንብ ማስከበርና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ እዮብ ከበደ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ አዲስ አበባ ውስጥ 23,235 ሕገ-ወጥ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች አሉ።
ከ23,235 ሕገ-ወጥ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች ውስጥ 17,779 ያህሉ ላይ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ ገንዘብ እስከ መቅጣትና ንብረት እስከመውረስ የደረሰ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል የሚሉት ዳይሬክተሩ "በዚህ ሩብ አመት ሆነ ተብሎ ውጤታማ ስራ ሳይሰራ ቀርቷል፤ ይህም ሰዎችን መቅጣት ለማንም ደስታ ስለማይሰጥ ግንዛቤ መስጠት ይቀድማል" በሚል እንደሆነ ያስረዳሉ።
ለመሆኑ ሕገ-ወጥ ናቸው በሚል የሚሳደዱት የመንገድ ዳር ነጋዴዎች ለኅብረተሰቡ የሚሸጡዋቸውን ዕቃዎች ከየት ያመጡታል ስንል ነጋዴዎቹንና የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊን ጠይቀናል።
ያነጋገርናቸውና ስማችንን ባትጠቅሱብን ያሉ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች ስለ ዕቃዎቻቸው ምንጭ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በሚካሄዱ ጨረታዎች እንደ ዕድላቸው የሚደርሳቸውን ያልተፈታ ቦንዳ በጨረታ እንደሚገዙና ለሽያጭ እንደሚያቀርቡ ይናገራሉ። አንዳንድ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች ደግሞ መርካቶ ሄደው እዛ ከሚገኙ ነጋዴዎች ዕቃዎቹን እንደሚያገኙ ያስረዳሉ።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሠፋ በበኩላቸው ለሽያጭ የሚቀርቡት ዕቃዎች ምንጭ ከየት እንደሆነ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ “በኮንትሮባንድ የሚገቡ የመኖሩን ያህል ህጋዊ የሆኑ ነጋዴዎችም ከግብር ስርዓት ለመሸሽ ንብረታቸውን ሰውረው በሕገ-ወጥ ነጋዴዎቹ አማካኝነት እንዲሸጥ ያስተላልፋሉ” ይላሉ።
በመንገድ ዳር ንግድ ለ3 ዓመት ያህል አልባሳትን በመሸጥ ያሳለፈውና አሁንም በዚህ ስራ ላይ የሚገኝ አንድ ስሜን አትጥቀሱብኝ ያለ የመንገድ ዳር ነጋዴ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገር “በተደጋጋሚ የንብረት መወረስ ቢያጋጥመውም በህጋዊ መንገድ ገብቶ ለመስራት ግን የገንዘብ አቅም ውስንነት ስላለበት በዚህ ሂደት ለመቀጠል ተገድጃለሁ” ሲል ነግሮናል።
“መንግስት ባዘጋጀው ኢ-መደበኛ የንግድ ስርዓት ላይ ለመካተት ተመዝግቤ የነበረ ቢሆንም ምላሽ ሳላገኝ ወራት ተቆጠሩ” ያለን የመንገድ ዳር ነጋዴ “ምክንያቱ ደግሞ የአዲስ አበባ የነዋሪነት መታወቂያ ስለሌለኝ ይሆናል” ሲል ግምቱን ያስቀምጣል።
በተመሳሳይ መልኩ በዚህ ስራ ላይ ለ10 ዓመት የቆየውና ሜክሲኮ አካባቢ መንገድ ዳር ሲነግድ ያገኘነው አንድ ወጣት እንደነገረን በኢ-መደበኛ የንግድ ማዕቀፍ ውስጥ የተካተተ ቢሆንም የተሰጠውን ቦታ እንደ ዕቃ ማስቀመጫነት በመጠቀም የአዲስ አበባ ጎዳኖችን ለንግድ ማካሄጃ ስፍራነት ይጠቀምባቸዋል።
የተሰጠህ የንግድ ቦታስ ያልነው ይህ ወጣት “የተሰጠኝ ስፍራ ለንግድ ግብይት አመቺ አይደለም” ይላል። የተሰጠውን የመሸጫ ቦታ ከኋላ የሱሪ ኪስ ጋር የሚያመሳስለው ይህ ወጣት “ስፍራው ልክ እንደ ኋላ የሱሪ ኪስ ደበቅ ያለ ነው፤ በመሆኑም ልክ አሁን እንደምነግድበት ጎዳና ገበያ በፍፁም የለውም” ሲል ያማርራል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሠፋ እንደሚሉት ግን ስለ ቦታው አመቺነት ያን ያህል ቅሬታ የሚያስነሳ ነገር የለም። እንደ ምክትል ኃላፊው ገለፃ “ቦታውን አመቺ አድርጎ የማላመድ ስራ የነጋዴው ነው።”
በሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የደንብ ማስከበርና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ እዮብ ከበደ ኅብረተሰቡ ሕገ-ወጥ በሆነ፣ ጥራቱ ባልተረጋግጠና የመንገድ ላይ አደጋ በሚያመጣ እንቅስቃሴ ባለመሳተፍ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
ሕገ-ወጥ ናቸው ከተባሉት የጎዳና ነጋዴዎች ላይ ቦርሳ ሲገዙ ያገኘናቸው በእምነት አያሌው እና ህይወት መንበሩ ግን በገበያው ቅሬታ የላቸውም። “ከሌሎች የንግድ ተቋማት ጋር ሲነፃፀር የምንከፍለው ገንዘብ አነስተኛ ነው” የሚሉት በእምነት እና ህይወት “አመቺ ሁኔታዎች ተመቻችተው ግብይቱ ቢቀጥል” የሚል አስተያየታቸውን አጋርተውናል።
አሁን በመዲናይቱ የሚገኙት የጎዳና ላይ ነጋዴዎች “የእሁድ ገበያ” በሚል ስራቸውን እንደሚያከናውኑት ነጋዴዎች ሁሉ መደራጀት ካልቻሉ አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት አዳጋች እንደሚሆን አቶ እዮብ ከበደ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።