በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ስድስት መስመሮች እና አራት ነባር መስመሮች ላይ አገልግሎት የሚሰጡ የብዙኃ ትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች መነሻ እና መዳረሻቸውን እንዲራዘሙ ይደረጋል ተብሏል።
በዚህም መሰረት ከፒያሳ - ዊንጌት - ሳንሱሲ፣ ከጦር ኃይሎች - አየር ጤና፣ ከቅዱስ እስጢፋኖስ - አራት ኪሎ - ሽሮ ሜዳ፣ ከመገናኛ - ሾላ - ቀበና - 6 ኪሎ፣ ከመገናኛ - ሾላ - ቀበና - አራት ኪሎ እና ከከዛንቺስ - ብሄራዊ ባሉት መንገዶች የአውቶቡስ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም መስመር የነበራቸዉ ነገር ግን እንዲራዘሙ የሚደረጉት ደግሞ ከሜክሲኮ - ሳርቤት - ጀርመን አደባባይ የነበረዉ አስከ ጀሞ፣ ከሜክሲኮ - ሳርቤት - ጀርመን አደባባይ የነበረዉ እስከ ኃይሌ ጋርመንት፣ ከመገናኛ - ላምበረት የነበረዉ እስከ ሳራ አምፖል እና ከሜክሲኮ - ፒያሳ የነበረዉ እስከ አዲሱ ገበያ እንደሚራዘሙና ምንም አይነት የዋጋ ለዉጥ ሳይደረግ አገልግሎት እንዲሰጥ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ማሩ ነግረውናል፡፡
ለብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ የሚያገለግሉ መስመሮች መጀመራቸው የብዙኃን ትራንስፖርት ምልልስ መጠኑን ከፍ በማድረግ አገልግሎትን ማቀላጠፍ እንደሚያስችሉ እንዲሁም የትራፊክ መጨናነቅንና የተሽከርካሪ ግጭትን በመቀነስ ረገድ አስተዋዕፆ እንደሚኖረው የነገሩ አቶ አረጋዊ ከዚህ ቀደም በከተማዋ ተግባራዊ በተደረጉ የአውቶቡስ መስመሮች የሚባክነው ጊዜ በአማካይ በ23 ደቂቃ ማሻሻል እንደተቻለ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ለብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሆኑ አዳዲስ የትራፊክ መስመሮች ለመምረጥ በተደረገዉ ጥናት የመንገዱ የስፋት መጠን በሶስት እና ከዛ በላይ የተከፈለ ከሆነና በመንገዱ ላይ በሰዓት በአማካይ 34 እና ከዚያ በላይ የብዙኃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱበት መሆኑን እንዲሁም በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚጓጓዘው ተሳፋሪ ብዛት ከ202 ሺህ እስከ 300 ሺህ መሆኑ እንደ መስፈርት ተቀምጧል ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።
አገልግሎቱ መቼ ይጀመራል ያልናቸው ዳይሬክተሩ የተለዩትን መስመሮች ቀለም መቀባት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ በአንድ ወር ዉስጥ ተሰርቶ በሚቀጥለዉ ወር መጀመሪያ አካባቢ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል። አገልግሎቱ የሚሰጠው አሁን ስራ ላይ ባሉ የብዙኃን ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እንደሆነና ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች እንደማያስፈልጉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
መጋቢት 10 ፣ 2013
ለብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ የሚውሉ ስድስት አዳዲስ የትራፊክ መስመሮች ተግባራዊ ሊደረጉ ነው ተባለ
በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ስድስት መስመሮች እና አራት ነባር መስመሮች ላይ አገልግሎት የሚሰጡ የብዙኃ ትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች መነሻ እና መዳረሻቸውን እንዲራዘሙ ይደረጋል ተብሏል።